የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምስረታ እና ጉዞ!




እግር ኳስ የወንድማማችነት፣ የሰላም፣ የአብሮነት መሰረት መሆኑን በፍቅራችንን እያሳየን እነሆ 82 ዓመት ሞላን። በአራዳ ጊዮርጊስ አከባቢ የተመሰረተው የእኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ እልፎችን በድል፣ በክብር እና በፍቅር አስከትሎ የ82 ዓመታትን ዕድሜ ደፈነ። ታህሳስ ወር የኛ የቅዱስ ጊዮርጊሳዊያን ወር ነው። ከዘመን ቀድመው የዘመኑ ወጣቶች ቅዱስ ጊዮርጊስን የመሰረቱበት ወር ነው። 1 ተብሎ የተጀመረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስረታ ዘመናትን በክብር ተሻግሮ ዛሬ ላይ 82 ዓመታትን ደፈነ።


በአራዶቹ መንደር ፒያሳ የተመሰረተ፣ በኳስ የልዩነትን ድንበር ያለፈ፣ በአርበኝነት ትግል ውስጥ አሻራውን ያሰረፈ፣ ሰንደቅ አላማችንን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የአቅሙን የጣረ፣ ትላንትም ሆነ ዛሬ ያለማቋረጥ በድል መስመር የተጓዘው ክለባችን ዛሬ በያዝነው የታህሳስ ወር 82ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። እንኳን አደረሰን! እንኳንም የዚህ ዘመን ተሻጋሪ ክለብ ቤተሰብ ሆንን!


ከዛሬ 82 አመት በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምስረታ እና ጉዞ!

አየለ አትናሽ እና ጆርጁ ዱካስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መስራች ናቸው። ክለቡን ሲመሰርቱት ወጣት ነበሩ። ማንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ያን አስቸጋሪ ዘመን ይሻገራል ብሎ ባያስብም በእነዚህ ልበ ብርቱ ወጣቶች አነሳሽነት እና ክለቡን በተቀላቀሉ ቆራጥ የዚያ ዘመን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ጥረት ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ክለብ ቆመ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ያኔ ያቋቋሙት ጊዮርጊስን ይሁን እንጂ ቡድኑ ጠንካራ መሰረት ከያዘ በኋላ ጣሊያኖችን ድል አድርጎ ለኢትዮጲያ ታሪክ ሰርቷል። ይህ ቡድን በጣሊያን ጊዜ በዚያ ቀውጢ ሰዓት እንኳን ሳይፈርስ የቆየው በቡድኑ ውስጥ ወንድማማችነት እንዲሁም ከቤተሰብ ደረጃ የሚበልጥ ፍቅር በተጨዋቾቹ መሃል የተሳሰረ በመሆኑ ነው።


አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ህልውና ከመታገላቸውም ሌላ የአራዳ ዘበኛ ዱላ እና እርግጫ ሳይቀር እየተከተላቸው ቡድኑን ይዘው ተጉዘዋል። ጊዮርጊስ ከሁሉም ብሔረሰብ የተውጣጣ ተጫዋች የሚገኝበት ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ዜጎችም የቡድኑን ተጫዋቾች ፍቅር በማየት ከልብ በመውደድ እነርሱም ተቀላቅለው የተጫወቱበት ወቅት ነበር።



አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ዱካስ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምስረታ እና መሰል ታሪኮች ያወጉትን እስኪ ለ82ኛ ዓመት ክብረ በዓላችን ይሆን ዘንድ ወዲህ እናምጣው፦


ቅዱስ ጊዮርጊስ የተመሰረተው እነ ጆርጅ ዱካስ ቤት በሚገኘው ዶሮ ማነቂያ ነው። የአራዳ ዘበኛ የጊዮርጊስ ጠላት ነበር። ተጫዋቾቻችንን ሁሉ አስሮብናል። ቡድን መሆኑን አያውቁም፤ ወሮበሎች እንመስላቸው ነበረ። እኛ ግን ያሰባሰበን የወንድማማችነት ፍቅር ስለነበረ የአራዳ ዘበኛ በየሄድንበት እየተከታተለ ቢያባረንም አልተበገርንለትም። ቀኑን በሙሉ በየቦታው እየሄድን ሜዳ ስናፈላልግ ሳናገኝም ሆነ አግኝተንም ቢሆን እየተባረርን ሳንጫወት መሽቶብን የተመለስንበት ወቅት ነበር።

አንድ ቀን ፍልውሃ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አሁን ጉምሩክ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኛበት አጠገብ የጎል አግዳሚ እና ቋሚ ተሸክመን በመሄድ ልምምድ ስናደርግ የሳር ቦታ ነው ተብለን ተባረርን። እንደገና ጎላችንን ነቅለን እዚያ አሮጌ ቄራ አከባቢ የእቴጌ መስክ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ለመጫወት ጎላችንን ተክለን ስንጀምር የሰፋሩ ሰው ተረባርቦ አባረርን። ከዚያም እንደገና ጎላችንን ነቅለን በላይ ዘለቀ መንገድ ዘበኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ስንጫወት የአራዳ ዘበኛ መጥቶ አባረርን፤ ነገር ግን አንድነታችን እየጠነከረ ስለመጣ ሊለያዩን አልቻሉም። እኛን ለመለያየት ያልተሞከረ ነገር አልነበረም።

አንድ ጊዜ ከአርመኖች ጋር ለመጫወት ተነጋግረን የጎል እንጨታችንን ተሸክመን እነርሱን አስከትለን በየሰፈሩ ስንሄድ ሲያባርሩን ተስፋ ሳንቆርጥ አርመኖች ጥለው እንዳይሄዱ ስናባብላቸው ቆየን፡፡ «በቃ እዚያኛው ቦታ ማንም የለም» እያልን ስንሄድ ሲያባርሩን በመጨረሻ በችግር ምክንያት ልጆች ስላልነበሩን «ባለን ልጅ እንገጥማችኋለን» ብለን በራድ መኮንን ድልድይ ስናልፍ ይድነቃቸውን አገኘነው። ተፈሪ መኮንን ት/ቤት እንተዋወቅ ስለነበረ አርመኖች ከመንገድ ዳር ሲጠብቁን ለይድነቃቸው «ሰው ጎድሎን ነው፤ ለምን አታግዘንም?» አልነው፡፡ እርሱም የመጫወት ዕቅድ ባይኖረውም ጥያቄያችንን ተቀብሎ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ሜዳ ተጫውተን 2—0 አሸነፍን፡፡ ሁለቱን ጎል ያገባው ይድነቃቸው ነበር።


በመሰረቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በሁለታችን አዕምሮ ተጠንስሶ በሁለታችን አማካኝነት ይመስረት እንጂ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለዚህ እንዲበቃ ያደረገው ይድነቃቸው ነው። ስለቡድኑ መመስገን የሚገባው እርሱ ነው። እኛ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሰረትነው እሱ ደግሞ ከኢትዮጲያ ህዝብና ከአፍሪካ ጋር አስተዋወቀው። እኛንም በኢትዮጲያ የእግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያዎቹ የኳስ ቡድን መስራቾች ተብለን እንድንጠራ አበቃን። ከእኛ በኃላ ብዙ ቡድኖች ተቋቁመው ነበር፤ ነገር ግን እንደ ይድነቃቸው አይነት ጠንካራ ሰው ስላልነበራቸው ፈራርሰው ቀሩ። ስለዚህ ይድነቃቸው ለጊዮርጊስ ባቻ ሳይሆን ለኢትየጲያ ስፓርትም ዕድገትም ባለውለታ ነው።


የክለባችን የመጀመሪያ መለያ ቡናና ነጭ ነው። ይሄንን የመረጥነው ወደን አልነበረም። ገንዘብ ይጎድለን ስለነበር ያለን ሁለት ጠገራ ብር ስለሆነ ፒያሳ «ግሪካዊ አውግስታስ ዱስ» ከተባለ ሱቅ በርካሽ ያገኘነው ይሄ ስለሆነ ነበር ልንገዛ የቻልነው።


ከዚያ ቀስ በቀስ ገንዘብ እያገኘን ስንሄድ የመጀመሪያውን ማሊያ ለሁለተኛ ቡድን ሰጥተን ተመካክረን አንድነታችንን የሚገልፅ መደቡ ነጭ ሆኖ የኢትዮጲያ ባንዲራ ያለበትን ማሊያ አሰራን። በዚህ ማሊያ ፎቶ ከመነሳት በስተቀር ግጥሚያ ሳናደርግ ጣሊያን ገብቶ ቡድናችንን አፈረሰብን። ሁላችንም ከውስጥ አድርገን ጨረስነው። በተገናኘን ቁጥር ተደብቀን ተጫዋቾች የቡድናቸውን ፍቅር የሚገልፁት ከውስጥ አድርገው በመጫወት ነው።

-
ገንዘብ የምናገኘው በቀላሉ አልነበረም። ጆርጅ ከቤተሰቡ የደብተር መግዣ ብሎ ይቀበላል። ሌላውን ደግሞ «ሆያ ሆዬ» እንጨፍራለን። ያኔ ገንዘብ አይሰጥም የሚሰጠን ዳቦ ነው። ይህንን ዳቦ በኮሮጆ ሰብስበን ወዛደር ሰፈር የሚባል ቦታ ወስደን ዳቦው ይሸጣል። ያንን ገንዘብ ተቀብለን ማሊያ ከተገዛ በኃላ የሚተርፈውን ጨዋታ ባለ ጊዜ ፋርኖ እና ቆሎ ይገዛበታል። በልምምድ ወቅት ራቅ ያለ ስፍራ ስንጓዝ ያንን ቆሎ እየቆረጠምን እንጓዛለን። አድካሚ ጨዋታ የሚኖርብን ከሆነ ዳቦና ሻይ እንበላለን። ይህም ሻይ ቤት ሄደን አይደለም የምንበላው፤ በሁለት ቤሳ ለብዙ ቀን የሚሆነን ስኳር እንገዛለን። የስኳሩ ምርቃት ሻይ ቅጠል ነው። ያንን ይዘን የገዛነውን ፋርኖ ዳቦ ጋግረን የክለቡ መስብሰቢያ የሆነው በጆርጅ ቤት ሻይ አፍልተን እንጠጣለን። በልተን ከዚያ ፀሎት አድርገን እንሄዳለን።


በወቅቱ ጊዮርጊስ የነበረው ንብረት ሁለት ጠገራ ብር፣ አንድ ኳስ፣ የጎል አግዳሚና ቋሚ እንጨቶች እና ማህተም ነበሩ። ጣሊያን ሲገባ ሁሉም ነገር ተተረማመሰ፡፡ ዋናው ጣሊያን ቤዙ ደግሞ አራዳ ጊዮርጊስ ነበር፡፡ ያ ደግሞ የእኛ መሰብሰቢያ ነበር። ሆኖም እኛ የአንድ ሰፈር ልጆች በመሆናችን ማሊያውን ከውስጥ ለብሰን እየተሹለከለክን ቡድናችን እንዳይፈርስ እንታገል ነበር። በመኃል ጣሊያኖች ጆርጅን ወስደው አሰሩት፡፡ ይድነቃቸውም ጣሊያን ሄደ። ጣሊያን ሲገባ ሁሉም ነገር ዝብርቅርቅ ብሎበን ነበር፡፡ ዘረፋው በየቦታው ነበር፡፡ አዲስ አበባን የሚያስተዳድራት አልነበረም።


ጆርጅ ከእስር ከተፈታ በኃላ ወደ ቤት ተመለስን፡፡ የክለባችን ንብረት በጠቅላላ ተዘርፎ ነበር። የጣሊያንን ነገር ተወው። በተለይ የእኛን ክለብ ብዙ ነገር በድሏል፤ አስለቅሶ ነው የለቀቀን። ዕንባችንን እየዘራን ስንሄድ እያዩ ይስቁብን ነበር። አንድ ቀን አንድ አርመናዊ ከብዙ ጊዜ በኃላ አንዲት ኳስ ሰጥቶን ነበር፡፡ የሰጠን አዲስ ኳስ ነው፡፡ ተጋጣሚ ጠርተን ሌሊቱ አልነጋ አለን፡፡ ጊዮርጊስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ኳስ ሊጋጠም ነው። ኳሷ ገና አልተነፋችም ነበር፡፡



ሲነጋ ብስክሌት የሚያከራዩት እስኪመጡ ጠብቀን እነርሱ ፓምፕ ስላላቸው በነፃ ይነፋልናል። እዚያው አከባቢ የነበረ አንድ ጣሊያናዊ ጎሚስታ ያለው ሰው «እኔ እነፋላችዋለሁ» አለንና ሰጠነው። የተንኮሉ ብዛት ኳሱን ራሱ ይዞ በኮምፕሬሰር ነፍቶ ከአቅም በላይ አየር በመጨመሩ ያቺ አዲስ ኳስ አየር ላይ ፈነዳች። እሱ ግን ቆሞ ይስቅ ነበር። እኛ ሁሌ በዚያ ስናልፍ የነበረን ፍቅር ያስቀናው ነበር። አሁን ግን ኳሳችንን አፈንድቶ ተበቀለን።የምንይዘውና የምንጨብጠው ጠፋን፤ ዕንባችን ከዐይናችንን ዱብ ዱብ ሲል እርሱ የተበታተነችውን ኳስ በእጁ ይዞ ያፌዝብን ነበር። ያለችንን ንብረት እንደዚህ ጉድ አደረገብን።


ጣሊያኖቹ በአጠቃላይ የኢትዮጲያ ህዝብ እንደ ሌሎቹ ለእነርሱ ፍፁም አልተመቻቸውም ነበርና በዚህም የተነሳ ይናደዱ ነበር። በአብዛኛው ህዝቡ ይፋቀር ስለነበር ለመለያየት ሞክረው አልተሳካላቸውም። በተለይ የእኛ ክለብ እየታወቀ ሲመጣ ህዝባዊነትን በመላበሱ ጣሊያኖች ያነጣጠሩት እኛ ክለብ ላይ ነበር። የእነርሱ ተንኮል የማያልቅ ነበር። ሌላው ቀርቶ ዶሮ እያዞሩ የሚሸጡ ኢትዮጲያኖችን «እስኪ አምጣው?» ይሉና «ስንት ነው?» ይላሉ፡፡ «ይህን ያህል» ሲሏቸው «ቀንስ! በዚህን ያህል» ይሏቸዋል፡፡ «ይኸው ነው» ሲሉ አይናቸው እያየ የዶሮውን አንገት በጥሰው ይሰጧቸዋል። መቼም የሞተ ዶሮ ይዞ የሚዞር ስለሌለ ባሉት ዋጋ ይሸጡላቸዋል።


አትዮጲያ ውስጥ ከእኛ ቀጥሎ ክለብ የተቋቋመው በጣሊያን አማካኝነት ነበር። ከእኛ በኃላ ያሉት ቡድኖች የተቋቋሙት በ1930 ዓ.ም ነበር፡፡ የተመሰረቱት ጣሊያን በገባ በሁለት አመቱ ማለት ነው። 6 ኪሎ የሚባለው ቡድን ነው። ይህ ቡድን ጣሊያኖች ለዘዴ ያቋቋሙት ቡድን ነው፤ የተቋቋመበት ዓላማ እኛን ለማፍረስ ነበር፡፡ ያኔ ስማችንንም አስቀይረውን ነበር። ይህ ቡድን የእኛ ፀር ነበር። የሚረዳቸው እዚያው 6 ኪሎ ያለው «ኩኛክ አሎቮ» የተባለው ፋብሪካ ነው። ማሊያ እና ሸራ ጫማ ተገዝቶላቸው ነበር። ቼንኮ ማጄ ይበላሉ። ግንቦት 5 ማለት ነው፡፡ በዚህ ስም የሚጠሩት ጣሊያንም የገባው በዚሁ ቀን ስለሆነ ነው።


እነሱ ጠግበው ሲመጡ እኛ ቆላችንን ቆርጥመን እንመጣለን። ያኔ እናሸንፋቸዋለን፤ እንደለመዱት ይደበድቡናል። ይረግጡናል። 6 ኪሎና ጊዮርጊስ ሲጫወቱ በሰላም አልቆ አያውቅም። ሁሌ ይናደዱብናል። እኛ ሕዝብ ይደግፈናል፡፡ ጥሩ እንጫወታለን፡፡ ከውጭ ሀገር ኮሚኒቲዮች ሆነ ከራሳቸው ከጣሊያኖች ጋር ስንጫወት ስለምናሸንፋቸው የተከበርን ነን፡፡ ህዝቡም ጥላቻውን የሚወጣው በእኛ ነበር። ያሸነፍናቸው ቀን ዱላቸውን ይጀምራሉ። እንደውም ግጥም ነበረው።

«ይጫወቱ ነበር በቴስታ በጋንባ፣
መገን 6 ኪሎ ተሸንፎ ገባ፡፡»
እያልን እንጨፈር ነበር። ጋምባ ማለት እግር ማለት ነው። ሌላም እንጨምር፡፡
«ግጥም አይነቃነቅም የብረት ዲጂኖ፣
እንዴት ነህ አየለ የአራዳ ተርሲኖ።»
ሌላ ደግሞ ኤልያስ የሚባል በኃላ አውሮፕላን አብራሪ የሆነ ጎበዝ ተጨዋች ነበረን፡፡ ህዝቡም የእርሱን እና የይድነቃቸውን ጥምረት እያየ እንደዚህ እያለ ይገጥም ነበር፡፡
«በሰማይ ኤልያስ በምድር ይድነቃቸው፣
ለመታሰቢያነት እግዜር ፈጠራቸው።»
ይባል ነበር።


ጣልያኖች የህዝቡ ሁኔታ እያሰጋቸው መጣ፡፡ ሁሉም ለትግል ወደ ጫካ መግባት ሆነ ስራው። ከዚያ አንድ ዘዴ ፈጠረ፡፡ የአገዛዙን ጥሩነት ለማሳየት የእኛን ክለብ እንደመቀስቀሻ ለመጠቀም ሞከረ። ጊዮርጊስ በህዝቡ ውስጥ ያለውን ቦታ ያውቁታል። ብዙ ህዝብ ይከተለን ነበር፡፡ ህዝቡም እኛን ከለላ አድረጎ ስለ አርበኝነቱ እና ስለ ጫካ ትግሉ ይንሾካሾክ ነበረ።


አንድ ቀን ጣሊያን «ህዝቡ ሰላም ነው፤ ኑና ተመልከቱት» ብሎ ወደ ራስ አበበ አረጋይ መልዕክት ይልካል። ጎን ለጎንም በጃንሜዳ ልዩ ጨዋታ ያዘጋጃል። ድንኳን ተተክሎ ለህዝቡ መቀመጫ ተደርጎ አርበኞቹ ተጠሩ። ራስ አበበም ጣሊያን አይታመንም ብለው አንድ ጣሊያናዊ ጄኔራል በመያዣነት ተረክበው ደጃች ደምሴ ወ/ሚካኤልን ሁኔታውን እንዲከታተሉ ይሉካቸዋል። ጣሊያንም የእኛን ክለብ አስጠርቶ ጨዋታውን በሰላም እንድንጨርስ ማሳሰቢያ ይሰጣል፡፡ 


ከዚያም ጣሊያን ከመሰረታቸው ቡድኖች 6 ኪሎ ተመርጦ ከእኛ ጋር እንዲጫወት ይደረጋል። ጨዋታው ብዙ አልቀጠለም፤ ወዲያው እነርሱ ፀብ አስነሱ፡፡ እኛም ሁኔታውን ህዝቡ እንዲያውቀው ተያያዝን፡፡ ህዝቡም ከኳሱ ይልቅ ፀቡ ስላስደሰተው በማጨብጨብና በመሳቅ በፀቡ እንድንገፋበት ይገፋፋን ነበር። ጨዋታው ሳያልቅ ተቋረጠ።

በጣሊያን ጊዜ ከትንሹ ጀምሮ ቤተመንግስት ሁሉም የጊዮርጊስ ደጋፊ ነበር። ዮፍታሄ ንጉሴ ቀንደኛ የክለባችን ደጋፊ እና አስተማሪያችን ነበር። ጠላት በገባ ጊዜ ወደ ሱዳን ተሰዶ ነበር። «አፋጀሽኝ» የተባለው ድራማ ሲሰራ በዚያ ቴአትር ላይ 3 የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ተሳትፈን ነበር። ንጉሱ ሀገር ከመግባታቸው በፊት አርበኞች ትግሉን በየጫካው አጧጥፈውት ነበር። እኛ የጊዮርጊስ ተጨዋቾች ደግሞ በየቡና ቤቱ ጓሮ እየገባን የሚጠጣውን ሰው እንሰብክ ነበር። «ለነፃነትህ ታገል፤ ጊዜው ተቃርቧል። ባንዲራህን አስመልስ» እያልን ህዝቡን እንቀሰቅስ ነበር። አርበኞች ትግሉን እያጧጧፉ እንደሆነ እየተሽሎኮሎክን በየቡና ቤቱ ብዙ ኢትዮጲያውያንን መስበክ ጀምረን ነበር። በኃላ ሁሉም በትግሉ ገባበት።

በመጨረሻ ንጉሱ ወደ ሀገር ሲገቡ በዮፍታዬ ንጉሴ ተደርሶ በካፒቴን ናልባዲን የተቀናበረውን የኢትዮጲያን ህዝብ መዝሙር «ኢትዮጲያ ሆይ ደስ ይበልሽ» የሚለውን መዝሙር ጃንሆይ ፊት ሄደን የዘመርነው እኛ ነበርን።»


Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ