ትውስታ - በ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞ ክፍል 1


የ2018 የቶታል ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የክለቦች ውድድር በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ይጀመራል፡፡ በዚህ ውድድር ለተከታታይ 4 አመታት አገራችን ኢትዮጵያን በመወከል ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ይሳተፋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ክለብ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ መጀመርን ተንተርሰን ያሳለፍነው ዓመት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞን ልናነሳሳ ወደድን፡፡


ቅድመ ማጣሪያ - ኮት ዲ ኦር ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2017 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ያደረገው ከሲሼልሱ የወቅቱ ሻምፒዮን ኮት ዲ ኦር ጋር ነበር፡፡ ይህ የመጀመሪያ ጨዋታ በሲሸልስ ሲደረግ ፈረሰኞቹ ሳላሃዲን ሰኢድ ባስቆጠራቸው 2 ጎሎች ታግዘው ከሜዳቸው ውጪ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የመልሱን ጨዋታ ወደ ሃዋሳ አቅንተው ያደረጉት ፈረሰኞቹ በርካታ ደጋፊዎቻቸው በሃዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን ተከታትለዋል፡፡ ክለባቸውንም በሚገባ ደግፈው ለድል አብቅተዋል።
ጨዋታው በተጀመረ በ7ኛው ደቂቃ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ በ32ኛ ደቂቃ አስቻለው ታመነ እና በ36ኛ ደቂቃ አዳነ ግርማ ባስቆጠሩት ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 መምራት ጀመረ። ሆኖም ጨዋታው 55ኛ ዲቂቃ ላይ ተቋረጠ፡፡ ይህም የሆነው በስታዲየሙ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ጨዋታ በማግስቱ ቀጥሎ ጨዋታው በነበረው ውጤት 3-0 ተፈጽሟል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ የሲሸልሱን ክለብ ኮት ዲ ኦር በድምር ውጤት 5-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋገጠ፡፡


የ1ኛ ዙር ጨዋታ - ኤሲ ሊዮፓርድስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2017 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የ1ኛ ዙር ጨዋታውን ያከናወነው የኮንጎ ብራዛቪል ክለብ ከሆነው ኤሲ ሊዮፓርድስ ጋር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ጨዋታ እጅግ ወሳኝ ጨዋታ በመሆኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተሰቦች ዘንድ እጅግ በጉጉት የተጠበቀ ጨዋታ ነበር፡፡ ፈረሰኞቹ ይህንን የመጀመሪያ ጨዋታ ለማከናወን ወደ ገጠራማው የኮንጎ ብራዛቪል ግዛት ፓንት ኖር ለመጓዝ ተገደው ነበር፡፡

ይህ ጨዋታ የመጨረሻው መጀመሪያ ጨዋታ ነበር፡፡ የታላቅ ታሪክ መንደርደሪያ ፍልሚያ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት የቀረው ይህንን ጨዋታ በደርሶ መልስ ውጤት ማሸነፍ ነበር፡፡ ለዚህም ፈረሰኞቹ በታላቅ ቁርጠኝነት ወደ ሜዳ ገቡ፡፡ በጨዋታው 25ኛ ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ ባለሜዳው ቡድን ላይ ግብ አስቆጠረ፡፡ የውጤት ሰሌዳው ኤሲ ሊዮፓርድስ 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ መሆናቸውን አሳየ፡፡ የጨዋታው ዳኛ በግልጽ የሚታዩ ጫናዎችን በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ማሳረፍ ጀመሩ፡፡ ጎል አስቆጣሪውን ምንተስኖት አዳነን ባልተገበ መንገድ ከሜዳ በቀይ ካርድ አሰናበቱ፡፡ ፈረሰኞቹ ግን እጅ የሚሰጡ አልሆኑምና በታላቅ ታጋድሎ ኤሲ ሊዮፓርድስንም ሆነ የመሃል ዳኛውን አሸነፉ፡፡ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ ሲሰማ ኤሲ ሊዮፓርድስ 0—1 ቅዱስ ጊዮርጊስ መሆኑ ታወጀ፡፡ ፈረሰኞቹ ከጠንካራ ክለቦች ጋር ከሜዳ ውጪ ሲጫወቱ ያላቸውን ታሪክ ቀይረው ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸናፊ አደረጉ።

በጨዋታው የአሸናፊነትን ጎል ያስቆጠረው ምንተስኖት አዳነ ከጨዋታው በኋላ በፈረሰኞቹ ገጽ በኩል ለደጋፊዎች መልዕክቱን ያስተላለፈው እንዲህ በማለት ነበር፡፡

«ኤሲ ሊዮፓርድስ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ እኛ ለዚህ ጨዋታ በጣም ትኩረት ሰጥተን ወደ ሜዳ ስለገባን ከጨዋታው የምንፈልገውን ውጤት ማግኘት ችለናል፡፡ ለጨዋታው ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን በመግባታችን ተጋጣሚያችን ሳይቀር ተደንቀው ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በምናደርጋቸው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ነገሮችን አክብደን እንመለከት ነበር፡፡ ለራሳችን የምንሰጠው ግምት አነስተኛ ነበር፡፡ አሁን ላይ በስነ ልቦና ረገድ ጠንካራ ሆነናል፡፡ እንደ እኔ ግምት ሁል ጊዜ ዕቅዳችን የምድብ ድልድል ውስጥ መግባት ነው፤ ነገር ግን ጠንክረን ከተጫወትን ከዚያ በላይ መሄድ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡

ሁሌም ቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ስትጫወት ማሊያውን ለብሰክ ለመውጣት ብቻ አታስብም፡፡ ብዙ ታሪካዊ ተጨዋቾች በዚህ ማሊያ ስር አልፈዋልና መጫወት ያለብህ ከእነርሱ እንደ አንዱ ለመሆን ነው፡፡ እኔም በጨዋታው ላይ ጎል በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ለሆነውም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

በጨዋታው ላይ ቀይ ካርድ መመልከቴን እስከ አሁን ማመን አልቻልኩም፡፡ ፋወል ተሰርቶ ኳሱ ቆሞ ነበርና ዳኛውን አናገርኩት፡፡ «ይሄ ፋወል ነው?» ብዬ ስጠይቀው ምንም መልስ ሳይሰጠኝ የቢጫ ካርድ ሰጠኝ፡፡ ከዚያ ዞር ብዬ እየሄድኩ ሳለ ጠርቶኝ ቀይ ካርድ ሰጠኝ፡፡ ይመስለኛው ዳኛው ቀድሞ ቢጫ ካርድ ያለብኝ መስሎታል፡፡ ደግሜ ሳወራው ወረቀቱን አውጥቶ ሲመለከት ቢጫ የለብኝም፡፡ «ምንም ማድረግ አልችልም ውሳኔ ስላሰጠሁ ከሜዳ ውጣ» አለኝ፡፡
እንግዲህ ይሄ ድል የተሳካው ደጋፊዎቻችን ልምምድ ሜዳ ላይ መጥተው «የኢትዮጵያ አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን» ስላሉን ነው፡፡ ለዚህም በጣም እናመሰግናለን፡፡ ስለ መልሱ ጨዋታ ምን ማለት እችላለሁ? ለእኛ ደጋፊዎች መልዕክት ማስተላለፍ ይከብዳል፤ ምክንያቱም ደጋፊዎቻችን የሚያደርጉትን በሚገባ የሚያውቁ ደጋፊዎች ናቸው፡፡» 

የዚህ ጨዋታ የመልስ ግጥሚያ አዲስ አበባ ላይ ሊከናወን የጨዋታው ቀን ደረሰ፡፡ በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ ወደ አፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ የደረሰው ስብስብ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ በአሰልጣኝ ማርት ኖይ የሚመራው ስብስብ ታሪክ ቀያሪነቱን ለማወጅ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሙሉ ስታዲየሙን በመቆጣጠር ድጋፋቸውን ጀመሩ፡፡ ስታዲየሙ በውጥረት ተሞላ፡፡ በቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካንማ ቀላማት ተዋበ። በዝማሬዎች ድብልቅልቁ ወጣ።

ጨዋታው ተጀመረ። የቅዱስ ጊዮርጊስ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነው ሳላሃዲን ሰኢድ 15ኛ ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ አደረገ፡፡ ግብ ጠባቂው ኳሱን በእግሩ እየገፋ ለቡድን ጓደኞቹ ኳሱን አርቆ ለመምታት ሲሞክር ሳላሃዲን ሰኢድ በፍጥነት ግብ ጠባቂው ጋር ደርሶ ኳሱን ተደረበ፡፡ በሰላሃዲን የተደረበችው ኳስ ወደ ጎል ስታቀና ሳላሃዲን በፍጥነት ወደ ኳሷ ላይ ደርሶ የመጀመሪያው ጎል አስቆጠረ፡፡ ስታዲየሙ ከጭንቀቱ ተነፈሰ፡፡ በዝማሬ ነደደ፡፡ በድጋፍ ቀለጠ፡፡
ፈረሰኞቹ የታወቁበትን የጥንቃቄ ጨዋታ ቀጠሉ። በመልሶ ማጥቃት በመጫወት ጫና ለመፍጠር ተንቀሳቀሱ። ኤሲ ሊዮፓርዶች በተደጋጋሚ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ቢደርሱም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ማሸነፍ አልቻሉም።
የጨዋታው መገባደጃ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ላይ ፈረሰኞቹ ተጨማሪ ጎል አስቆጠሩ፡፡ 90+2 ዲቂቃ ላይ የኤሲ ሊዮፓርድስ ተጨዋቾች እና ግብ ጠባቂዎች የቆመ ኳስን ለመሻማት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ሲያቀኑ ሳላሃዲን ሰኢድ የመሃል ሜዳው አቅራቢያ ላይ ቆሞ ኳስ ይጠብቅ ጀመር፡፡ የቅጣት ምቱ ኳስ ሲመለስ ሳላሃዲን እግር ላይ ኳሱ ደረሰ፡፡ ሳላሃዲን ተንደርድሮ የመጣውን የኤሲ ሊዮፓርድ ተከላካይ አታሎ አልፎ ኳሱን ወደ ፊት ለብቻው መግፋት ጀመረ፡፡

በዚህ ሰዓት በስታዲየም ውስጥ የነበሩ ደጋፊዎች ስሜት ምን እንደነበር መግለጽ ከባድ ነው፡፡ ስታዲየሙ በታላቅ ድምጽ ተናወጠ፡፡ ሳላሃዲን ኳሱን ለብቻው ወደ ጎል ይገፋል፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች እና ግብ ጠባቂ ከሳላሃዲን ጀርባ ይከተሉት ነበር። በጭንቀት የተወጠሩ ደጋፊዎች መቆጣጠር በማይችሉት ድምፅ ሳላሃዲንን ያጅቡታል፡፡ ሳላሃዲን ተረጋግቶ ኳሱን ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ድረስ ይዞት ገብቶ በቀላሉ የጨዋታውን ሁለተኛ ጎል አስቆጠረ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ታወጀ፡፡ ፈረሰኞቹ በድምር ውጤት 3—0 አሸነፉ። ታሪክ ተቀየረ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለረጅም አመታት የኢትዮጵያ ክለቦች የከበዳቸውን ዳገት ወጣው፡፡ ተንደርድሮና ጋልቦ ከአፋፉ ላይ ቆመ፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ታሪክ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ የገባው የመጀመሪያው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆነ፡፡
ከታሪክ ቀያሪዎች አንዱ የሆነው ሳላሃዲን በርጌቾ ከጨዋታው በኋላ በፈረሰኞቹ ገጽ በኩል ለደጋፊዎች መልዕክቱን ያስተላለፈው እንዲህ ነበር፡፡

«ከጨዋታው በፊት የነበሩትን ቀናቶች እንዴት ይህንን የረጅም ዓመት ምኞት ማሳካት እንዳለብን ስናስብ ነበር፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ኮንጎ ላይ አሸንፈን ስንመለስ እሁድን በጉጉት ስንጠብቃት ቆየን፡፡ በህይወቴ አንድ ሳምንት እንደዚህ ረዝሞብኝ አያውቅም፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት ውስጤ ሲመላለስ የቆየ ነገር ነበር፡፡ ለዚህ ታላቅ ክለብ ታሪክ ሰርተው ካለፉ ተጨዋቾች መካከል እንዴት ራሴን መካተት እንዳለብኝ ሳሰላስል ቆየሁኝ፡፡ የትላንቱ ጨዋታ ኮንጎ ላይ ካደረግነው ጨዋታ የሚለይበት ነገር ነበር፡፡ ይኸውም በደጋፊያችን ፊት መጫወታችን እና ብዙ የጎል ዕድሎችን ፈጥረን መጠቀም አለመቻላችን ነው፤ ሆኖም ጨዋታውን በድል ተወጣን፡፡ ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የነበረኝን ደስታ ቃላት አይገልጸውም፡፡

እናንተ የክለባችን ደጋፊዎች ሆይ፣ እኔ በህይወቴ እንደ እናንተ ያለ ምርጥ ደጋፊዎችን አይቼ አላውቅም፡፡ ለክለባችሁ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እናመሰግናችኋለን፡፡»

ይቀጥላል ….!

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ