በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ
ያለፉት አመታት የኢትዮጵያ እግርኳስ የክለቦች ውድድር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተመሳሳይ ቅኝቶችን ይዘዋል፡፡ ፖለቲካው ሲያቃጥል እግርኳሱ ይግላል፡፡ ፖለቲካው ሲግል እግርኳሱ ለብ ይላል፡፡ በፖለቲካ መሪዎች የሚሰጡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እግርኳስ ሜዳ ላይ አሻራቸውን በተዘዋዋሪ ያሳርፋሉ፡፡ በእግርኳስ ሜዳ ላይ የሚታዩት ዘረኝነት፣ ወዳጅነት፣ ህብረት እና ክፍፍሎች በተዘዋዋሪ ፖለቲካው መንደር ላይ ቀድመው ይታያሉ፡፡ በእርግጥ ይህ በአለም የእግርኳስም ሆነ የፖለቲካ አካሄድ ላይ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የእግርኳስ ስታዲየሞች ፖለቲካዊ ድጋፍ እና ተቃውሞ ማስተናገጃ ሆነው ያውቃሉ፡፡ ክለቦች በፖለቲካ አካሄዶች ሲጠለፉም ይታያል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ባለባቸው አገራቶች ውስጥ ይህ አይነት አካሄዶች መታየታቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም በዚህ አይነት አካሄድ የተጓዙ አገራት ለእግርኳሳቸው ያተረፉት አንዳችም እምርታ የለም፡፡ እግርኳሱን ወደ ኋላ ጎትተው ጣሉት እንጂ ቀና አላደረጉትም፡፡ እግርኳስን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ፍጆታቸው አዋሉት እንጂ እግርኳስ ከፖለቲካው ያተረፈው ነገር የለም፡፡ በወታደራዊው አገዛዝ ዘመን ይህ አይነት አካሄዶች በስታዲየሞቻችን ውስጥ ታይተው ነበር፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የተቃውሞ አመጽ እግርኳሱን ጠልፎት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወታደራዊ ክለቦች እና በህዝባዊ ክለቦች መካከል በአገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት እጁን አሳረፈበት፡፡ ወታደራዊው ክለብ የወታደሩ፣ ህዝባዊ ክለቦች የተቃዋሚዎች መሳሪያ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አስተሳሰብ ብሔርን፣ ሐይማኖትን እና መሰል ልዩነቶች የተከሰተበት አልነበረም፡፡ ልዩነቶቹ በፖለቲካ አስተሳሰብ እና በርዕዮተ ዓለም መለያየት ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ፡፡ ይህ ልዩነት የእግርኳስ ...