የፈረሰኞቹ ገጽ - ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!


ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ወልዲያ፣ ጎንደር እና ወላይታ ሶዶ ላልተጓዙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች «ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው» ብሎ በማለዳ እንደማብሰር ታላቅ ዜና የለም። ያለፉትን ረጅም ቀናት ቅዱስ ጊዮርጊስን ባለማየት ናፍቆት ለተጠጋቸው ደጋፊዎቻችን ይህች ቀን ተናፋቂ ቀን ናት።


ይህ የዛሬው ቀን የራሱ ቀለም አለው። የራሱ ቅኝት አለው። የራሱ ስልተ ምት አለው። ቀለሙ ቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካንማ ነው። ቅኝቱ ቅዱስ ጊዮርጊሳዊ ነው። ስልተ ምቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሚታወቁበት ዝማሬ ነው።


ባለፉት ረጅም ቀናት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ክለቡን ናፍቀዋል ብሎ መግለፅ ስሜታቸው ማሳነስ ነው። ይልቁንም ክለቡን ባለማየት፣ በስታዲየም ባለመታደም፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዝማሬዎች ባለመድመቅ በደረሰባቸው ከባድ ናፍቆት ምክንያት ታመዋል። ይህ ህምም የሚፈወሰው እንደ ዛሬው ባለው ቀን ነው። ይህ ናፍቆት የሚታበሰው የቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያን በሜዳ ውስጥ በማየት ነው። ይህ ናፍቆት የሚሽረው ፈረሰኞቹ በሚጎናፀፉት ድል ነው።


የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ የስታዲየም ውበት፣ የከተማዋ ድምቀት፣ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ህይወት ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ያለው ቀን የአዲስ አበባ ስታዲየምም ሆነ የአዲስ አበባ ዙሪያ ሰላማዊ አየር ይተነፍሳል። እግርኳሳዊ ስሜት እና ጥልቅ የክለብ ፍቅር ብቻ ይነበባል። ይህ ክለብ ለዚህ ዕንቁ ደጋፊ ምኑ እንደሆነ በህይወት እየኖረ ያሳየ የተግባር መምህር፣ የጨዋነት ምሳሌ ነው።


ይህ ደጋፊ ከመሪው ክለብ በየትኛውም የነጥብ ርቀት ላይ ቢሆን፣ ቡድኑ በተከታታይ ነጥብ ቢጥል፣ የቡድኑ አቋም ቢዋዥቅ «የመጨረሻዋ ደስታ የኛ ናት» ብሎ አርማውን ከፍ አድርጎ የሚዘምር ደጋፊ ነው። በክለቡ ላይ ከአለት የጠነከረ እምነት በልቡ የያዘ፣ ሁሌም በከፍታ ስለሻምፒዮንነቱ የሚዘምር ታማኝ ደጋፊ ነው። በየትኛውም ሁኔታም ቢሆን ለሚወደው ክለቡ ዋጋ የሚከፍል፣ የፈረሰኞቹ የጀርባ አጥንት ነው።



ቅዱስ ጊዮርጊስ የ1ኛ ሳምንት የኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ በ11 ሰዓት ከድሬደዋ ከነማ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል።

Comments

Popular posts from this blog

3 የምዕራብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾች በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በሙከራ ላይ ይገኛሉ፡፡

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!