የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከነማ


ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ3 ተከታታይ የክልል ስታዲየም ጨዋታዎች በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል፡፡ ከወልድያ፣ ጎንደር እና ወላይታ ሶዶ ጉዞ እና ጨዋታ በኋላ ከአዲስ አበባ ካሉ ደጋፊዎቻቸው ጋር ይገናኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ1 ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታውን በነገው ዕለት ምሽት 11 ሰዓት ላይ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ያከናውናል፡፡ ይህ ጨዋታ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት እና ጨዋታ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረ ጨዋታ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከነማ 2009 ዓ.ም የእርስ በእርስ ግንኙነት!

2009 . የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት ሐሙስ ታህሳስ 27 ቀን 2009 . ነበር። ይህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9 ሳምንት መርኃ ግብር ሆኖ የተከናወነ ሲሆን ጨዋታው የተካሄደው በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11:30 ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፍጹም የበላይነት 3 ነጥብ ያገኘበት ጨዋታ ነበር፡፡ በጨዋታው ፈረሰኞቹ 3-0 ያሸነፉ ሲሆን አዳነ ግርማ 30 ደቂቃ፣ ሳላሃዲን ሰኢድ 67 ደቂቃ እና አብዱልከሪም ኒኪማ 83 ደቂቃ ላይ የአሸናፊነት ጎሎችን ማስቆጠራቸው ይታወሳል፡፡

በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች የ2ኛ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት ሐሙስ ሚያዚያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ የተካሄደው በድሬዳዋ ስታዲየም ሲሆን ጨዋታው ጅማሬውን ያደረገው ከቀኑ 10 ሰዓት ሲል ነበር፡፡ በዚህ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በመጀመሪያ ዙር የነበራቸውን የበላይነት ያስቀጠሉ ሲሆን ጨዋታው በፈረሰኞቹ 5-3 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


መሃሪ መና በ17ኛ ደቂቃ፣ አዳና ግርማ በ33ኛ ደቂቃ፣ ሳላሃዲን ሰኢድ 45+1  እና በ49ኛ ደቂቃ፣ ፕሪንስ ሰቬርኒሆ 80ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠሩት ጎል ፈረሰኞቹ 5-0 መምራት ችለው ነበር፡፡ ሆኖም ድሬዳዋዎች በቀሪዎቹ 10 ደቂቃዎች 3 ጎል ማስቆጠር የቻሉ ቢሆንም ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 5-3 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 11 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 5 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ፣ 5 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሞ በ1 ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ ድሬዳዋ ከነማ በበኩሉ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል 1 ጨዋታን በአሸናፊነት፣ 6 ጨዋታን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ 4 ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ፈረሰኞቹ 20 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 4 ደረጃ ላይ ሲገኙ ድሬዳዋ ከነማ 9 ነጥቦችን በመያዝ 15 ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡


ድሬዳዋ ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥመው ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በመሆኑ አስቀድመን ድሬዳዋ ከነማ ከሜዳ ውጪ ያለውን ውጤት እንመልከት፡፡ 


ድሬዳዋ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ 5 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 5 ጨዋታዎች ላይ በአንድም ጨዋታ ድል ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ውስጥ በ3 ጨዋታዎች ተሸንፈው በ2 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ ይህም ክለቡ ከሜዳው ውጪ ጨዋታን ሲያደርግ ያለውን ድክመት በግልጽ ያሳያል፡፡ ይህ ክለብ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ሽንፈትን ያስተናገደው በመከላከያ፣ ሀዋሳ ከነማ እና መቐለ ከነማ ሲሆን ውጤቶቹም በሃዋሳ ከነማ 1-0፣ በመከላካያ 1-0 እና በመቐለ ከነማ 2-0 በሆነ ውጤት ነው፡፡ እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል ከወልድያ 0-0 እና ከወላይታ ድቻ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያቷል፡፡


ድሬዳዋ ከነማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ ተጋጣሚውን ካሸነፈ 2 ወር ከ21 ቀን ተቆጥሯል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 ሲሆን ይህ ጨዋታ የተካሄደው በድሬዳዋ ስታዲየም እሁድ ህዳር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ነው፡፡ በአጠቃላይ ድሬዳዋ ከነማ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ላይ 1 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ድሬዳዋ ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው ያደረገው 6 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ነው፡፡ በደጋፊያቸው እና በሜዳቸው ማድረግ ከቻሉት 6 ጨዋታዎች መካከል 1 ጨዋታ ላይ ድል ሲቀናቸው፣ 4 ጨዋታ አቻ ተለያተው በቀሪው 1 ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡ ይህ ክለብ በሜዳው ካከናወናቸው ጨዋታዎች ጅማ አባ ጅፋርን ብቻ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ይህም ጨዋታ የተጠናቀቀው በድሬዳዋ ከነማ 1-0 በሆነ ውጤት ነው፡፡

ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የተሸነፈው ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሲሆን ይህ ጨዋታ የተጠናቀቀው በኢትዮጵያ ቡና 2-0 አሸናፊነት ነው፡፡ ይህ ቡድን በሜዳው ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል 4 ጨዋታዎች አቻ የተለያየ ቢሆን ከደደቢት 0-0፣ ከአዳማ ከነማ 0-0፣ ከፋሲል ከነማ 1-1 እና ከሲዳማ ቢና 1-1 የአቻ ውጤቶቹ ናቸው፡፡ ድሬዳዋ ከነማ በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 3 ጎል ሲያስቆጥር 4 ጎል አስተናግዷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 14 ጎሎችን ሲያስቆጥር 4 ጎሎቹን አስተናግዷል፡፡ ድሬዳዋ ከነማ በበኩሉ 11 ጨዋታዎች 4 ጎሎችን ሲያስቆጥር 9 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካይ በጨዋታ 1.27 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ድሬዳዋ ከነማ በጨዋታ በአማካይ 0.36 ጎል እያስቆጠሩ ለዚህ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ በአማካይ 0.36 ጎሎችን ሲያስተናግድ ድሬዳዋ ከነማ በጨዋታ በአማካይ 0.81 ጎል አስተናግዷል፡፡

የድሬዳዋ ከነማ የጨዋታ አቀራረብ

ድሬዳዋ ከነማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ አዲስ ተጨዋቾችን ያስፈረመ ክለብ ነው፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ስም ያላቸውን እና ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ አምጥቷል፡፡ በያዝነው የውድድር ዓመት ጥሩ አቋም ሊያሳዩ ይችላሉ ተብለው ከተጠበቁ ክለቦች ተርታም የተመደበ ክለብ ነበር፡፡ ሆኖም የታሰበው ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ሰዓት በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡ በጨዋታም ሆነ በውጤት ረገድ እጅግ ደካማ ቡድን መሆኑም በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡


ይህንን ውጤት ማጣት ተከትሎ ወጣቱ እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ጥሩ ስም ካላቸው አሰልጣኞች መካከል የሚጠቀሰው ዘላለም ሽፈራው ክለቡን ከ7 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በኋላ የተለቀቀ አሰልጣኝ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ድሬዳዋ ከነማ ያለፉትን ጨዋታዎች በምክትል አሰልጣኙ ስምዖን አባይ እየተመራ ይገኛል፡፡

አሰልጣኝ ስምዖን አባይ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ 4-4-2 ዳይመንድ የጨዋታ ዘይቤን በሚመሩት ቡድን ላይ እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ የዳይመንድ የጨዋታ ዘይቤ ላይ ጎልህ ሚና ያላቸው የዳይመንዱ የጎን ተሰላፊዎች ሚና ይህንን የጨዋታ ዘይቤ ወደ 4-1-3-2 በተደጋጋሚ ይቀይረዋል፡፡ በተጨማሪም በውስን ጨዋታዎች ላይ የታክቲክ ለውጥ በማድረግ እና በመሃል ሜዳ የተጨዋቾች ቁጥር ለማብዛት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ቡድን ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የጨዋታ ጅማሬው የታክቲክ አቀራረብ ለ4-4-2 ዳይመንድ እና 4-1-3-2 ፎርሜሽን የቀረበ ነው፡፡

ድሬዳዋ ከነማ ቀዳሚ 11 ተሰላፊዎቹን መርጦ ያልጨረሰ ቡድን ነው ብንል የተሳሳትን አይመስለንም፡፡ ይህ ቡድን በተለያዩ ጨዋታዎችን ላይ የተለያዩ ተጨዋቾችን እየሞከረ ይገኛል፡፡ በተከታታይ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ከ3-4 ተጨዋቾችን በጨዋታ ጅማሬ ላይ ቀይሮ የመሰለፍ ዕድልን በመስጠት በቡድን ግንባታ ላይ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ይህም ከአሰልጣኝ ለውጥ እና ቡድኑ አስቀድሞ ሲተገብረው ከነበረው የጨዋታ ዘይቤ ጋር ካለው ልዩነት የመጣ እንደሆነ በግልጽ ይታያል፡፡

ድሬዳዋ ከነማ ኳስ ይዞ በመጫወት እና ኳስን ከራስ ሜዳ በመገንባት ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ለመድረስ የሚሞክር ቡድን ነው፡፡ በዚህም በሜዳው ካሉት የተጨዋቾች ቁጥር ማነስ ጋር በተያያዘ ቡድኑ ተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲሰራ ይታያል፡፡ በተለይም የተከላካይ ክፍሉ በተጋጣሚ ቡድን ጫና ሲደርስበት ተደጋጋሚ ስህተቶችን ይሰራል፡፡ ከግብ ጠባቂ ኳሶችን ሲመሰርቱ እና ኳሱ ተከላካዮች ጋር ሲደርስ ያለመረጋጋት የሚነበብበት ስብስብ ነው፡፡

ድሬዳዋ ከነማዎች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ከገቡ በኋላ ሜዳውን በማጥበብ የሚጫወቱ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ ለዚህም የሚገደዱት ከወገብ በላይ ባላቸው ስብስብ ውስጥ ያሉት 4ቱ የዳይመንድ ቅርጽ የሚሰሩ ተጨዋቾች ከቡድኑ የመስመር ተከላካዮች ያላቸው እገዛ አናሳ ስለሆነ መጠጋጋትን ይመርጣሉ፡፡ ሆኖም የቡድኑ አጥቂዎች ጋር ያላቸው ርቀት የሚታይ በመሆኑ ኳሶችን ሲነጠቁ እና የተነጠቁት ኳሶች ለጥቃት ሲያጋልጣቸው ተመልክተናል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ክለቦች አብዛኛውን ጊዜ ትኩረታቸውን የሚያደርጉት በመሃል ሜዳ ተጨዋቾችን በማከማቸት እና በጥልቀት በመከላካል ላይ ነው፡፡ ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ ቡድኖች አካሄድ በነገው ጨዋታ ላይም ሊከሰት ይችላል ብለን እንገምታለን፡፡ ይህም ከሆነ ድሬዳዋ ከነማ ከ4-4-2 ወደ 4-2-3-1/4-5-1 የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል፡፡ 
በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት የማይሰለፉ ተጨዋቾች!

ከጉዳት ጋር ተያይዞ አሉላ ግርማ እና ናትናኤል ዘለቀ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ምክንያት፣ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ ታደለ መንገሻ እና አቤል አንበሴ ከቀላል ልምምድ ወደ ሙሉ ልምምድ የተሸጋገሩ ፈረሰኞች ቢሆንም የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም፡፡ 



እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን
!

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ