«የክለባችን ኃላፊዎች በጣም ጎድተውናል፤ በህይወታችን አንዴ ሊገጥመን የሚችል ጥሩ ዕድል አምልጦናል፡፡» የአል ሰላም ዋኡ ተጨዋቾች



በ22ኛው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ መርኃ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አል ሰላም ዋኡ በትላንትናው ዕለት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ባለመገኘቱ ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ በፎርፌ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ መቻሉ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ይህ ሲሆን የአል ሰላም ዋኡ ክለብ ተጨዋቾች ስሜታቸው ምንድን ነው
? ሂደቱን እንዴት ተከታተሉት እና መሰል ጉዳዮችን ለማጣራት ሞከርን፡፡ ከተወሰኑ ተጨዋቾች ጋር ስለሆነው ነገር ስናወራ ከድልድሉ መሰማት አንስቶ ያለውን ነገር አጫወቱን፡፡ ድልድል እንደተሰማ የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ተጨዋቾች ደስተኛ እንደሆኑ ነገሩን፡፡ ምክንያታቸውንም እንዲህ ሲሉ ለፈረሰኞቹ ገጽ አጫወቱን፡፡

«ቅዱስ ጊዮርጊስ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ስማቸው ገኖ ከሚታወቅ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ከአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች ጋር ተጫውቶ ያመጣውን ውጤት እናውቃለን፡፡ ከዚህ ክለብ ጋር መጫወት ለእኛ ታላቅ ዕድል ነበር፡፡ ይህ ክለብ ከአገር ውስጥ ተጨዋቾች በተጨማሪ ከአፍሪካ የተለያዩ አገራቶች ተጨዋቾችን እንደሚያስፈርም እናውቃለን፡፡ ይህም ለእኛ መልካም ዕድል ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን ሊግ ደካማ ነው፡፡ በዚያ ላይ አገሪቱ ውስጥ ያለው የእርስ በእርስ ግጭት እግር ኳሱ ላይ ጥላውን በግልጽ እያጠላ ይገኛል፡፡ ይህም ለእኛ ለተጨዋቾች በጣም አስቸጋሪ አድርጎብናል፡፡ »


የፈረሰኞቹ ገጽ የጨዋታው ቀን ከተቃረበ አንስቶ እንዲሁም የእንግዳው ቡድን ከመምጣት እና መቅረት ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ መረጃዎች ሲወጡ ከአል ሰላም ዋኡ ክለብ አባላት መካከል ከተወሰኑት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ መረጃ ይለዋወጥ ነበር፡፡ በዚህም የአል ሰላም ዋኡ ክለብ ተጨዋቾች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለመጫወት ያላቸውን ጉጉት ለመረዳት ችለናል፡፡ የክለቡ ተጨዋቾች እስከ መጨረሻ ሰዓት ድረስ ጉዞ እንዳለ ተስፋ በማድረግ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ የጠበቁት ጨዋታ እንዳልተሳካ ሲያውቁ የተሰማቸውን ስሜት ለፈረሰኞቹ ገጽ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

«የክለባችን ኃላፊዎች በጣም ጎድተውናል፤ በህይወታችን አንዴ ሊገጥመን የሚችል ጥሩ ዕድል አምልጦናል፡፡ ይህ ሁሉ ስህተት የተሰራው በክለባችን ኃላፊዎች ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን እንደሚፈልገው እናውቃለን፡፡ ሆኖም እኛ የፈለግነውን ያህል እንደማይሆን በእርግጠኝነት ልንናገር እንወዳለን፡፡ ጨዋታው ባለማካሄዱ በጣም አዝነናል፡፡ ይህ ዕድል እንዳያልፈን ፈልገን ነበር፡፡ የክለባችን ኃላፊዎች ይህንን ጨዋታ እንዲያስተካክሉ እና በጨዋታው ላይ እንድንካፈል በተደጋጋሚ ጠይቀን ነበር፡፡ እስከ መጨረሻ ሰዓት ድረስ ሁኔታዎችን እያስተካከሉ እንደሆኑ ነግረውን ስንጠባበቅ ነበር፡፡ ሆኖም አልተሳካም፡፡

ደጋፊዎች በስታዲየም ገብተው እና ከስታዲየም ውጪ ያለውን ድባብ በፎቶዎች እያየን ነበር፡፡ እነዚህን ፎቶ ስንመለከት የሚሰማን ስሜት ምን እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡ ከጨዋታው በፊት ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ስናስብ አብዛኞቻችን በጨዋታው ጥሩ ብቃት አሳይተን የቅዱስ ጊዮርጊስን ትኩረት ለማግኘት አስበን ነበር፡፡ ጎን ለጎን በሌሎች የአገሩቱ ክለቦች የመፈለግ ዕድል ያጋጥመናል ብለንም አስበን ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ኃሳባችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡»

አሁን ላይ የደቡብ ሱዳን የሊግ ውድድር አልጀመረም፡፡ የመልሱ ጨዋታ ጁባ ላይ እንዲደረግ በወጣው የመርኃ ግብር ቀንም ምንም አይነት ጨዋታ የለንም፡፡ በዚያ ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፈቃደኛ ሆኖ የወዳጅነት ጨዋታ ዕድል ቢሰጠን ደስተኞች ነን፡፡ እኛ ተጨዋቾች ይህንን በጣም እንፈልጋልን፡፡ የእናንተ ክለብ ይህንን ማድረግ ከቻለ ለእኛ ለተጨዋቾች በጣም አስደሳች ነው፡፡ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ እንዲያደርጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አል ሰላም ዋኡ በወጣላቸው መርኃ ግብር ቀን በወዳጅነት ጨዋታ መልክ ጁባ ላይ የመጫወቱ ዕድል ቢኖር ደስተኞች ነን፡፡»

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ