የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ


ቅዱስ ጊዮርጊስ የ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል፡፡ ይህንን ጨዋታ የሚያደርገው ከአዳማ ከነማ ጋር ሲሆን ጨዋታው ነገ (ሐሙስ) በ11 ሰዓት ይካሄዳል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከነማ የ2009 ዓ.ም የእርስ በእርስ ግንኙነት!

በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት እሁድ ታህሳስ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር። ይህ ጨዋታ የ2009 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ የ5ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ሆኖ የተከናወነ ሲሆን ጨዋታው የተካሄደው ምሽት 11፡30 ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ ጨዋታ ብዙም የሚነሳ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳይካሄደበት 0-0 በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ጨዋታ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በጨዋታው በጥልቅ መከላከል የቀረቡት አዳማ ከነማዎች ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ተወጥተው ጨዋታውን ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ ፈረሰኞቹ በጥልቀት የሚከላከሉ የአዳማ ከነማ ተከላካዮችን አልፈው ጎል ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታውን በአቻ ውጤት ፈጽመዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች የ2ኛ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት ረቡዕ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ የተካሄደው በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲሆን ጨዋታው ጅማሬውን ያደረገው ከቀኑ 9 ሰዓት ሲል ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተዳክሞ የቀረበበት እና አዳማዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰው ጨዋታውን 1-0 ያሸነፉበት ጨዋታ እንደሆነ ይታወሳል፡፡

ጨዋታው በዝናብ ታጅቦ የተካሄደ ጨዋታ ነበር፡፡ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በስታዲየሙ የጣለው ዝናብ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ሚዛን ወደ አዳማ ከነማ እንዲያጋድል አድርጎ ነበር፡፡ መጠነኛ ድካም ይታይባቸው የነበሩት ፈረሰኞቹ ከዝናቡ ጋር ተዳምሮ ሙሉ በሙሉ በጨዋታው ላይ ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር፡፡ አዳማ ከነማዎች በረዣዥም ኳሶች በመታገዝ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡ ፈረሰኞቹ በዚህ ጨዋታ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ አጠናቀዋል፡፡

በጨዋታው 79ኛ ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ረዥም ኳስ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች ዳዋ ሁጤሳ በግንባር በመግጨት አዳማ ከነማን አሸናፊ የሚያደርግ ጎል አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላማ አዳማዎች ብልጫ ወስደው ጨዋታውን በአዳማ ከነማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 12 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 5 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ፣ 6 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሞ በ1 ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ አዳማ ከነማ ካከናወናቸው 14 ጨዋታዎች መካከል 5 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት፣ 7 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በ2 ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ከቅዱስ ጊዮርጊስ የ2 ጨዋታ ብልጫ የያዙት አዳማ ከነማዎችን 22 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ነጥቦችን በመያዝ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

አዳማ ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥመው ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በመሆኑ አስቀድመን አዳማ ከነማ ከሜዳ ውጪ ያለውን ውጤት እንመልከት፡፡

አዳማ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ 7 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 7 ጨዋታዎች ላይ በ2 ጨዋታዎች ላይ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ በ3 ጨዋታዎች አቻ ወጥተው በ2 ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡ አዳማ ከነማ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ወላይታ ድቻን እና ኢትዮ. ኤሌክትሪክን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ወደ ወላይታ ሶዶ ተጉዘው ወላይታ ድቻን 2-1 እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም አቅንተው ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-2 ማመሸነፈቻው ይታወሳል፡፡

ከሜዳቸው ውጪ ተጉዘው 3 ጨዋታዎችን ኣቻ የተለያዩት አዳማ ከነማዎች የአቻ ውጤታቸውን ያስመዘገቡት ከሚከተሉት ክለቦች ጋር ነው፡፡ መከላከያ፣ ድሬዳዋ ከነማ እና መቐለ ከነማ አቻ የወጣቸው ክለቦች ናቸው፡፡ ከመከላካያ እና ከድሬዳዋ ከነማ በተመሳሳይ 0-0 እንዲሁም ከመቐለ ከነማ 1-1 የአቻ ውጤቶቹ ናቸው፡፡

ይህ ክለብ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ሽንፈትን ያስተናገደው በ2 ጨዋታዎች ሲሆን አዳማ ከነማዎችን ጋብዘው ድል ያደረጓቸው ክለቦች ወልዲያ እና አርባምንጭ ከነማ ናቸው፡፡ ወልዲያ 2-0 እና አርባምንጭ ከነማ 1-0 አዳማ ከነማን በሜዳቸው ጋብዘው የረቱ ክለቦች ናቸው፡፡

አዳማ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ለፕሪሚየር ሊጉ ውድድር 2 ጊዜ መምጣት ችሏል፡፡ አንደኛውን ጨዋታ ከመከላከያ ሌላውን ከኢትዮ. ኤሌክትሪክ ጋር አድርጓል፡፡ በዚህም አንድም ጊዜ ሽንፈትን አላስተናገደም፡፡ ከመከላከያ ጋር አቻ ሲለያይ ኢትዮ. ኤሌክትሪክን 3-2 ማሸነፉን ከላይ አንስተናል፡፡ በአጠቃላይ አዳማ ከነማ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 6 ጎል ማስቆጠር ሲችል 7 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው አዳማ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው ያደረገው 7 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ነው፡፡ በደጋፊያቸው እና በሜዳቸው ማድረግ ከቻሉት 7 ጨዋታዎች መካከል በ3 ጨዋታ ላይ ድል ሲቀናቸው በ4 ጨዋታ አቻ ተለያተዋል፡፡ አዳማ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው ሽንፈትን ያላስተናገደ ክለብ ነው፡፡ ይህ ክለብ በሜዳው ካከናወናቸው ጨዋታዎች ሃዋሳ ከነማን፣ ኢትዮጵያ ቡናን እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሃዋሳ ከነማን 1-0፣ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 3-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

አዳማ ከነማ በሜዳው እና በደጋፊው አቻ የተለያው ከደደቢት 0-0፣ ከፋሲል ከነማ 0-0 እና ከጅማ አባ ጅፋር 1-1 መሆኑ ይታወሳል፡፡ አዳማ ከነማ በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 8 ጎልችን ሲያስቆጥር 3 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 15 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ጎሎቹን አስተናግዷል፡፡ አዳማ ከነማ በበኩሉ በ14 ጨዋታዎች 14 ጎሎችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካይ በጨዋታ 1.25 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ድሬዳዋ ከነማ በጨዋታ በአማካይ 1.00 ጎል እያስቆጠሩ ለዚህ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ በአማካይ 0.42 ጎሎችን ሲያስተናግድ አዳማ ከነማ በጨዋታ በአማካይ 0.71 ጎል አስተናግዷል፡፡

የአዳማ ከነማ የጨዋታ አቀራረብ!

በአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ የሚመራው አዳማ ከነማ ከፍ ዝቅ እያለ ለዚህ ጨዋታ ደርሷል፡፡ ቡድኑ ወጥ አቋም ማሳየት ያልቻለ ሲሆን ብቃቱም ከሳምንት ሳምንት የተለያየ ነው፡፡ ይህ ስብስብ ባለፉት ቅርብ ሳምንታቶች ውስጥ 4-4-2 የጨዋታ ፎርሜሽንን እየተገበረ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ክለቡ 1-1 ሲለያይ የተጠቀማቸው ተጨዋቾች እነኚህ ናቸው፡፡

ግብ ጠባቂ፡- ጃኮ ፔንዜ
ተከላካዮች፡- ምኞት ደበበ፣ ተስፋዬ በቀለ፣ ሱሌማን መሃመድ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ
አማካዮች፡- እስማኤል ሳንጋሪ፣ በረከት ደስታ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ሲሳይ ቶሊ
አጥቂዎች፡- ዳዋ ሆጤሳ፣ ቡልቻ ሹራ

አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ልክ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ በተጨዋቾች ጉዳት የተጠቃ ክለብን እየመሩ የሚገኙ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከላይ በተቀመጠው አሰላለፍ ላይ የቡድኑ ቀዳሚ ተከላካይ ሙጂብ ቃሲም ጉዳት ላይ በመሆኑ የግራ መስመር ተከላካዩን ሱሌማን መሃመድ በመሃል ተከላካይነት ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በርካታ ተጨዋቾችን በጉዳት ምክንያት ሊያገኙ አለመቻላቸው በግልጽ ይታያል፡፡

አዳማ ከነማ በ4-4-2 ቀጥተኛ አጨዋወት ይቀርባል፡፡ ይህ ስብስብ ኳስን ተቆጣሮ ለመጫወት ቢሞክርም ሁነኛ የግብ ዕድል መነሻዎቹ ከመስመሮች እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ፈጣን ሽግግር የታገዘ ነው፡፡ በተለይም ሁለቱ የፊት አጥቂዎች ሜዳውን በማስፋት እና በሜዳው ቀኝ እና ግራ ወደ መስመር ተጠግተው በመቆም ከቡድኑ የመስር ተከላካዮች በቀጥታ የሚደርሳቸውን ኳሶች ለመቀበል ያላቸው ዝግጁነት ማራኪ ነው፡፡

የአዳማ ከነማ የመስመር ተከላካዮች ከፊት አጥቂዎች ጋር ያላቸው የኳስ ግንኙነት በተደጋጋሚ በጨዋታ እንቅስቃሴዎች ላይ ይታያል፡፡ እነኚህ የመስመር ተከላካዮች ከአጥቂዎች ፊት ኳስ በመጣል እና ረጃጅም ኳሶችን በማሻገር ለዳዋ ሁጤሳ እና ቡልቻ ሹራ የሚያደርሷቸው ኳሶች ለአዳማ ከነማ ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ፈጠራ መነሻዎች ናቸው፡፡

አዳማ ከነማ ኳስ ይዞ ለመጫወት ሲሞክር በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ጫና በቀላሉ ኳስ የሚነጠቅ ስብስብ ነው፡፡ ለዚህም ወደ ሜዳ ይዘውት የሚገቡት የጨዋታ ዘይቤ ጫና ውስጥ እንደከተታቸው መመልከት ይቻላል፡፡ ከአማካዮች ርቀው የሚገኙት ሁለቱ አጥቂዎች እንዲሁም ተዘርዝረው የሚገኙት የአማካይ ክፍል ተጨዋቾች ኳስን መስርተው ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ለመግባት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ቡድኑ በመሃል ሜዳ ላይ በተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች በቁጥር ተበልጦ ይታያል፡፡ ይህም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድርባቸዋል፡፡ የተጋጣሚ የአማካይ እና የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጫና በመፍጠር ሲጫወቱ ከአዳማ ከነማ የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች በቀላሉ ኳስ መንጠቅ ሲሳካላቸው ተመልክተናል፡፡ ይህም አዳማ ከነማን ጫና ውስጥ ሲከተው ይታያል፡፡

አዳማ ከነማ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ስብስብ ነው፡፡ ቡድኑ አራቱን ተከላካዮች በአንጻራዊነት ለተከላካዮች አቅርቦ የሚጫወት ክለብ ነው፡፡ በመሆኑም በተከላከዮች እና በግብ ጠባቂው መካከል ያለው ጠባብ ክፍተት ቡድኑ በቀላሉ እንዳይጋለጥ ያደረገው ይመስላል፡፡ ቡድኑ በጉዳት ምክንያት ወሳኝ ተከላካዮቹን እና ግብ ጠባቂውን ባጣበት ወቅት እንኳ በቀላሉ ግብ የሚያስተናግድ የተከላካይ ክፍል የለውም፡፡ በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ ከ4ቱ የተከላካይ ክፍል ተጨዋቾች መካከል በጉዳት ምክንያት ተጨዋቾቹን እየቀየረ ቢገባም ቡድኑ ጠንካራ ሊባል የሚችል የተከላካይ ክፍል እንዳለው ተመልክተናል፡፡

በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት የማይሰለፉ ተጨዋቾች!

ከጉዳት ጋር ተያይዞ ናትናኤል ዘለቀ እና አስቻለው ታመነ የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም፡፡ ከእነዚህ ከጠቀስናቸው ተጨዋቾች ውጪ ሁሉም ፈረሰኞች ከቡድኑ ጋር ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ሳላሃዲን ሰኢድ እና ታደለ መንገሻ ከጉዳት ተመልሰው ከቡድኑ ጋር ጠንካራ ልምምድ እያደረጉ ቢገኙም አሰልጣኞቹ የዚህ ጨዋታ አካል ያደርጓቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከዚህ ውጪ ባለፉት ጨዋታዎች በጉዳት ከጨዋታ የራቁት ተጨዋቾች የዚህ ጨዋታ አካል ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው፡፡

እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ