በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ውጤት በማምጣት ጭምር እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ከአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች ጋር ጨዋታዎችን ማድረግ ችለናል፡፡ ከታላላቅ ክለቦች ጋር ስንጫወት ከእግር ኳሱ ጎን ለጎን የምንቀስማቸው አስተዳደራዊ እና መሰል ተግባራት ሊኖሩ ይገባል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ገብቶ ጨዋታዎችን ሲያደርግ የነበረው የሚዲያ አጠቃቀም ደካማ ነበር፡፡ ሆኖም የፈረሰኞቹ ገጽ በዚያ ወቅት አንድም ነገር ለመናገር አልወደድንም ነበር፡፡ ምክንያታችን የነበረው ለውድድሩ እንግዳ ከመሆን የመነጨ ነው በሚል ነበር፡፡ ይህ ከያዝነው ውድድር ዓመት አንስቶ ይስተካከላል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡

ሆኖም ግምታችን ትክክል አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬም በሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ እጅግ ደካማ ክለብ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምስረታ ከረጅም አመት በኋላ የተመሰረቱ ክለቦች ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ሲንቀሳቀሱ እየታዘብን እንገኛለን፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ብዙም በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ታሪክ የሌላቸው ክለቦች ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሚሻሉ እያየን ነው፡፡ ለዚህም ማሳያዎችን እንጥቀስ፡፡

1. የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ይፋዊ ድረ ገጽ!

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የራሱን ድረ ገጽ ከፍቶ መረጃዎችን ያስተላልፍ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ድረ ገጹ ዘመናዊነት ያልተከተለ ቢሆንም ጥረቶቹ ግን የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡ ይህ ድረ ገጽ አሁን ላይ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ ከዓመታት በፊት የተሰጡትን መረጃዎች ይዞ ተቀምጧል፡፡ በአሁን ሰዓት የድረ ገጹ የደረጃ ሰንጠረዥ ማሳያ እያሳየው የሚገኘው የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዥን ነው፡፡ የድረ ገጹ የዜና ማሳያ በዚህ ሰዓት እያሳየ የሚገኘው የ2009 ዓ.ም የ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መረጃን ነው፡፡ የድረ ገጹ ዋና ገጽ «የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ተመለሱ» በሚለው ዜና ላይ ቆሟል፡፡

2. የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ!

ይህ የፌስቡክ ገጽ ከ15 ቀናት በፊት በስራ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም እስከ አሁን ለደጋፊዎች ይፋ ባልተደረገ ምክንያት ከፌስቡክ ላይ ተነስቷል፡፡ ከተነሳም 15 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ 15 ቀናት ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱን ታላቅ ጨዋታ አከናውኗል፡፡ የመረጃ ጥቅም ጎልቶ በወጣበት በዚህ ዘመን ይህ የፌስቡክ ገጽ ከፌስቡክ ላይ ሲነሳ ምንም ዓይነት አማራጭ ክለቡ አልወሰደም፡፡ ለጊዜው ተለዋጭ አካውንት ከፍቶ መረጃን መስጠት አልፈለገም፡፡ ምንም እንኳ የፌስቡክ ገጹ ሳይነሳም በፊት የሚሰራቸው ተግባራት እና የሚከተለው የዘገባ መንገድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የማይመጥን ቢሆንም መኖሩ ብቻ ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ ቢያንስ ደጋፊዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን ገጽ የበላው ጅብ አልጮህ ካለ ሰነበተ፡፡ የፌስቡክ ገጽን ተጠቅሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደጋፊዎቹ አልፎ ራሱን በአህጉራዊ መንገድ ለማስተዋወቅ እና መረጃ ለመስጠት የነበረን አማራጭ አለፈን፡፡

3. የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ይፋዊ የትዊተር አካውንት!

ይህ የትዊተር አካውንት ራሱን ችሎ ተንቀሳቅሶ አያውቀም፡፡ የትዊተር አካውንቱ ከፌስቡክ ጋር ተያያዥ ተደርጎ በፌስቡክ የሚለቀቁ መረጃዎች በቀጥታ ወደ ትዊተር እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያር ወደ ትዊተር ጎራ ብሎ አካውንቱን የሚያንቀሳቅሰው ሰው የለም፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በፌስቡክ ተለጥፈው ስህተት ያለባቸው ጽሑፎች እርማት ሲሰጣቸው በትዊተር ያለው ግን ስህተቱ እንደያዘ እንዲቀመጥ ተፈርዶበታል፡፡ በአሁን ሰዓት የፌቡክ ገጹ በተዘጋበት ሰዓት እንኳ አማራጭ በማድረግ ለመጠቀም የሞከረ የለም፡፡ በመሆኑም በርካታ ተከታዮች ያሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የትዊተር ገጽ አፉን ከፍቶ ከተቀመጠ ረጅም ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡

4. የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የራዲዮ ፕሮግራም!

ይህ የራዲዮ ፕሮግራም በሳምንት ለ1 ሰዓት ብቻ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይህ የራዲዮ ፕሮግራም በቅዱስ ጊዮርጊስ ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የበዛ ትችቶችን አስተናግዶ ነበር፡፡ በዚህም የሥራ አማራር ቦርድ አባላት እርማት እንደሚሰጥ እና መሻሻያ እንደሚደረግበት ተናግረው ነበር፡፡ ሆኖም ዛሬም መጀመሪያ ላይ በተሰፈረበት ሚዛን ላይ እንደተቀመጠ አለ፡፡ እያጎደለ እንጂ እየሞላ አልመጣም፡፡ የደጋፊዎች ትችት እና ወቀሳ ተሰንዝሮበትም በዚያው መልኩ ቀጥሏል፡፡ ዛሬም ለቅዱስ ጊዮርጊስ የማይመጥን የመረጃ አሰጣጥ እና አቀራረብን ይዞ ይገኛል፡፡

ከላይ በጠቀስናቸው የሚዲያ አጠቃቀሞች ዙሪያ ክለባችን የኋላዮሽ ጉዞ ላይ ነው፡፡ እጅግ የወረደ እንዲሁም ለቅዱስ ጊዮርጊስ የማይመጥን አካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ዘመን የክለቦች ውድድር እስከ ሚዲያ ዘርፍ ድረስ ደርሷል፡፡ የክለቦች ደረጃ በሚዲያ አዘጋገብ ሳይቀር ለውድድር ይቀርባል፡፡ ሚዲያ ቀላል ጉልበት እንደሌለው ዘመኑ ምስክር ይሆነናል፡፡ የማንቆጣጠራቸው ሚዲያዎች ላይ ጣታችንን ከመቀሰር በፊት ክለባችን ይህንን እንዲያሻሽል መጠየቅ ከእኛ ከደጋፊዎች ይጠበቃል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ አመራሮችን በዚህ ዙሪያ እንሞግት፡፡ ታላቅነታችንን የሚመጥን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገልጽ ሚዲያ እና የመረጃ አሰጣጥ ይኑረን ብለን ጥያቄ እናንሳ፡፡ ተቆጥረው የማያልቁ ስፖንሰሮችን ይዘን ብዙም ወጪ የማይጠይቁ ነገር ግን ለክለባችን ጥቅማቸው በርካታ የሆኑ ነገሮችን ችላ ባንል ይመረጣል፡፡

ተነግረው የማያልቁ ታሪኮች፣ አፍ የሚያስከፍቱ ድሎች፣ የማይጠገቡ ዋንጫዎች፣ አስገራሚ ውጣ ውረዶችን የያዘ ክለብ በዚህ አይነት የሚዲያ አጠቃቀም ላይ መገኘቱ አሳፋሪ አካሄድ ነው፡፡ መረጃን ለደጋፊ መስጠት ግዴታ የሆነበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ዘመናዊ የሚዲያ አጠቃቀም እና በዕውቀት መረጃዎችን የሚሰጥበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ይህንን አካሄድ ከመከተል ውጪ አንዳችም አማራጭ የለንም፡፡ ስለሆነም ዛሬ ነገ ሳንል ራሳችንን መቀየር ይኖርብናል፡፡

በዚህ ሰዓት ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሰበኩ ያሉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነኚህ ደጋፊዎች የግል ፌስቡክ ገጻቸውን በመጠቀም ቅዱስ ጊዮርጊስን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን ለክለባቸው በመስጠት እጅግ አስደማሚ ድባብን በፌስቡክ ላይ ፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ደጋፊዎች እየሠሩ ያሉትን ስራ እንኳ ክለባችን ሲሰራ አንመለከተም፡፡ በመሆኑም ክለባችን ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያስገድደው ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በሚዲያ ዘርፉ ተገቢው ልምድ እና ዕውቀት ያለውን ሰው በማምጣት የቅዱስ ጊዮርጊስን ገጽታ የመገንባት እንዲሁም የክለባችንን ተደራሽነት ማስፋት ይጠበቃል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

3 የምዕራብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾች በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በሙከራ ላይ ይገኛሉ፡፡

የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ