ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!





ውድ የፈረሰኞቹ ገጽ ተከታታዮች ይህ ገጽ 3 አመታት ለቀረቡ ጊዜያት ያህል ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመለከተ ዘገባ ሲሰራ በደጋፊዎች መሃል የሚነሱ ግጭቶችን እምብዛም ሽፋን አይሰጥም ነበር። ምክንያቱም ግጭቶቹ እግርኳሳዊ በመሆናቸው እና በአገራችን ሜዳዎች የሚከሰቱ ግጭቶች የተለመዱ እና እግርኳሳዊ ፉክክሮች የሚያስነሳቸው በመሆናቸው ነበር። እንዲሁም የፈረሰኞቹ ገጽ በዳኛ ውሳኔ ላይ በፍፁም አስተያየት ሰጥቶ አያውቅም። በተጨማሪም በዳኛ ውሳኔ ላይ ግላዊ አሰተያየቶችን በገፃችን ላይ አቅርበን አናውቅም። ምክንያታችንም የዳኛ ስህተት የእግርኳስ የጨዋታ አካል በመሆኑ እንዲሁም ስህተቶች ያሉ እና የሚኖሩ በመሆናቸው ብቻ ነበር። ሆኖም በጅማ ስታዲየም የተከሰተው ፍፁም ከእግርኳስ መሰረታዊ መርህ ያፈነገጠ፣ በእግርኳስ ሜዳ ሊከሰት የማይገባው እና የፈረሰኞቹ ገጽ እንደ አንድ የስፖርቱ ባለድርሻ አካል የምናወግዘው በመሆኑ የተፈጠሩ ሁነቶችም አንድ ሁለት ብለን ልንናገር ወደድን። 


በጅማ ስታዲየም የመጀመሪያው ችግር የተከሰተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ጅማ ከተማ ሲደርሱ ነው። ደጋፊዎቹ በአውቶብሶቻቸው ላይ ሆነው እየዘመሩ ወደ ጅማ ከተማ ሲገቡ ከከተማው ነዋሪዎች የጠበቃቸው ነገር አስደንጋጭ ነበር። «አሸንፋችሁን ከዚህ ከተማ በሰላም እንወጣለን ብላችሁ ካሰባችሁ የዋሆች ናችሁ» የሚሉ ድምፆች በርካቶች ናቸው። ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ከተጓዙ አውቶብሶች መካከል 1 አውቶብስ ላይ ድንጋይ ሲወረወር የፈረሰኞቹ ገጽ አንድ ባልደረባ የዐይን እማኝ ሆኖ ተመልክቷል።  የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን የሚዘልፉ፣ የሚያንጓጥጡ እና የሚያስፈራሩ ድምፆች በየቦታው ሰምተናል። በዚህ ሰዓት የተረዳነው እግርኳሳዊ ፉክክር ያመጣው እንደሆነ እና ይህ ከቀልድ ያለፈ እንዳልሆነ ብቻ ነበር።


የፈረሰኞቹ ገጽ አንድ ባልደረባ ጅማ ስታዲየም የገባው ከቀኑ 6:30 ነበር። ይህም የተደረገው ምን አልባት ስታዲየም ሞልቷል በሚል ምክንያት ወደ ስታዲየም እንዳንገባ እንዳይደረግ በሚል ስጋት ነበር። ወደ ከተማው ቀድመው የደረሱ 2 አውቶብስ ደጋፊዎች እና ከጨዋታ ቀን አስቀድሞ ጅማ ከተማ የደረሱ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም መግባት ጀመሩ። ሆኖም በመቀጠል ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ የተጓዙ 3 አውቶብስ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ ተደረጉ። የተሰጣቸውም መልስ «ስታዲየሙ ሞልቷል። ለእናንተ የሚሆን ቦታ የለንም» የሚል ነበር። በእውነቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ በሚደረግበት በዚህ ሰዓት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የተያዘው ቦታ ባዶ መሆኑን ተመልክተናል። ሆኖም ደጋፊዎች ለረጅም ደቂቃዎች ወደ ስታዲየም እንዳይገቡ ተደረጉ። በዚህ ምክንያት የጸጥታ አካላት በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ደጋፊዎች ጉዳት ደረሰባቸው። በመጨረሻም ከረጅም ሰዓታት በኋላ ደጋፊዎቹ ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ተደረገ። ወደተያዘላቸው ቦታም ሄደው ተቀመጡ።


ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የተያዘው ቦታ ከጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎች ጎነረ ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ያለምንም የቦታ ክፍተት እና ልዩነት ከጅማ አባ ጅፈር ደጋፊዎች ጎን ተጠጋግተው እንዲቀመጡ ተደርጓል። ይህ ስጋት የፈጠረባቸው ደጋፊዎች የጸጥታ አካላትን እና አስተባባሪዎችን ለምን እንዲህ እንደተደረገ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ሰምተናል። ሆኖም የተሰጣቸው ምላሽ «ምንም አይፈጠርም። ስጋት አይግባችሁ፤ እኛ አለን።» የሚል ነበር።


በዚህ አይነት መንፈስ ጨዋታው ተጀመረ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአንፃራዊነት ሰላማዊ በሚባል ሁኔታ ተጠናቀቀ። የጨዋታው ዋና ዳኛ ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ በውስን የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ካሳለፉት የተዛባ ውሳኔ ውጪ የጨዋታን ውጤት የሚቀይር ውሳኔ ሲያስተላልፉ አልተመለከትንም። በዚህም የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ተጨዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አመሩ።


የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ተጀመረ። ጨዋታው በሰላማዊ መንፈስ ቀጠለ። ሆኖም 69ኛው ደቂቃ ላይ የተፈጠረው ድርጊት የጨዋታውን ሙሉ መንፈስ የቀየረ ነበር። 69ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካይ ተጨዋች አብዱልከሪም መሃመድ ከራሱ የግብ ክልል ይዞት የሄደውን ኳስ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት አስደናቂ ጎል አስቆጠረ። በዚህ ጊዜ የተፈጠረው ነገር ሙሉ በሙሉ የስታዲየሙን መንፈስ የቀየረ፣ ከእግርኳስ መርህ ያፈነገጠ እና ሰብአዊነት ያልታየበት ነበር።


በጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎች መሃል የተቀመጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የድንጋይ ናዳ ወረደባቸው። ከተለያዩ አቅጣጫዎች ድንጋዮች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተወረወሩ። ደጋፊዎቹ ወደ ፊትም ወደኃላም ወደ ጎንም ሲሄዱ የፍንጋይ ናዳ ይወርድባቸው ነበር፡፡ በዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጉዳት አስተናገዱ። ከተለያዩ አቅጣጫዎች ድንጋይ የተወረወረባቸው ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ መቆየት የሚያስችላቸው ነገር አልነበርም። በመሆኑም ህይወታቸውን ለማትረፍ ያላቸው አማራጭ ወደ ሜዳ ውስጥ መግባት ብቻ ነበር። በመሆኑም ጉዳት ያስተናገዱ በርካታ ደጋፊዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተይዘው ሁሉም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ውስጥ ገቡ። በዚህ ሰዓት ጉዳት ያስተናገዱ ደጋፊዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አልነበረም። በሜዳው ውስጥ በየቦታው በርካታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወድቀዋል፡፡ በየቦታው ደማቸው ፈሶ ይታያል፡፡ በጅማ ስታዲየም ያሉ የቀይ መስቀል ሰራተኞች ህክምና መስጠት እስኪያቅታቸው ድረስ ደጋፊዎች በየቦታው ወድቀዋል፡፡ በሜዳ ውስጥ የሚሰማው ጩኸት እና ለቅሶ ሰው መሆንን ለመጥላት ያደርሳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የህክምና ቡድኖች የተፈነከቱ፣ የተሰበሩ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ደጋፊዎች ህክምና በመስጠት ተቀላቀሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች በየቦታው የሚያለቅሰውን ደጋፊ በማባበል ላይ ተሳተፉ፡፡




አስገራሚው ነገር ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ ከመቀመጫ ቦታቸው ተፈንክተው እና ተሳደው ሜዳ የገቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሜዳ ገብተውም ድንጋይ ውርወራው እና ጥቃቱ አልቆመም ነበር፡፡ ከተለያዩ የስታዲየም ቦታዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ድንጋዮች ይወረወሩ ነበር፡፡ በዚህ ሂደትም የቅዱስ ጊዮርጊስ የካሜራ ባለሙያ ከጥላፎቅ በተወረወረ የለስላሳ መጠጥ ጠርሙስ ተፈነከተ፡፡ የጸጥታ አካላት በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የተቀመጡበት ቦታ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ደጋፊዎችን ይወተውቱ ነበር፡፡ ሆኖም ስፍራውን ከተቃራኒ ደጋፊዎች ነጻ አላደረጉም፡፡ ጥቃቱ ላይ የተሳተፉ ደጋፊዎችን ከስታዲየም የማስወጣትም ሆነ የማራቅ ተግባር አልፈጸሙም ነበር፡፡




ጉዳት ያስተናገዱ ደጋፊዎች የህክምና እርዳታ ተሰጣቸው፡፡ ራሳቸውን የሳቱ እና ከበድ ያለ ጉዳት ያስተናገዱ ደጋፊዎች ወደ ጅማ ሆስፒታል በአምቡላንስ ተጓዙ፡፡ የጥቃት ሰለባ የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በድፍን ስታዲየም ታዳሚዎች ለመግለጽ የሚከብድ ስብድ ሲያስተናገድዱ በስፍራው እየተመለከትን ነበር፡፡ በጣም አሳፋሪው ነገር በርካታ የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎች ባደረጉት ድርጊት የሚኮሩ ነበሩ፡፡ በነውራቸው ሲኮሩ በአደባባይ ተመልክተናል፡፡ በዜማ «ጅማ ማለት እንዲህ ነው» ብለው ሲዘምሩም በዐይናችን ያየነው ሃቅ ነው፡፡


የፈረሰኞቹ ገጽ ይህንን ድርጊት በካሜራ ለማስቀረት በሚሞክርበት ሰዓት ከጸጥታ አካላት ግልጽ ማስፈራሪያ እና ድርጊቶችን መቅረጽ የማይቻል መሆኑ ተገለጽልን፡፡ በተጨማሪም ካሜራው የቀረጻቸው ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ተከፍቶ እንዲታይ ተደረገ፡፡ ሆኖም አስቀድመን የቀረፅናቸውን ምስሎችና ቪዲዮ ሚሞሪ ካርዶች ወደ ሌሎች የፈረሰኞቹ ገጽ አባላት ስልክ ልከን ስለነበር በካሜራችን ላይ የተገኘው ሚሞሪ ባዶ ስለነበር ከሚደርስብን ጥቃት ልንተርፍ ችለናል፡፡



በመቀጠል የጸጥታ አካላት እና የጅማ አባ ጅፋር የክለብ አመራሮች ጨዋታው እንዲቀጥል ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከግቡ ጀርባ እንዲሆኑ በማድረግ ጨዋታው እንዲቀጥል ለማድረግ ተሞከረ፡፡ ሆኖም በድጋሚ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላይ የድንጋይ ጥቃት በመፈጸሙ ሊሳካ አልቻለም፡፡ የጸጥታ አካላት ከግቡ ጀርባ ባለው የስታዲየም ክፍል በመቆም ደጋፊዎች ከግቡ ጀርባ በመሆን ጨዋታውን እንዲጀመር ለማድረግ ሞከሩ፡፡ በመጨሻም ተሳክቶ ጨዋታው ከ48 ደቂቃዎች በኋላ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡










የፈረሰኞቹ ገጽ በማንኛውም ጨዋታ ላይ የሰዓት አያያዝ ላይ የማያወላዳ አቋም አለው፡፡ በጨዋታዎች ላይ 2 የገጹ አባላት ሰዓት እንዲይዙና ድርጊቶችን እንዲመዘገቡ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ጨዋታው ለ48 ደቂቃዎች መቋረጡን አረጋግጠናል፡፡ ጎሉ የተቆጠረው 69ኛ ደቂቃ ላይ በመሆኑ እና ተጨዋቾች ደስታቸውን ሲገልጹ ከቆዩባቸው ደቂቃዎች መነሻነት ጨዋታው 70 ደቂቃ ብሎ ቀጠለ፡፡ እኛም ጨዋታውን ከ70ኛ ደቂቃ አንስቶ በቀጥታ የጽሑፍ ስርጭት ማስተላለፋችን ቀጠልን፡፡


ከጨዋታው መቀጠል በኋላ የጨዋታው ዋና ዳኛ ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ግራ የሚያጋቡ ነበሩ፡፡ ሆኖም ጨዋታው ያለምንም መቆራረጥ ቀጥሏል፡፡ ይህ ነው የሚባሉ ሰዓት ማባከኖች እና መሰል የሰዓት መግደል አካሄዶች እምብዛም አልተመለከትንም፡፡ ጅማ አባ ጅፋሮች በረጅም ኳስ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ፈረሰኞቹ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ በዚህ ሂደት በጨዋታው 85ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታው ዋና ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ለአቡበከር ሳኒ የቢጫ ካርድ ያሳዩታል፡፡ አቡበከር ሳኒ የሰራው ጥፋት ካርድ የሚያስመዝዝበት ነው ብሎ መናገር ቢከብድም ዋናው ዳኛ ከአቡበከር ሳኒ ጋር የተነጋገሩትን ማወቅ ስለማንችል ውሳኔውን መተቸት አንችልም፡፡ በዚህም ዋናው ዳኛ ቢጫ ካርዳቸውን ቀይረው አቡበከር ሳኒን በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጡት፡፡


ይህ ሲከናወን ጨዋታው 85ኛ ዲቂቃ ላይ ነበር፡፡ ጅማ አባ ጅፋሮች ምንም ንክኪ ባልነበረበት ቦታ ላይ ተደጋጋሚ የቅጣት ምት ሲሰጣቸው እየተመለከትን ነው፡፡ እንዲሁም የተሰጣቸው ቅጣት ምት ቦታውን በመልቀቅ ኳሶችን ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን ሲያስጠጉ ዋናው ዳኛ ለአንድም ጊዜ ሲከለክሉ አልተመለከትንም፡፡


መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቀቀ፡፡ ሆኖም ጭማሪ ሰዓት አልታየም፡፡ የጨዋታው 4ኛ ዳኛ የሰዓት ጭማሪውን ሳያሳዩ 3 ደቂቃዎች አለፉ፡፡ 93ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታው ዋና ዳኛ 5 ተጨማሪ ደቂቃዎችን አሳዩ፡፡ ይህ ግራ የሚያጋባ ድርጊት ነበር፡፡ 4ኛው ዳኛ ይህንን ተጨማሪ ደቂቃ ማሳየት ያለባቸው በጨዋታው 90ኛ ደቂቃ ላይ ቢሆንም ጭማሪ ደቂቃውን ሲያሳዩ ጨዋታው 93ኛ ደቂቃን እያገባደደ ነበር፡፡


ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ ጨዋታው መገባደድ የነበረበት 95ኛ ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው የተጨዋች ለውጥ ስለነበር ቢዘገይ እንኳ ለጥቂት ደቂቃ ነበር፡፡ በጨዋታ አጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጣት ምት አግኝቶ ዋና ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ይህንን ቅጣት ምት ሊያስመታ ወደ መስመር በተጠጋበት ሰዓት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሰዓት ማለቁን ስሙን እየጠሩ ይገልጹለታል፡፡ ሆኖም የዋና ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ምላሽ እጅግ አሳፋሪ ነበር፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላይ የማይገባ ድርጊት በማሳየት ወደ ጨዋታው ተመለሰ፡፡ ይህንን የፈረሰኞቹ ገጽ በቅርበት ሆኖ ተመልክቷል፡፡


ዋናው ዳኛ ጨዋታውን ቀጥለው 102ኛ ደቂቃ ላይ ደርሰዋል፡፡ መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ ጭማሪ ሰዓት ከታየ 12 ደቂቃዎች አልፈዋል፡፡ ሆኖም ጨዋታው በዳኛው ፊሽካ አልተጠናቀቀም፡፡ በዚህ ሂደት የጨዋታው የመሃል ዳኛ ለጅማ አባ ጅፋር የፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ፡፡ ይህ ሲከናወን የጨዋታው መደበኛ ደቂቃ እና ጭማሪ ደቂቃ ከተጠናቀቀ 7 ደቂቃዎች አልፈው ነበር፡፡


የጨዋታው ዋና ዳኛ ለጅማ አባ ጅፋር ፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጡ ቁጥራቸው 3 የሚደርሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እየሮጡ በመግባት ዋናው ዳኛ ላይ ጥቃት ለመስንዘር ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ተጨዋቾቹን ስለያዟቸው ዳኛው ጋር ሳይደርሱ ተመልሰዋል፡፡ በዚህ ሂደት በርካታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በጸጥታ አካላት ድብደባ ሲፈጸምባቸው የፈረሰኞቹ ገጽ የዐይን እማኝ ሆኖ ተመልክቷል፡፡ በዱላ፣ በፌሮ፣ በቦክስ እና በእርግጫ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከባድ ድብደባ ሲፈጸምባቸው ተመልክተናል፡፡ ሴቶች እና ህጻናት የዚህ ድብደባ ሰለባ ነበሩ፡፡ በርካታ ደጋፊዎች በጸጥታ አካላት በደረሰባቸው ድብደባም ተጎድተዋል፡፡




ጨዋታው በድጋሚ 8 ደቂቃዎች ያህል ተቋርጦ ከቆመበት ቀጠለ፡፡ ጅማ አባ ጅፋር የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት አስቆጠረ፡፡ ከዚህ በኋላ የጨዋታው ዋና ዳኛ ይርጋለም ወልደ ጊዮርጊስ የጨዋታው መጠናቀቅን የሚያውጀውን ፊሽካ አሰሙ፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቂያ በኃላ ሁሉም የቡድኑ አባላት በከፍተኛ ልቅሶ ከደጋፊው ጋር ተቃቅፎ ሲያለቅሱ መመልከት እጅግ ልብን ይነካ ነበር። ከዚህ በኋላ የጸጥታ አካላት የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎችን ከሜዳ ለማስወጣት አስለቃሽ ጭሶችን ተጠቀሙ፡፡ ሆኖም 1 ሰዓት ያህል ስታዲየሙ ሊረጋጋ አልቻለም ነበር፡፡ በመጨረሻም የጅማ አባ ጅፋር ደጋፊዎችን ከስታዲየም በማራቅ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ከስታዲየም ወደ ሆቴላቸው አጅቦ ወስዷቸዋል፡፡ ምን አልባትም የልዩ ኃይል የፀጥታ አካላት ወደ ስታዲየም ባይመጡ ኑሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከስታዲየም በሰላም መውጣታቸው እጅግ አስጊ ነበር፡፡



የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከአዲስ አበባ ሲነሱ ፍፁም በሆነ ቀናነት ነበር፡፡ ለዚህም በጅማ ለሚኖሩ አቅመ ደካሞች የሚሆን አልባሳትን ጨምሮ በርካታ የእርዳታ ቁሳቁሶችን በመያዝ ወገኖቻቸውን ለመርዳት ቀና ልብ ነበራቸ፤ ነገር ግን ይህንን ሳያሳኩ የገዙትንም ቁሳቁሶች እንደያዙ ወደ መጡበት ለመመለስ ተገደዋል፡፡ ጨዋታው መጠናቀቅ ከነበረበት እጅግ በጣም ዘግይቶ በመጠናቀቁ በዚህ ሁሉ ትርምስ መሃል ግን ቀና ለመሆን የሚጥሩ እና ለሙስሊም ደጋፊዎች እና ተጨዋቾች ለማስፈጠሪያ ውሃ የሚያቀብሉ የጅማ አስተባባሪዎችን ተመልክተናል።


በመጨረሻም አንድ የጅማ ከተማ ነዋሪ ለፈረሰኞቹ ገጽ በውስጥ መስመር ያደረሰንን መልዕክት እናስፍር፡-

«ሙቀቱ የጀመረው የሳንጃው ደጋፊዎች በመንገዱ ሁሉ ሲዘምሩ ነው። እኔም አብሬ በሳንጃው «እናሸንፋለን» መዝሙር ለማበድ ትክክለኛውን ጊዜ እየጠበኩ ነበር። ጨዋታው ሲጀመር ግን ከሳንጃው ወንድሞቼ ጋር ቆሞ ለመዘመር አቃተኝ፡፡ ምክንያቱም የከተማው ሰዎች ቢያዩኝ ህይወቴ እዚህ ከተማ ላይ እንዳይበላሽ በሚል ስጋት ነው። ያደረሱት ግፍ ሁሉ እንደሰራላቸው ይሰማኛል። ያሳዝናል፡፡»

Comments

Popular posts from this blog

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምስረታ እና ጉዞ!