የፈረሰኞቹ ገጽ ‏- ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!

መውጣትና መውረድ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ካልከሸፉ እውነታዎች ውስጥ አንዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ ሆኖ አልቀረም። «ነበር» በሚባል ቃል ያላበቃ ክለብ ነው። ከዘመናት በፊት፣ ከዘመናት በኋላ፣ ትላንትም ሆነ ዛሬ ባሰመረው መስመር እየተጓዘ የሚገኘው የእኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው። ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኋላ ተመስርተው ያልፀኑ፣ በተሻለ ዘመን ተነስተው በእግራቸው ያልቆሙ ክለቦች እልፍ ናቸው።

ዘመናቸውን የቀደሙ፣ ነገን ቀድመው በተረዱ ወጣቶች አራዳ ላይ በአራዳዎች የተመሰረተ ክለብ አለን። እግር ኳስ በኢትዮጵያ እንግዳ በነበረበት ጊዜ ከሜዳ ሜዳ አንግል እየተሸከምን፣ በኖራ መስመር ሰርተን፣ ሹራብ እንደ ማልያ ለብሰን፣ ተጨዋቾችን ለማስፈረሚያ ቆሎን እንደ ክፍያ ሰጥተን የኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክን ጠፍጥፈን የሰራን እኛ ነን።

ከኪሳችን ገንዘብ እያዋጣን የእግር ኳስን «ሀ፣ ሁ» ያስተማርን ቀዳሚዎች እኛ ነን። ነጭና ጥቁር በቀለማቸው ብቻ በተቦደኑት በዚያ ጊዜ የማይሞከረውን እንዲሆን በማድረግ በሰብአዊነት የቆምን እኛ ነን። እግር ኳስን ለሀገራዊ ነፃነት እንቅስቃሴ በማዋል ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ቀድመን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማን በአዲስ አበባ አውለብልበን ነፃነታችንን ያረጋገጥን እኛ ነን።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለ14 ጊዜ ዋንጫ ወስደናል። ውድድሩ እንደ አዲስ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለብቻችን በፍፁም የበላይነት የከበርን እኛ ብቻ ነን። ሀገራችንን በተደጋጋሚ በአፍሪካ መድረክ በመወከል ስማችንን በጉልህ የፃፍን፣ ለአራት ተከታታይ አመታት ማንንም ጣልቃ ሳናስገባ የሊጉን ዋንጫ ያነሳን እኛ ብቻ ነን። በሊጉ ውድድር ያለምንም ሽንፈት ዋንጫ አንስተን የማይቻለውን ችለን ያሳየን እኛ ብቻ ነን። የአዲስ አበባ ስታዲየምን ከአሰልቺ ጭፈራ አውጥተን በሞዛይክ ጥበብ ያስጌጥን፣ ጥበብን በፍቅር አስተምረን የብዙዎችን ልብ የማረክን እኛ ብቻ ነን።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪክ፣ ጉዞ እና ድል የዋሆች በሚሰጡት ተቀጥያ የሚንቋሸሽ አይደለም፡፡ ስም በመለጠፍ የሚያንስ አይደለም፡፡ ለማጉደል ስለተሯሯጡ የሚጎድል አይደለም። ከ80 ዓመታት በላይ በታላቅ ስፖርታዊ ትግል የገነባነው ታሪክ በየዋሆች የሃሰት ምላስ የሚጠፋ አይደለም፡፡ ታሪክ በምላስ እንደማይሰራ ሁሉ በምላስ አይጠፋም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ድሎች ቀን የጎደለባቸው ስላሳነሱት የሚያንስ አይደለም፡፡ ስም ስለለጠፉበት የሚዋረድ አይደለም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ እግርኳስ መምህር የሆነ ክለብ ነው። ክሽፈት በተጠናወተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የክለቦች ታሪክ ያልከሸፈው የእኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ዛሬ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደርጋል።

Comments

Popular posts from this blog

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ምስረታ እና ጉዞ!