በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ

ያለፉት አመታት የኢትዮጵያ እግርኳስ የክለቦች ውድድር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተመሳሳይ ቅኝቶችን ይዘዋል፡፡ ፖለቲካው ሲያቃጥል እግርኳሱ ይግላል፡፡ ፖለቲካው ሲግል እግርኳሱ ለብ ይላል፡፡ በፖለቲካ መሪዎች የሚሰጡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እግርኳስ ሜዳ ላይ አሻራቸውን በተዘዋዋሪ ያሳርፋሉ፡፡ በእግርኳስ ሜዳ ላይ የሚታዩት ዘረኝነት፣ ወዳጅነት፣ ህብረት እና ክፍፍሎች በተዘዋዋሪ ፖለቲካው መንደር ላይ ቀድመው ይታያሉ፡፡

በእርግጥ ይህ በአለም የእግርኳስም ሆነ የፖለቲካ አካሄድ ላይ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የእግርኳስ ስታዲየሞች ፖለቲካዊ ድጋፍ እና ተቃውሞ ማስተናገጃ ሆነው ያውቃሉ፡፡ ክለቦች በፖለቲካ አካሄዶች ሲጠለፉም ይታያል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ባለባቸው አገራቶች ውስጥ ይህ አይነት አካሄዶች መታየታቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም በዚህ አይነት አካሄድ የተጓዙ አገራት ለእግርኳሳቸው ያተረፉት አንዳችም እምርታ የለም፡፡ እግርኳሱን ወደ ኋላ ጎትተው ጣሉት እንጂ ቀና አላደረጉትም፡፡ እግርኳስን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ፍጆታቸው አዋሉት እንጂ እግርኳስ ከፖለቲካው ያተረፈው ነገር የለም፡፡

በወታደራዊው አገዛዝ ዘመን ይህ አይነት አካሄዶች በስታዲየሞቻችን ውስጥ ታይተው ነበር፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የተቃውሞ አመጽ እግርኳሱን ጠልፎት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወታደራዊ ክለቦች እና በህዝባዊ ክለቦች መካከል በአገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት እጁን አሳረፈበት፡፡ ወታደራዊው ክለብ የወታደሩ፣ ህዝባዊ ክለቦች የተቃዋሚዎች መሳሪያ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ ብሔርን፣ ሐይማኖትን እና መሰል ልዩነቶች የተከሰተበት አልነበረም፡፡ ልዩነቶቹ በፖለቲካ አስተሳሰብ እና በርዕዮተ ዓለም መለያየት ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡ ይህ ልዩነት የእግርኳስ ክለቦች እና ስታዲየሞች ውስጥ ተከስቶ በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል፡፡ ፖለቲካው አሻራውን ያሳረፈበት እግርኳስ ልዩነቶቹ የርዕዮተ ዓለም በመሆናቸው ምክንያት በስርዓት ለውጥ ቆመ፡፡

የእግርኳስ ሜዳዎች የፖለቲካ ማንጸባረቂያ ሲሆኑ አደጋው የከፋ መሆኑን ዩጎስላቪያ ምስክር ትሆነናለች፡፡ በብሔር ግጭቶች ትናጥ የነበረችው ዩጎዝላቪያ የፖለቲካ ልዩነቶቻቸው ማሳያ ስታዲየሞቻቸው ነበሩ፡፡ በተለያዩ ስታዲየሞች ተደጋጋሚ የብሔር ልዩነትን የሚሰብኩ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ የስታዲየም የድምጽ ማስተጋቢያ መሳሪያዎች በብሔርተኞች ቁጥጥር ስር ውለው ልዩነቶች እና ጥላቻዎች ማስተላለፊያ ሆነው ነበር፡፡ የሚቋረጡ ጨዋታዎች፣ በድጋሚ ቀጥለው የማያልቁ ግጥሚያዎች፣ በገልለተና ሜዳ እና በዝግ ስታዲየም የሚካሄዱ ግጥሚያዎች በርክተው ነበር፡፡ በመጨረሻም የሊግ ውድድሩ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም ዩጎዝላቪያ እንደ አገር መቆየት አቅቷት 7 የተለያዩ አገራት ለመሆን ተገዳለች፡፡ የዩጎዝላቪያ የፖለቲካ መጻኢ ሁኔታ አስቀድሞ በግልጽ የታየው በስታዲየሞቻቸው ውስጥ እንደነበር ኢቫን ኦርዶቪክ የተባለው ጸሓፊ «እግርኳስ እና ጦርነት በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ» በተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ አስፍሮታል፡፡

ዛሬ ላይ በስታዲየሞች ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶች እና ሁከቶች መነሻቸው በአገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ አካሄዶች መሆኑ አይካድም፡፡ ባለፉት አመታት በአገራችን በተለያዩ ከተሞች የተከሰቱ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች እና ግጭቶች ቀስ በቀስ ወደ ሰታዲየሞች መምጣታቸውን ለስታዲየም ቤተኛ የሆኑ ደጋፊዎች ያውቋቸዋል ብለን እናስባለን፡፡ በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሱት ግጭቶች በፍጥነት አሻራቸውን በክለቦች ላይ ማሳደራቸው አይካድም፡፡ በህዝቦች መካከል የተከሰቱት ብሔር ተኮር ግጭቶች በቀጥታ ስታዲየሞች ውስጥ ጥላቸውን አጠሉ፡፡

ኢትዮጵያ እየተመራችበት ያለችው ፌደራላዊ ስርዓት ነጸብራቅ በእግርኳሱ ላይ በግልጽ ይታያል፡፡ ቋንቋ ተኮር የሆነው ፌደራላዊ ስርዓታችን የእግርኳስ ክለቦችን በር አንካኩቶ ገብቷል፡፡ «እኛ የእንትን ክልል ወኪል ነን፤ እኛ የእከሌ ህዝብ ወኪል ነን» የሚለው ብሔርን የተንተራሰው አስተሳሰብ የአንድነት መሰባሰቢያ የሆነውን እግርኳስ የልዩነት መንጸባረቂያ አድርጎታል፡፡ «አንድ ያደርጋል» ተብሎ የተሰበከው እግርኳስ «እኛ» እና «እነሱ» በሚሉ አስተሳሰቦች ተከፋፍሏል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በእግርኳሳችን ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ከያዝነው የውድድር ዘመን አንስቶ በግልጽ ይታይ ጀምሯል፡፡ ወትሮም በእግርኳስ ወዳዱ ማህበረሰብ ይዘገብ የነበረው የክለቦች ዜና ዛሬ በብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ተይዟል፡፡ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ዛሬ ላይ «የብሔራችን ወኪል» ብለው ስለሚጠሩት ክለብ መዘገብ የዘወትር ሥራቸው ሆኗል፡፡ የብሔር መብት አራማጆች የእኔ ብለው ስለሚጠሩት ክለብ የቀን ተቀን ሂደት መረጃ ሰጪዎች ሆነዋል፡፡ እነኚህ ዘገባዎች ብሔርን የተንተራሱ እንዲሁም ከአገራዊ ስሜት በላይ ብሔርን ያገነኑ መሆናቸው ለልዩነት ተጨማሪ ግብአቶች መሆናቸው አይካድም፡፡ እነኚህ ብሔርተኛ አራማጆች በዘገባዎቻቸው ውስጥ ጭቆና፣ የሴራ ትንተና እና ከስፖርት መርህ የወጡ ዘገባዎችን በመስራት ስፖርቱን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ጥድፊያ ውስጥ ናቸው፡፡

ዛሬ ላይ ጥቂት የማይባሉ ስታዲየሞች የፖለቲካ ማስተጋቢያ ቦታዎች ሆነዋል፡፡ ስታዲየሞቻችን የተቃውሞ ፖለቲካ ማሰሚያ፣ ስለ ብሔር ጭቆና የሚተነፍሱ አካላት መገኛ፣ ስለ ማንነት እና መሰል ጥያቄዎች የሚሰማባቸው ስፍራዎች ሆነዋል፡፡ ለዓመታት አብሮን የቆየው እግርኳስ ዛሬ ላይ በብሔር ፖለቲካ አራማጆች እየተጠለፈ ይገኛል፡፡ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት ስፖርት የሆነው እግርኳስ በብሔር፣ በዘር እና በጎሳ ከፋፋዮች ጥላ ስር ወድቋል፡፡ ትላንት የአንድ ክለብ ደጋፊ የሆኑ ደጋፊዎች ዛሬ ላይ በብሔር የሚመስሏቸውን ክለቦች ሰብስበው ይደግፋሉ፡፡ የሚደግፏቸውን ክለቦች ስለ እግርኳስ ሳይሆን ስለ ብሔር ውክልና፣ ስለ ጭቆና ማስተጋቢያ፣ የመተንፈሻ መንገድ እና የማንነት ማሳያ አድርገው አስቀምጠዋቸዋል፡፡ ይህ የብሔር ግጭት ከደጋፊዎች አልፎ፣ ተጨዋቾች፣ የክለብ ኃላፊዎች እና ዳኞች ጋር ወላፈኑ ደርሷል፡፡ ይህ ከእግርኳስ ጽንሰ ኃሳብ ያፈነገጠ መሆኑ አይካድም፡፡

የፖለቲካው ወላፈን በጥላቻ ላይ ብቻ ሳይሆን በፍቅር ላይም ጎልቶ ይታያል፡፡ በሁለት ክልል አስተዳዳሪዎች መካከል የሰላም አየር ሲሰፍን የሁለቱ ክለቦች ወንድማማችነት፣ የቅድመ ጨዋታ አቀባበል እና ፍጹም ሰላማዊ የሆነው አየር በስታዲየም ውስጥ ይሰፍናል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል አለመግባባት እና ግጭቶች ከተከሰቱ በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ወቅት ስታዲየም ያለው አየር ልክ እንደዚያው ይሆናል፡፡ የእግርኳስ ስታዲየሞቻችን አየር የሚዘወረው በፖለቲካችን ሙቀትና ቅዝቃዜ ሆኗል፡፡ በአንድ ክልል ስር የሚገኙ ሁለት ክለቦች በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነቶች ምክንያት በስታዲየም ውስጥ በደጋፊዎች መካከል በተነሳ ሁከት ጨዋታዎች ሲቋረጡ የያነውም በያዝነው ውድድር ዓመት ላይ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ድምር ውጤት ዛሬ ላይ እግርኳሳችን ላይ በቀጥታ አሻራውን በግልጽ እያሳረፈ ይገኛል፡፡ በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን ዛሬ ላይ እየተካሄደ አይገኝም፡፡ በ1960 ገደማ በስፖርት እና ፖለቲካ ጉዳይ ሃሳቡን ያካፈለው እንግሊዛዊው የስፖርት ሰው ኤድዋርድ ሃሪሰን ፖለቲካ ስፖርት ውስጥ እጁን ሲያስገባ ያለውን ጉዳት እንዲህ አስቀምጦታል፡፡

«ፖለቲካ እግርኳስ ውስጥ ሲገባ መሰረታዊ መርሆች ይናዳሉ፡፡ ስታዲየሞች የአመጽ ማስተጋቢያ ይሆናሉ፡፡ የእግርኳስ ባለድርሻ አካላት ለህግ እና ስነ ስርዓት ተገዢ መሆናቸውን ያቆማሉ፡፡»

እኚህ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳቶች በግልጽ በእኛ አገር እግርኳስ ላይ እየተመለከትናቸው እንገኛለን፡፡ በፖለቲከኞች እና መሰል አራማጆች መነሻነት የእግርኳስ መርህ በግልጽ ተንዷል፡፡ ወንድማመችነት እና ወዳጅነት ከስታዲየሞቻችን በመጥፋት ላይ ናቸው፡፡ የእግርኳስ ባለድርሻ አካላት የሆኑት ደጋፊዎች፣ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ የክለብ አመራሮች መሰል አካላት ለህግ እና ለስነ ስርዓት ተገዢ መሆንን ትተው ፍትህን በእጃቸው ለማግኘት በመሯሯት ላይ ናቸው፡፡

እግርኳስ የሰላም አየር የሚነፍስበት ስፍራ ነው፡፡ በእርግጥ «ህዝብ በሚሰባሰብባቸው ስፍራዎች ላይ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች አይነሱ» ማለት ቢከብድም ለእግርኳሳችን ጤንነት ከእንደዚህ አይነት አካሄዶች መቆጠብ የምንወደውን እግርኳስ ይታደጋል፡፡ የእግርኳስ ጽንሰ ኃሳብን የሚጋፉ ድርጊቶች ላይ አለመሳተፍ እና የተሳሳቱ አካሄዶችን ማውገዝ ከእግርኳስ ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል፡፡ በቋፍ ላይ ያለው እግርኳሳችን እንኳን ተለያይተን ተጋግዘንም ማንሳት ከብዶናል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ፖለቲካን የተደገፈ እግርኳሳችንን የማላቀቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ እግር ኳስ የአብሮነት ስፖርት መሆኑን ከቃል ባለፈ በተግባር የማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን፡፡

በመጨረሻም ሃናን ኢብራሒም አሊጃክ የተባለች ጸሓፊ ያነሳችውን ሃሳብ ወደዚህ አምጥተን እናብቃ፡፡
«እግርኳስ የፖለቲካውን ውድቀት ይሰበስባል። የስታዲየሙ ንጉስ ይመራዋል፤ ያስተዳድረዋል፡፡ ይህ የመሰባሰብ ባህል ያመጣው ነው። ፖለቲከኞች ግን የተመልካችን መሰባሰብ ተጠቅመው ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ የእግርኳሱን ሜዳ ወደ ብጥብጥ እንዲሁም የመገዳደል ባህል ለወጡት።»

Comments

Popular posts from this blog

3 የምዕራብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾች በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በሙከራ ላይ ይገኛሉ፡፡

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!