ትውስታ - በ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞ - ክፍል 2


የ2018 የቶታል ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የክለቦች ውድድር በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ይጀመራል፡፡ በዚህ ውድድር ለተከታታይ 4 አመታት ኢትዮጵያን በመወከል ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ይሳተፋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ በአፍሪካ ሻምዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ክለብ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ መጀመርን ተንተርሰን ያሳለፍነው ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞን እያነሳሳን እንገኛለን፡፡ በትላንትናው ዕለት በክፍል አንድ ምልከታችን ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2017 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ እና የ1ኛ ዙር ጨዋታን ማነሳሳታችን ይታወሳል፡፡ ለዛሬ በክፍል 2 ያዘጋጀነው ጽሑፍ ይህንን ይመስላል፡፡

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ
ይህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ እግርኳስ የክለቦች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ያደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ነው፡፡ የዚህ ጨዋታ ድልድል ከተሰማ አንስቶ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዝግጅታቸው ጀመሩ፡፡ በፕሪቶሪያ የሚገኙ ህንጻዎች፣ ጎዳናዎች እና ሆቴሎች ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ መናገር ጀመሩ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አርማዎችን፣ ማሊያዎችን እና መሰል የድጋፍ ቁሳቁሶችን በማዘጋጀት ክለባቸውን ለመቀበል ተዘጋጁ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ የልዑካን ቡድን ደቡብ አፍሪካ ሲደርስ ቁጥራቸው በርካታ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ደማቅ አቀባበል ተደረገለት፡፡ ከአየር ማረፊያ እስከ ሆቴል በደጋፊዎች ታጅበው ተጓዙ፡፡ ፕሪቶሪያ ከባለሜዳው ቡድኖች በላይ በእንግዶቹ ደጋፊዎች ደመቀች፡፡ በዚህ ሁሉ ደማቅ መስተንግዶው መሃል የጨዋታ ቀን ደረሰ፡፡
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን ነው፡፡ የ2016 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ነው፡፡ ይህ በስፍራው ለነበሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሚያሳስባቸው ነገር አልነበረም፡፡ ሃሳባቸው እንደ ተራራ የገዘፈውን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲፈትነው ማየት ነው፡፡ ዓላማቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ታላላቅ ቡድኖችን መፈተን የሚችል ክለብ መሆኑን ማሳየት ነው፡፡

በጨዋታ ቀን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከተለያዩ ስፍራዎች ፕሪቶሪያ ላይ ተሰባሰቡ፡፡ ፕሪቶሪያ ዝናባማ እና ከፍተኛ ብርድ እያስተናገድች ብትገኝም ይህ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሉካስ ሞሪፔ ስታዲየም እንዳያቀኑ እንቅፋት አልሆነባቸውም፡፡ በተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮች ወደ ስታዲየም ተጓዙ፡፡ የስታዲየሙን አንዱን ክፍል ሞልተው በዝማሬ ስታዲየሙን ማድመቅን ተያያዙት፡፡

ጨዋታው ተጀመረ፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ከመደበኛ አሰላለፍ ለውጥ እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው ነባራዊ እውነታዎች ነበሩ፡፡ ምንተስኖት አዳነ እና ሳላሃዲን ሰኢድ ይህ ጨዋታ በቅጣት የሚያልፋቸው ፈረሰኞቹ ነበሩና እነዚህን ተጨዋቾች በሌሎች ቀይረው ቀረቡ፡፡ እንዲሁም የማሜሎዲ ሰንዳውን የጥቃት መስመር የነበረውን የቀኝ የሜዳ ክፍል ላይ አንድ ያልተጠበቀ ውሳኔ አሳለፉ፡፡ በመሃል ተከላካይነት ሳላሃዲን በርጌቾ እና ደጉ ደበበን አጣምረው አስቻለው ታመነ በቀኝ መስመር ተከላካይነት እንዲሰለፍ አደረጉ፡፡

በጨዋታው ጅማሬ ላይ ሰንዳውንሶች በተደጋጋሚ የፈረሰኞቹን የግብ ክልል ጎበኙ፡፡ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አደረጉ፡፡ ሆኖም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች የሚያልፉ ኳሶች ከሮበርት ኦዶንኮራ ማለፍ አልተቻላቸውም፡፡ ሮበርት ማሜሎዲ ሰንዳውንሶች የፈጠሯቸውን ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን በመያዝ ግቡን አላስደፍርም አለ፡፡ በአስደናቂ አቋሙ ብቃቱን አስመሰከረ፡፡ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ ፈረሰኞቹ የበለጠ እየተደራጁ መከላከል ጀመሩ፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንሶች በቀላሉ ፈረሰኞቹን ማለፍ እና የግብ ዕድል መፍጠር እየተሳናቸው መጣ፡፡

ማሜሎዲ ሰንዳውንሶች የተለያዩ የማጥቃት ዕቅዶችን መተግበር ተያይዘዋል፡፡ ኳሶችን በማደራጀት እና በመስመር አጥቂዎች የአግድሞሽ ሩጫ በመታገዝ የሞከሩት ዕቅድ ስላልተሳካ በ2ኛ ኳስ ለመጠቀም መሞከር ተያይዘዋል፡፡ ሆኖም ይህ የጨዋታ ዕቅድም አልተሳካም፡፡ የጨዋታ ዕቅዳቸውን በመከላከል ላይ ያደረጉት ፈረሰኞቹ ዕቅዳቸውን በሚገባ ተወጡ፡፡ ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ፡፡ ፈረሰኞቹ ወሳኝ 1 ነጥብ ከሜዳቸው ውጪ በመያዝ ከታላላቅ ክለቦች ጋር መፋለም ብቻ ሳይሆን ታላላቅ ቡድኖችን ማቆም እንደሚችሉ አሳዩ፡፡


ፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ወደ አዲስ አበባ ከመመለሳቸው በፊት ሶዌታን ላይቭ ከሚባል ድረ ገጽ ጋር ቆይታ አድርገው የሰጡትን አስተያየት የፈረሰኞቹ ገጽ ወደ አማርኛ ተርጉሞ በወቅቱ ያቀረበው ዘገባ ይህንን ይመስል ነበር፡፡

«ካለፉት 17 አመታት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በአፍሪካ ውስጥ ነኝ፡፡ በ6 አገራት በአሰልጣኝነት ሰርቻለሁ፡፡ በመሆኑም ተጨዋቾቼ ካላቸው የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የተሻለ እኔ አለኝ፡፡ በዚህም ምክንያት የተነሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ እኔን መርጦኛል፡፡ እኔም ደስተኛ ነኝ፡፡
እኔ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ነኝ፡፡ በእኛ የአሰልጣኝነት ትምህርት ውስጥ የጨዋታ ትንተና በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በመሆኑም ከራሴ ሰዎች ጋር በመሆን ከጨዋታው በፊት የሰንዳውንስን ጨዋታ መርምሬያለሁ፡፡ እኛ ለእያንዳንዱ ጨዋታ የራሳችን ሰው እንልካለን፡፡ በመሆኑም ለቀጣይ ጨዋታ በቱኒዝ የራሳችን ሰው አለን፡፡
ይህ የአቻ ውጤት ለእኛ ድል ነው፡፡ የተጫወትነው ኳስን በአጭር ቅብብል እና በፍጥነት ከሚጫወት ቡድን ጋር ነው፡፡ ይህንን እኛ በአገራችን ውስጥ መጠቀም አለመድንም፡፡ በመሆንም ይህ ለእኔ ተጨዋቾች ትልቅ ልምድ ይሆናቸዋል፡፡ በመሆኑም ሰንዳውንስን ማቆም በመቻላችን እና ይህ አጨዋወታችንን ሊሰበሩ ባለመቻላቸው ኩራት ይሰማኛል፡፡ በእኔ አመለካከት ቅርጻችንን ጠብቀን እና በጣም ተደራጅተን ተጫውተናል፡፡»

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤኤስ ቪታ
ይህ ጨዋታ የምድቡ 2ኛ ጨዋታ ነው፡፡ ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም መካሄዱም ይታወሳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ አንድ ነጥብ ይዞ በመመለሱ ጨዋታው በታላቅ ጉጉት ተጠብቋል፡፡ እንደ ተለመደው ሁሉ የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ዙሪያው ተጥለቀለቀ፡፡ ባለቀለም የስታዲየም ማስዋቢያዎች ተዘጋጁ፡፡ አዳዲስ ግጥምና ዜማዎች ተጠኑ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሚታወቁበት የቅብብል ህብረ ዝማሬዎች በስታዲየም መደመጥ ጀመሩ፡፡

ጨዋታው ሲጀመር አዲስ አበባ ስታዲየም የነበረውን ድባብ መግለጽ አዳጋች ነው፡፡ ስታዲየሙ በአንድ አይነት ዝማሬ ተንቀጠቀጠ፡፡ ዝማሬዎች ሙሉውን ስታዲየም ሸፈኑ፡፡ ስታዲየሙ በቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካንማ ቀለማት አሸበረቀ፡፡ ለጥንቃቄ ጨዋታ ቅድሚያ የሚሰጡት አሰልጣኝ ማርት ኖይ በ2 የተከላካይ አማካይ ለጨዋታ በመቅረብ በፈጣን ሽግግር ጎል የማስቆጠር ዕቅድን ይዘው ወደ ሜዳ ገቡ፡፡

ጨዋታው በተጀመረ 2ኛ ደቂቃ ላይ ፕሪንስ ሰቬርኒሆ ያሻገረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመለሰ፡፡ ይህ የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ ሙከራ ሆነ፡፡ ሆኖም የጨዋታውን የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ቪታ ብልጫ ወስዶ ነበር፡፡ ሆኖም ከ15 ደቂቃ በኋላ ፈረሰኞቹ የተወሰደባቸውን ብልጫ አስመለሱ፡፡ ጨዋታውን መቆጣጠር ቻሉ፡፡ በተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር ቻሉ፡፡
ሆኖም ጨዋታው ጎል ማስተናገድ አልቻለም፡፡ በደጋፊያቸው አይነተኛ እገዛ እየተደረገላቸው የሚገኙት ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢንቀሳቀሱም ግብ ማስቂጠር አልቻሉም፡፡ ጨዋታው 59ኛ ደቂቃ ላይ ደረሰ፡፡ ቪታዎች በግብ ክልላቸው አከባቢ ኳስን እየተቀባበሉ ሳለ አብዱልከሪም ኒኪማ ተከላካዩን ተጭኖ ኳሱን ተቀበለው፡፡ የተቀበለውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለሚገኘው ሳላሃዲን ሰኢድ አቀበለው፡፡ ሳላሃዲን ኳሱን አክርሮ በመምታት ድንቅ ጎል አስቆጠረ፡፡

ስታዲየሙ በጩኸት ተናጋ፡፡ በዝማሬ ተንቀጠቀጠ፡፡ ደጋፊዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው ድረስ በደስታ ፈነጠዙ፡፡ ጨዋታውን በቀጥታ እያስተላለፈ የሚገኘው የቢኢን ስፖርት የቀጥታ አስተላለፊ «እግርኳስን በዚህ አይነት የስታዲየም ድባብ እና ተመልካች ፊት የሚያደርጉ ተጨዋቾች ዕድለኞች ናቸው፡፡ በዚህ ሰዓት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደስታ እና ድጋፍን መግለጽ ከባድ ነው፡፡» ሲል ገለጸው፡፡

ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 ነጥቦችን በመሰብሰብ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቦችን በመሰብሰብ መጓዙን ቀጠለ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራስ ደ ቱኒዝ

ይህ ጨዋታ የምድቡ 3ኛ ጨዋታ ሆኖ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተከናወነ ጨዋታ ነው፡፡ ይህ ጨዋታ በአፍሪካ ትልቅ ስም ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ ከሆነው ከኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ጋር የሚደረግ ጨዋታ ነው፡፡ ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ. ኤሌክትሪክ ጋር ለመጫወት በዝግጅት ላይ ሳለ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ከባድ ህመም አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል አቅንተዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ከህመማቸው ማገገም ባለመቻላቸው ምክንያት ይህ ቡድን በምክትል አሰልጣኞቹ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ እየተመራ ወደ ሜዳ ገባ፡፡

የስታዲየሙ ድባብ እንደተለመደው ነው፡፡ የደጋፊዎች ድጋፍ እና ዝማሬው በተለመደው መልኩ ቀጥሏል፡፡ የሰሜን አፍሪካው ክለብን በማሸነፍ ነጥባቸው 7 ለማድረስ ፈረሰኞቹ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሃይሉ አሰፋን በጉዳት ምክንያት ያጡት አሰልጣኞቹ አብዱልከሪም ኒኪማን በቀኝ መስመር አማካይነት በማሰለፍ አዳነ ግርማን የ10 ቁጥር ተጨዋች አድርገው በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገቡ፡፡
ፈረሰኞቹ ጨዋታውን በተሻለ እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ በአጭር እና በረጅም ኳስ በመታገዝ ግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ 14ኛ ዲቂቃ ላይ ሮበርት ኦዶንኮራ ጉዳት አስተናግዶ በዘሪሁን ታደለ ተቀየረ፡፡ ጨዋታው ቀጠለ፡፡ ፈረሰኞቹ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ኳሶችን አክርረው በመምታት ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ቀጠሉ፡፡ ሆኖም ጨዋታው በተደጋጋሚ መቋረጦች ይገጥመው ነበር፡፡ የኤስፔራንስ ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ሜዳ ውስጥ በመውደቅ ጨዋታውን በተደጋጋሚ ያቋርጡ ጀመር፡፡

ከእረፍት መልስ በፈጣን ቅብብል የግብ ዕድል ለመፍጠት እየሞከሩ የሚገኙት ፈረሰኞቹ የተሻለ መንቀሰቀስ ችለው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በጨዋታው 62ኛ ደቂቃ ላይ የኤስፔራንሱ ተጨዋች ከኳስ ውጪ ተጨዋች በመማታቱ በ2ኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጣ፡፡ የቁጥር ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ኤስፔራንሶች መከላከል ጀመሩ፡፡ እንዲሁም ጨዋታውን በተደጋጋሚ በማቆራረጥ ላይ ትኩረታቸውን አደረጉ፡፡
ጨዋታው 0-0 በሆነ ተፈጸመ፡፡ ፈረሰኞቹ ከሜዳቸው 1 ነጥብ ብቻ ለማግኘት ተገደዱ፡፡ ሆኖም ከ3 ጨዋታ 5 ነጥቦችን በመሰብሰብ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡

ይቀጥላል …







Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ