ትውስታ - በ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞ - ክፍል 3 (የመጨረሻ ክፍል)


የ2018 የቶታል ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የክለቦች ውድድር በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ይጀመራል፡፡ በዚህ ውድድር ለተከታታይ 4 አመታት ኢትዮጵያን በመወከል ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ይሳተፋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ በአፍሪካ ሻምዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ክለብ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ መጀመርን ተንተርሰን ያሳለፍነው ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞን እያነሳሳን እንገኛለን፡፡ ባለፉት ቀናት በክፍል አንድ እና ሁለት ምልከታችን ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2017 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ፣ የ1ኛ ዙር እና የምድቡ የመጀመሪያ 3 ጨዋታዎችን ማነሳሳታችን ይታወሳል፡፡ ለዛሬ በክፍል 3 እና በመጨረሻ ክፍል ያዘጋጀነው ጽሑፍ ይህንን ይመስላል፡፡

ኤኤስ ቪታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ይህ ጨዋታ የ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ 4ኛ ጨዋታ ሆኖ ተከናውኗል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከዚህ ጨዋታ ድረስ 9 ጎል አስቆጥሮ ምንም ጎል አላስተናገደም፡፡ የተጋጣሚዎቹን መረብ 9 ጊዜ ጎብኝቶ የራሱን መረብ በሚገባ ከጥቃት ጠብቆ ቆይቷል፡፡ ከታላላቆቹ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ጋር ጨዋታውን አድርጎ ጎሉን አላስደፈረም፡፡ በዚህም የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ በግልጽ ታይቷል፡፡ የመሃል ተከላካዮቹን አስቻለው ታመነን እና ሳላሃዲን በርጌቾን በምርጥ 11 የካፍ ስብስብ ውስጥ አስገብቷል፡፡
በሌላ በኩል አሰልጣኝ ማርት ኖይ ወደ ክለቡ እንደማይመለሱ እርግጥ ሆኗል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቦርድ አመራሮች ስብሰባ አድርገው ምክትል አስልጣኞቹ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሽንገታ ክለቡን ይዘው እንዲቀጥሉ ውሳኔ አሳለፉ፡፡ በዚህም ፈረሰኞቹ በምክትል አሰልጣኞቹ እየተመሩ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቀኑ፡፡

በሃይሉ አሰፋ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደ ጨዋታ መመለሱ የዚህ ጨዋታ መልካም ዜና ነበር፡፡ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ በ4-2-3-1 የጨዋታ አቀራረብ ፈረሰኞቹን እየመሩ ለጨዋታ አቀረቡ፡፡ አዳነ ግርማ እና ምንተስኖት አዳነ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀመጡ፡፡ ዘሪሁን ታደለ የግብ ጠባቂነቱን ቦታ ያዘ፡፡ ፍሬዘር ካሳ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሳላሃዲን በርጌቾ እና አበባው ቡጣቆ አራቱ ተከላካይ ሆነው ቀረቡ፡፡ ናትናኤል ዘለቀ እና ተስፋዬ አለባቸው የተከላከይ አማካይ ሚናን ያዙ፡፡ አብዱልከሪም ኒኪማ ብቸኛ የአጥቂ አማካይ ተጨዋች ሲሆን በግራ ፕሪንስ ሰቬርኒሆ በቀኝ በሃይሉ አሰፋ ተሰለፉ፡፡ ሳላሃዲን ሰኢድ ብቸኛ የፊት አጥቂ ተጨዋች ሆነ፡፡

ጨዋታው ተጀመረ፡፡ ፈረሰኞቹ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ኳስን በራሳቸው ሜዳ መቀባበል እና ኳስን መስርተው ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ሙከራ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ሆኖም 7ኛ ደቂቃ ላይ ቪታዎች መሃል ሜዳ አቅራቢያ ላይ የነጠቁትን ኳስ ይዘው ገብተው የመጀመሪያውን ጎል አስቆጠሩ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ መረብ ከ7 ጨዋታዎች በኋላ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ተደፈረ፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ ቪታዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ወሰዱ፡፡ ፈረሰኞቹ የሚታወቁበት ፈጣን ሽግግር ሜዳ ውስጥ መታየት አልቻለም፡፡

27ኛው ዲቂቃ ላይ ብዙም አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ የመሃል ዳኛው ለኤኤስ ቪታ የፍጹም ቅጣት ምት ሰጡ፡፡ ፍሬዘር ካሳ የቢጫ ካርድ ተመለከተ፡፡ ቪታዎች የተሰተውን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ጎልነት ቀይረው ጨዋታውን 2-0 መምራት ቀጠሉ፡፡ ፈረሰኞቹ የሚታወቁበት የመከላከል ዕቅድ እንደተለመደው አልሆን አለ፡፡ በተደጋጋሚ በቪታዎች ሲፈተኑ ተመለከትን፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በኤኤስ ቪታ 2-0 መሪነት ተጠናቀቀ፡፡

ከሁለተኛው አጋማሽ መጀመር አንስቶ 2 የተጨዋቾች ቅያሪ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተደረገ፡፡ አዳነ ግርማ በሃይሉ አሰፋን ቀይሮ ወደ ሜዳ ሲገባ፣ ምንተስኖት አዳነ ተስፋዬ አለባቸውን ለውጦ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ ፈረሰኞቹ ከተጨዋች ለውጥ በኋላ በጨዋታው ላይ ግልጽ ብልጫ ወሰዱ፡፡ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቻሉ፡፡ 65ኛው ዲቂቃ ላይ ሳላሃዲን ሰኢድ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ጎል ሆነ፡፡ ኤኤስ ቪታ 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ፡፡

ፈረሰኞቹ ደጋግመው የግብ ዕድል መፍጠር ተያያዙ፡፡ በሳላሃዲን ሰኢድ፣ አዳነ ግርማ፣ ፕሪንስ ሰቬርኒሆ፣ ምንተስኖት አዳነ እና ናትናኤል ዘለቀ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቻሉ፡፡፡ ሆኖም ጎል ማስቆጠር ባለመቻላቸው ጨዋታው በኤኤስ ቪታ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2017 የካፍ ሻምፒንስ ሊግ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናገደ፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ

ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ አሸናፊው ክለብ ወደ ሩብ ፍጻሜ ይሸጋገራል፡፡ ተሸናፊው ክለብ ሩጫውን ይገታል፡፡ ይህ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደመካሄዱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተስፋን ሰነቁ፡፡ ሰንዳውንስ በማሸነፍ ተጨማሪ ታሪክ የመስራት ተስፋን ሰነቁ፡፡ እንደተለመደው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾችም ሆነ ደጋፊዎች ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡

የጨዋታው ቀን ከማለዳው አንስቶ የስታዲየም ዙሪያዎች በረጃጅም ሰልፎች ተጥለቀለቁ፡፡ በረጃጅም ሰልፎች የስታዲየሙ አከባቢዎች ተዋጡ፡፡ ስታዲየም ለመግባት ወደ ስፍራው ካቀናው በርካታ ህዝብ መካከል ውስኑ ወደ ስታዲየም ገባ፡፡ ሌሎች ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ሰዎች ስታዲየም በመሙላቱ ጨዋታውን በሌሎች የቴሌቪዥን አማራጮች ለመመልከት ተንቀሳቀሱ፡፡

የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅዱሰ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ዝማሬ በ1 እግሩ ቆመ፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ድምጽ እርጅናው ከተገፈፈባቸው ቀናቶች አንዱ ሆነ፡፡ የሰንዳውንስ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የልዑካን ቡድን አባላት አዲስ አበባ ስታዲየም ሲደርሱ በተመለከቱት የድጋፍ መንገዶች ፈጽሞ ተገረሙ፡፡ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ጫኑ፡፡ በስታዲየሙ የሚያዩትን ድጋፍ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ማስቀረት ያላቸው አማራጭ ነውና ተጣደፉ፡፡ እርስ በእርስ በግርምት በመነጋገር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ድጋፍ እጃቸውን ሰጡ፡፡

የማሜሎዲ ሰንዳውንስ ዋና አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ ስለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሰጡትን አስተያየት ሶከር ኢትዮጵያ በወቅቱ የዘገበውን ወደዚህ ልናመጣው ወደድን፡፡

«በሟሟሟቅ ላይ እያለን ያየነው የደጋፊዎች ድባብ ልክ እንደቱሪስት ቆመን ያላቸውን ጥልቅ ስሜት አድንቀናል፡፡ (ፒትሶ በድባቡ ለደጋፊዎቹ ያለቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልፀዋል፡፡) ቆንጆ ነበር፡፡ ይህንን ድባብ ቡድኔ ቢኖረው ኖሮ ቡድኔ ሙሉ ለሙሉ ይለወጥ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር በጣም ቆንጆ ነገር ነው የተመለከትነው፡፡»
«ለአሰልጣኞች ቡድን አባላት ነግሪያቸዋለው፤ የዛሬው የደጋፊዎች ድባብ በተጫዋችነቴ በአውሮፓ ያየሁትን ነገር ነው ያስታወሰኝ፡፡ እንደዚህ አይነት ድባብ በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ዛማሌክን ስንገጥም 70 ሺህ ተመልካቾችን አይተናል፡፡ ይህን ነገር በደቡብ አፍሪካ አንመለከትም፡፡ ተመልሼ መጥቼ የምንጫወትበትን ጊዜ እንዲመጣ እመኛለው፡፡»

ጨዋታው ተጀመረ፡፡ የጨዋታው ኳስ ጀማሪዎች ሰንዳውንሶች ሆኑ፡፡ ፈረሰኞቹ ከጨዋታው መጀመር አንስቶ የጨዋታ ብልጫ ወሰዱ፡፡ በተደጋጋሚ የሰንዳውንሶችን የግብ ክልል ጎበኙ፡፡ 4ኛ ደቂቃ ላይ በሃይሉ አሰፋ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ የሰንዳውንስ ተከላካይ ለማውጣት ሲሞክር ተጨርፎ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጣ፡፡ 6ኛ ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጣ፡፡ 11ኛ ዲቂቃ ላይ አበባው ቡጣቆ የመታው የቅጣት ምት በግብ ጠባቂው ተመለሰ፡፡ ጨዋታው በዚህ መልክ ቀጠለ፡፡
የጨዋታው 4ኛ ዳኛ የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሽ ለመጠናቀቅ የቀረው 1 ዲቂቃ መሆኑን አሳየ፡፡ በዚህ ቅጽበት የሰንዳውንስ ተከላካይ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጁ በመንካቱ ፈረሰኞቹ የፍጹም ቅጣት ምት አገኙ፡፡ ስታዲየሙ በድጋሚ ጋለ፡፡ በመጠኑ መደብዘዝ የጀመረው ድባብ ተነቃቃ፡፡ ሳላሃዲን ሰኢድ የፍጹም ቅጣት ምቱን ለመምታት ኳሱን በእጁ ያዘ፡፡ የፍጹም ቅጣት ምት መምቻ ቦታ ላይ አስቀመጠ፡፡ ከኳሱ ብዙም ሳይንደረደር በግቡ በስተቀኝ በኩል ኳሱን መታው፡፡ ሆኖም የአፍሪካ ቁጥር 1 ግብ ጠባቂ የሆነው ዴኒስ ኦኒያንጎ ኳሱን አወጣው፡፡ በዚህ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ሌላ ገጽታ ያዘ፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ሰንዳውንሶች ጨዋታውን በየምክንያቱ ማቆራረጥን ተያያዙት፡፡ የአቻ ውጤቱን የፈለጉ የሚመስል አካሄድን መረጡ፡፡ ፈረሰኞቹ ተደጋጋሚ የተጨዋች ለውጦችን አደረጉ፡፡ በሃይሉ አሰፋን በያሲር ሙገርዋ፣ ፍሬዘር ካሳን በቡሩኖ ኮኔ ቀይሩ፡፡ ሆኖም የበለጠ የቡድኑ ቅርጽ ተበላሸ፡፡ ቡድኑ ቅርጽ አልባ ሆነ፡፡ 83ኛ ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ሰንዳውንሶች ጎል አስቆጠሩ፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት 1-0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋገጠ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባት የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከብዙ ተስፋ እና ጥቂት ቁጭት፣ ከብዙ ደስታ እና ሽራፊ ሀዘን ጋር ሩጫው ተቋጨ፡፡

ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ይህ ጨዋታ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ሆኖ ቱኒዝ ላይ የተካሄደ ጨዋታ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሩጫውን መጨረሱን አውቆ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጦ የተከናወነ ጨዋታ ነው፡፡ ጨዋታው ለማከናወን ወደ ሜዳ ሲገቡ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ 4-3-3 የጨዋታ አቀራረብን ይዘው ወደ ሜዳ ገቡ፡፡

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ፈረሰኞቹ ጫና ውስጥ ወደቁ፡፡ ኤስፔራንሶች ሙሉ በሙሉ በጨዋታው ላይ ብልጫ ወሰዱ፡፡ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ቀጠሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ሥራ በዝቶባቸው ቆዩ፡፡ ሆኖም መረባቸውን መጠበቅ የቻሉት ለ28 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ኤስፔራንሶች በ28ኛ፣ 35ኛ፣ 81ኛ እና 90+4ኛው ዲቂቃ ላይ 4 ጎሎችን አስቆጠሩ፡፡ ፈረሰኞቹ ከፍጹም የጨዋታ ብልጫ ጋር 4-0 በሆነ ውጤት ተሸነፉ፡፡ ይህም የ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፍጻሜ ሆነ፡፡

የ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ አንጸባራቂ ድሎችን የተጎናጸፈበት ነው፡፡ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ የመግባት የረጅም ዓመት ዕቅድ የተሳካበት ዓመት ነው፡፡ የምድብ ድልድል ውስጥ ከመግባት አልፎ ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ የታየበት የውድድር ዓመት ነው፡፡ ከታጣው ይልቅ የተገኘው፣ ከጎደለው ይልቅ የሞላው የሚበልጥበት የውድድር ዓመት ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የቅዱስ ጊዮርጊሱ የፊት አጥቂ 7 ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችሏል፡፡

ውድ የፈረሰኞቹ ገጽ ተከታታዮች፣ የ2018 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሊጀመር ቀናቶች መቅረቱን ተንተርሰን የቅዱስ ጊዮርጊስን የ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞ ባለፉት 3 ክፍሎች ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ እጅግ አስደናቂ የሆነውን የውድድር ዓመት እያነሳን ለማስታወስ ሞክረናል፡፡ ይህ ብዙ ትዝታዎችን እና ድሎችን የተቀናጀንበት ዓመት አልፏል፤ ነገር ግን ዛሬም የትላንትን ድል የምንደግምበት እና የትላንትን ታሪክ ተሻግረን ሌላ አዲስ ታሪክ ለመስራት የሚያስችለን የውድድር ዓመት ሊጀመር ቀናቶች ቀርተውታል፡፡

ይህ የውድድር ዓመት ያለፈውን አመት ጠንካራ ጎናችንን የምናስቀጥልበት እና የቀደመውን ዓመት ስህትት የምናርምበት ሊሆን የግድ ይለናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በትላንት ድል ብቻ የሚዘከር ክለብ አይደለም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት የትላንት ድል እየተዘከረ ዛሬም ታሪክ የሚሰራበት ቤት ነው፡፡ የድል ታሪክ እና አዲስ ድል ተረባርበው የገነቡት ክለብ ነው፡፡ የዚህ የውድድር ዓመት ጉዞ በመጪው እሁድ በይፋ ይጀመራል፡፡ ፈረሰኞቹ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከደቡብ ሱዳኑ አል ሰላም ዋኡ ጋር እሁድ በ10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ያከናውናሉ፡፡

መልካም የውድድር ዓመት እና ድል ለታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ!
እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ