የፈረሰኞቹ ገጽ - ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!

«የሚገጥሙት ይፈሩታል፣
ዝና ሰምተው ያከብሩታል፤
ጀግንነቱን ያምኑለታል፣
ከዚህ በላይ ደስታ የታል?»

ዘንድሮም በታላቁ የአፍሪካ እግር ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ እየወከልን ያለነው እኛ ነን፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጎ ይዞ የተገኘነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ የክለባችንን አርማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጋር አጣምረው ይዘው የመገኘት ብቃቱን ያገኙት ፈረሰኞቹ ናቸው፡፡ ከምስረታው አንስቶ ከኢትዮጵያ ጎን ያልተለየ፣ በኢትዮጵያ የመከራ ጊዜም ሆነ የድል ጊዜ ከጎን የተገኘው የእኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡

እንሆ ረቡዕ ሆነ። በሁሉም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ልብ ውስጥ ሲናፈቅ የከረመው ቀን ደረሰ። ቁልቁል ቀን ሲቆጠርለት የነበረው የጨዋታ ቀን ተገኘ። የሚነጋ የማይመስሉ ለሊቶች፣ የማያልቅ የሚመስሉ ቀናቶች አልፈው፣ የማክሰኞ ረጅም ለሊት ተጠናቆ የጨዋታ ቀን ላይ ተገኘን።

በእንዲህ አይነት ቀን ህፃናት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቀለማት ይዋባሉ። የወጣቶቹ ልብ ቅዱስ ጊዮርጊስን በአፍሪካ አህጉር ታላቅ የማድረግ ህልማቸውን ይዘው ካልተኙበት መኝታቸው ላይ ይነሳሉ። የቅዱስ ጊዮርጊስ የታሪክ መዝገብ የሆኑት አረጋውያን በ "V" ምልክት የደመቀውን ኮፍያቸውን አደርገው በማለዳ ጉዟቸውን ወደ ካምቦሎጆ ያደርጋሉ። እስካርፓቸውን በአንገታቸው፣ አርማቸውን በእጃቸው ይዘው ከቤት ይወጣሉ። ለሁላችንም ቀኑን በጉጉት ለጠበቅን፣ ይህንን ቀን ለናፈቅን ሁሉ ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!!!

ዛሬ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ የሚነግስበት ቀን ነው። በአፍሪካ ታላቁ የውድድር መድረክ ላይ የሚታይበት ዕለት ነው። ዛሬ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው። በመላው የስታዲየሙ ክፍሎች የሻምፒዮኖቹ ደጀኖች ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታላቅነቱ ያዜማሉ። የዛሬ ዝማሪያችን የክብር ቦታችን ላይ ስለመንገስ ነው። በአፍሪካ ታላቁ የውድድር መድረክ ላይ ስማችንን ማስመዝገብ ነው። የኛ ሩጫ ከትላንትናው የጊዮርጊስ ታሪክ ጋር ነው። ፉክክራችን ከራሳችን ጋር ብቻ ነው።

አላማችን «የለም ሌላ» ብለን ለምንዘምርለት ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚነገር ታሪክ እና የሚፃፍ ማንነት በእግርኳስ ታሪክ ማስመዝገብ ነው። ህልማችን ረጅም ነው። ትግላችን ግልፅ ነው። የምንወዳት ሀገራችንን እና ክለባችንን በአፍሪካ የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ማንገስ ነው።

ጊዮርጊስ ባለበት የአሸናፊነት ታሪክ አለ። ጊዮርጊስ ባለበት ድል አድራጊነት አለ። ለኢትዮጵያውያን ክለቦች እንደ ተራራ የገዘፈውን ክብር ቅዱስ ጊዮርጊስ አሳክቷል። ለዚህም ክብርና ታላቅነት ስንል ዛሬ የሚቀር አንድም ጉልበት የለንም። የሚሰሰት አቅምም አይኖረንም። ቅዱስ ጊዮርጊስ የመላው ኢትዮጵያውያን ውበት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ የትውልድ አደራችን ነው። ሲሞቀን የምናወልቀው፣ ሲበርደን የምንደርበው አይደለም። የሁልጊዜም የክብር ልብሳችን ነው። ክለባችን ልዩ የሚያደርገን ጌጣችን ነው።

የካፍ ሻምፒየንስ ሊግ ትክክለኛ የውድድር መድረካችን ነው። ቦታችን ከፍ ያለ ነው። አፍሪካ በነጮች ስር እያለች ጥቁርነትን ከሰውነት በታች ለተመለከቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥቁርነት ቀለም እንጂ ልዩነት እንዳልሆነ ያሳየ የነፃነት ቀንዲል ነው። ይህ አፍሪካውያን ያሉበት ውድድር ለእኛ ለቅዱስ ጊዮርጊሳውያን በልካችን የተሰፋ ነው፡፡ በማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ መውጣት ውስጥ ትምህርት የምንቀስምበት ውድድር ነው፡፡ ታላቋን ኢትዮጵያ በታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምንወክልበት ውድድር ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የ1ኛ ዙር ጨዋታውን ዛሬ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከዩጋንዳውን ኬሲሲኤ ጋር ያደርጋል።

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ