ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!


 የዛሬ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ፣ መጠሪያውን ከምድር ጦር ወደ መከላከያ የቀየረው ክለብ፣ ከአገሪቱ ታላላቅ ክለቦች ተርታ የሚመደብ፣ ታላላቅ ድሎችን ያስመዘገበ፣ በርካታ ደጋፊዎች የነበሩት ክለብ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ምድር ጦር የሚያደርጉት ጨዋታ በከተማዋ ውስጥ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ነበር።


በዚያ ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ በህዝብ፣ ጦሩ በጦር ሰራዊቱ እና በሲቪሉ ህዝብ ይደገፋል። ወታደራዊ የነበረው መንግስት የስሙ መጠሪያ የነበረውን ክለብ ሲቻል በሰላማዊ ድጋፍ ካልሆነም የወታደሩ አዛዦችን ከጀርባ በመላክ ይደገፋል ተብሎ ይታማል። የወታደሩ ኃላፊዎች እና ባለስልጣናት የክለባቸውን እንቅስቃሴ ከእግርኳስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካው ጋር አቆራኝተው ይመለከቱት ነበር። «ወታደራችን አይሸነፍም» የሚለውን አመለካከት በክለባቸውም ላይ ያስተጋቡ ነበር። «የጦሩ በኳስ ሜዳ መሸነፍ የወታደሩን ክብር ይነካል» ብለው ያምኑ ነበር።


የጦሩ ደጋፊዎች በዚያ ወቅት «የጦሩ በር» በሚባለው በዚህ ሰዓት «ሚስማር ተራ» የሚባለውን የስታዲየም ቦታን ይይዛሉ። «ጦሩ ነመኛታ» እያሉ ስታዲየሙን ያደምቃሉ። ከጦር ሰራዊቱ በጉዳት የተሰናበቱ፣ የጦር ሰራዊቱ አባላት እና ሲቪሉ የጦሩ ደጋፊዎች ሚስማር ተራን ጥቅጥቅ አድርገው ይሸፍናሉ።


በዚያ ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ የስታዲየሙን ሰፊ መቀመጫ ይሸፍናል። ወደ ስታዲየም የሚጓዙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በቢጫ ቀለም ጨርቆች ላይ በቀይ "V" ምልክትን አሰርተው ይዘው ይጓዛሉ። በስታዲየም ውስጥ እነዚህ ደጋፊዎች በሚያወለብልቧቸው "V" ምልክቶች ይለያሉ። በሚሰሟቸው የድጋፍ ዝማሬዎች ክለባቸውን ያበረታታሉ፡፡


ምድር ጦር መቻል ተብሎም ይጠራል፡፡ ይህ ክለብ በወታደሩ ይታገዛል። በወታደሩ አመራሮች አይዞህ የሚባል ክለብ ነበር። በዚህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ እና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው በደል ቀላል የሚባል አልነበረም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጦሩ ላይ ጎል ሲያስቆጥር ለደጋፊዎች ስጋት ነበር። ከጦሩ ደጋፊዎች ባልተናነሰ በስታዲየም ውስጥ የጦሩ አንድ አካል በነበሩት ፖሊሶች ጥቃት ይደርስባቸዋል። በአንድ ወቅት ከመርኃ ግብር አወጣጥ ጋር በተያያዘ የወታደራዊው መንግስት የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ሳይቀሩ በእግርኳሱ ላይ ጣልቃ ገቡ። የጦሩ ኃላፊዎች ክለባችን እየተጠቃ ነው በማለታቸው ምክንያት እኚህ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ሳይቀሩ «ማን ነው ጦሩን የነካውብለው ወደ እግርኳሱ መሪዎች ሳይቀር ብቅ ብለው ትዕዛዝ ሰጥተዋል።


ይህ የትላንት ታሪክ ነው። ትላንት በትላንት ታሪኩ አልፏል። ዛሬ ነገሮች አይነታቸውን ቀይረዋል። ትላንት በህዝብ ይደገፍ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ መጠሪያውን እንደያዘ ዛሬም ያለ ዘመን ልዩነት በህዝብ እየተደገፈ አለ። በወታደሩ ይደገፍ የነበረው ምድር ጦር መጠሪያውም ወደ ጸሓይ ግባት በመቀጠል ወደ መከላከያ ቀይሮ አሁንም በኳስ ሜዳ አለ። ቁጥሩ እጅግ በርካታ በነበረው የጦር ሰራዊት እና ሲቪል ህዝብ ይደገፍ የነበረው ክለብ ዛሬ ላይ ደጋፊዎች የሉትም። ሁሉ ድጋፍ እና ትዕይንት ዛሬ ላይ በመከላከያ ዙሪያ የለም።


የቅዱስ ጊዮርጊስ የትላንት ተፎካካሪዎች ዛሬ የሉም። ቅዱስ ጊዮርጊስ ትላንት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ነገም የሚኖር ክለብ ነው የምንለው ከእውነታዎች ተነስተን ነው፡፡ ይህንን እንድንናገር ያለፍንበት ታሪክ፣ የመጣንበት መንገድ እና ያለፍናቸው መሰናክሎች ያስገድዱናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምስረታው አንስቶ ያለ ገደብ እና በጥልቅ እግርኳሳዊ ስሜት ዛሬም ይደገፋል። በአገዛዞች የሚደርስበት በደል ይህንን ደጋፊ አልነቀነቀውም። ከስታዲየም አላጠፋውም። ትላንትም ሆነ ዛሬ ታላቁን ቅዱስ ጊዮርጊስ እየደገፈ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ አርማን እንደለበሰ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምልክቶች ከፍ አድርጎ እያሳየ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡


ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9 ሳምንት መርኃ ግብር ዛሬ 10 ሰዓት ከመከላከያ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

Comments

Popular posts from this blog

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ