ጨዋነታችንን ዘመናት አይዋጁትም፤ ሁኔታዎች አይቀይሩትም!

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ ጋር ካደረገው ጨዋታ አንስቶ በተፈጠሩ ሁኔታዎች የተለያዩ አስተያየቶችን እየተመለከትን እንገኛለን፡፡ ከጋዜጠኞች፣ ከደጋፊዎች እና መሰል የእግርኳሱ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ አስተያቶች ሲሰነዘሩ ተመልክተናል፡፡ ለመደመጥ የሚበቁ፣ ለማድመጥ የሞከርናቸው እና ለአቅመ መደመጥ የማይበቁ የተለያዩ አስተያየቶችን ስናደምጥ ሰነበትን፡፡ እነዚህን ተንተርሰን የፈረሰኞቹ ገጽ አዘጋጆች የምናምንበትን ኃሳቦች ለመሰንዘር ተገደድን፡፡

በወቅቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ላይ የተነሳውን ተቃውሞና መሰል ድርጊቶች የፈረሰኞቹ ገጽ ተገቢ እንዳልሆነ እና ይህ በቀጣይ መደገም እንደሌለበት አንስተን ጽፈናል፡፡ እኛ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ይህንን ድርጊት ተንተርሰው መታረም ያለበትን ነጥብ መሆኑን በማንሳት የድርጊቱን ትክክል አለመሆን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ያለ ማንም ቀስቃሽ ድርጊቱን በይፋ አውግዘው ይቅርታ ሲጠይቁ ተመልክተናል፡፡ የተለያዩ መድረክ ያገኙም ደጋፊዎች ድርጊቱን አንስተው ተወያይተዋል፡፡


የፈረሰኞቹ ገጽ ትኩረትን የሳቡት በተለያዩ የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ይህንን ድርጊት ተንተርሶ እየተሰሩ ያሉ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሳይቀር ለግበአትነት መዋል የሚችሉ ፕሮግራሞች እንዳሉ መናገር ባንክድም ይህንን ድርጊት ተንተርሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የማጥላላት፣ ደጋፊውን የማሳነስ፣ ድጋፉን የማንቋሸሽ እና መሰል ስም ማጥፋቶች ሲሰነዘሩ የተመለከትናቸው የቴሌቪዥንም ሆነ የራዲዮ ፕሮግራሞች አሉ፡፡

ወቀሳ ጥሩ ነው፡፡ ትችት መልካም ነው፡፡ ሆኖም ወቀሳም ሆነ ትችት ዕውቀት ሊላበሱ እና ለተወቃሹ አካል መማሪያ ነጥብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ትችት ጥላቻን ሊላበስ አይገባም፡፡ ለመተቸት ሲባል ብቻ የቀደመውን የድጋፍ ጉዞ እና ያለውን የተሳካ ሂደት ጭቃ መቀባት ሙያዊ ስነ ምግባር አይደለም፡፡

የፈረሰኞቹ ገጽ ባዳመጣቸው ውስን ሊባሉ በማይችሉ የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የቀረበው ዘገባ ጤነኝነት ይጎድላቸዋል፡፡ ዘለፋ እና ስም ማጥፋት ተደባልቀው ሰምተናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብም ሆነ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የድጋፍ ታሪክ የተጀመረው የአዳማ ከነማ ጨዋታ ላይ ያስመስላሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ሰላማዊነት፣ ጨዋነት እና ለስፖርት ህጎች ያላቸውን ተገዢነት ከአዕምሯቸው ደምስሰዋል፡፡ ይህ እኛን ብቻ ሳይሆን በርካታ ደጋፊዎችን የሚያሳዝን ድርጊት ነው፡፡ ይህ ለዘመናት የምንታወቅበትን ጨዋነት እና ሰላማዊ የድጋፍ ድባብ ጭቃ ለመቀባት የሚሞከር የተለመደ አባዜ ነው፡፡



- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የአገር ውስጥ ደጋፊዎችንም ሆነ አህጉር አቀፍ የሚዲያ ባለሙያዎችን እንዲሁም ክለቦችን አፍ ያስከፈተ ድጋፍ ያሳዩ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ «ኢትዮጵያውያን የእግርኳስ ደጋፊዎች» ተብሎ ስማችን እንዲጠቀስ ያስቻሉ ደጋፊዎች ናቸው፡፡


- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የአዲስ አበባ ስታዲየም አይቶ የማያውቀው የድጋፍ ዘይቤ በማምጣት የአዲስ አበባ ስታዲየምን ከአሰልቺነት ያላቀቁ ናቸው፡፡

- እኚህ ደጋፊዎች የተቃራኒ ክለብ ደጋፊዎችን ሳይቀር የድጋፍ «ሀ…ሁ» አስተምረዋል፡፡ ድጋፍ ምን እንደሆነ፣ ዝማሬ ምን አይነት ቀለም እንዳለው እና የእግርኳስ ድጋፍ በዕውቀት መቃኘት እንዳለበት በተግባር አሳይተዋል፡፡

- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ስታዲየም እንዴት በቀለማት እንደሚደምቅ እንዲሁም የሞዛይክ ትርዒት ምንነትን ለአገራችን ደጋፊዎች ያስተማሩ ናቸው፡፡
- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ክለባቸው ተሸንፎ የተቃራኒ ክለብ ደጋፊዎች ድምጻቸው እንዳይሰማ በማድረግ እና ከክለባቸው ጎን በመገኘት ድጋፋቸውን መቸር የሚያውቁ ናቸው፡፡

- የክለባችን ደጋፊዎች ረጅም ርቀትን ተጉዘው እንዲሁም ክለባቸውን አበረታተው ውጤት ቢጠፋ እንኳ ከክለባቸው ጎን መገኘት ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ «ብትሸነፉም አቻ ብትወጡም፣ የእኛን ድገፋ መቼም አታጡም» ብለው በመዘመር ተጨዋቾቻቸውን ለቀጣይ ድል ማነሳሳት እንዴት እንደሚችሉ የሚያስቡ ናቸው፡፡

የፈረሰኞቹ ገጽ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የደረጉት መልካም ተግባር እንደ ውለታ ተቆጥሮ ስህተታችን ሊዘገብ አይገባውም የሚል ዕምነት የለውም፡፡ ሆኖም ስህተታችን እና ድክመታችን ሲዘገብ ያለውን ነባራዊ እውነታ ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡ የክለቡን የድጋፍ ታሪክ ሊያዛባ አይገባውም፡፡ የደጋፊዎችን ልፋት እና ጥረት ጭቃ ለመቀባት መንደፋደፍ አይገባም፡፡ በአንድ ቀን ድርጊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሊመዘኑም ሆነ ሊፈረጁ አይገባም ብለን እናምናለን፡፡

በአንድ ቀን ስህተት የክለቡን የድጋፍ ታሪክ ለማዛባት መሯሯጥ ስህተት ነው፡፡ የሚሰነዘሩት ትችቶች እና ወቀሳዎች የክለቡን ደጋፊዎች የሚያስተምሩ፣ ለቀጣይ ጨዋታዎች ትምህርት የሚሰጡን፣ ከስህተታችን ተምረን የበለጠ ተጠናክረን እንድንመጣ የሚያስችል መሆን አለባቸው ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ 82 ዓመታትን በጥፍራቸው እየቧጨሩ፣ በጉልበታቸው እየዳኹ፣ እየወደቁ እና እየተነሱ የተጓዙ ደጋፊዎች የተሰባሰቡበት ክለብ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ዓመታት ክለቡ እልፍ ደጋፊዎችን ከጀርባው አሰልፎ የተጓዘ ክለብ ነው፡፡ የእግር ኳስ ክለብን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የእግርኳስ ድጋፍን በአገራችን የቆረቆረቆሩት እኚህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ይህንን ታሪክ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ቀን ፍረጃ እና ድምዳሜ እግርኳሱን ቅጥ ያሳጣዋል፡፡ ስሜታዊነትን ከጋዜጠኝነት ሙያ ጎን ልታርቁ ይገባል እያልን ነው፡፡
ሆኖም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ላይ ልክ እንደ ስኬት ሁሉ ጉድለት እንዳለብን እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ባሳለፍነው ጨዋታ የተከሰተውም ይህ ነው፡፡ ከጉድለቶቻችን አንዱ ነው፡፡ ይህ በእግርኳስ አለም ሲከሰት የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው አይደለም፡፡ ይህ ጉድለት ለክለባችን ስምም ሆነ የድጋፍ ታሪካችን ተገቢ እንዳልሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም ይህንን ተረድተው ይህንን ተግባር ለመቅረፍ እየሰሩ ነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አመራሮችም እና ደጋፊዎችም ተቀራርበው ለመነጋገር እና በዚህ ዙሪያ ያለውን ክፍተት ለማረም ሊነጋገሩ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
                                      

ጨዋነት መለያችን ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሳዊነት ጨዋነት መሆኑን ምስክሮቻችን እልፎች ናቸው፡፡ ሰላማዊ ድጋፍን አንግበን ዘመናትን ተሻግረናል፡፡ ጨዋነታችንን ዘመናት አይዋጁትም፤ ሁኔታዎች አይቀይሩትም፡፡ ትላንት የተከሰተው ሁኔታ ቅዱስ ጊዮርጊስን አይገልጽም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች መገለጫም አይደለም፡፡ እግርኳስ ስሜታዊ ከሚያደርጉ ስፖርቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በዚህም የማይፈቀዱ እና ከስፖርት ህጎች ያፈነገጡ ድርጊቶች ይከሰታሉ፡፡ ይህ በጉዟችን ውስጥ ያጋጠመን እንቅፋት ነው፡፡ ይህንን ለማረም ጊዜያትን አናጠፋም፡፡ ስህተታችንን ለማረም ፈጥነን እንጓዛለን፡፡ ነገም በምንታወቅበት ያማረ እና ሰላማዊ የድጋፍ ዘይቤ ደምቀን እንገኛለን፡፡


ምንጊዜም ጊዮርጊስ!!!
                                        


Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ