የፈረሰኞቹ ገጽ - ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!




እንዲህ እንደ ዛሬው የጨዋታ ቀን ሲሆን ማለዳ ላይ የምንሰማው የወፎች ዝማሬ ሳይቀር ቅኝቱ ቅዱስ ጊዮርጊሳዊ ነው፡፡ ቀናችን በቅዱስ ጊዮርጊስ ዝማሬዎች ይጀመራል፡፡ ቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካናማ ለባሹ የጊዮርጊስ ሰራዊት ቀኑ የስራ እና የትምህርት ቀን ቢሆንም እንደ ልቡ ትርታ ዜማውን የሚያደምጠውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ፍለጋ ወደ ስታዲየም ይተማል፡፡ ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰራዊት ማለዳ ከቤቱ ሲወጣ ተማሪው በቦርሳው፣ ሠራተኛው ከሚለብሰው ልብስ ስር ማልያውን አድርጎ ነው፡፡

ከተማው ድንገት እንደ ገና መብራት በቀይ ቀለማት ይዋባል፡፡ እንደ ገና ዛፍ በማራኪ ቀለማቶች ያሸበርቃል፡፡ በቢጫ እና ብርቱካናማ ቀለማት ይደምቃል፡፡

«አሲና በል አሲና ሳንጅዬ እዮሃ፣
አሲና በል እዮሃ አሲና ሳንጅዬ፤
አሲና በል በሳንጃው ጨዋታ፣
አሲና በል አይቆጡም ጌታ፡፡»
ይህ የገና በዓል ሰሞን በሚኖረን ጨዋታ ስታዲየሙን የምናደምቅበት ዝማሬ ነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በዚህ ህብረ ዜማ ካምቦሎጆን ሊያደምቁ፣ የቀኑን ጸሓይ በድምቀታቸው፥ የማታውን ብርድ በትንፋሻቸው ሊያሞቁ ወደ ስታዲየም ያቀናሉ። ከ11ዱ ተሰላፊ እንደ አንዱ ሆነው ከ90 ደቂቃ በኋላ የመጨረሻውን ሳቅ ሊስቁ ደስታቸውን ፍለጋ ካምቦሎጆ ይተማሉ።

ታህሳስ የኛ የቅዱስ ጊዮርጊሳዊያን ወር ነው፡፡ በወሩ መገባደጃ ቀናት ላይ ጨዋታችንን ስናደርግ የምናስባቸው ብዙ ባለውለተኞች አሉን፡፡ ደም እና ላብ እየገበሩ ለክለባቸው ዋጋ የከፈሉትን እናስባለን፡፡ «ቪ በልብ» ብለው መጪውን የተስፋ ቀን ይናፍቁ የነበሩ ቅዱስ ጊዮርጊሳውያንን እናወሳለን፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለትውልድ ያስተላለፉ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ መልበስን ትርጉም ከቃል በላይ በተግባር የገለጹትን እናስታውሳለን፡፡ በእነርሱ ሞት ክለባችንን በህይወት ያቆዩልንን እንዘክራለን።

«ቅዱስ ጊዮርጊስ - እውነተኛ
ቅዱስ ጊዮርጊስ - ስሜቴ ነው
ቅዱስ ጊዮርጊስ - አለኝ ያልኩት
ቅዱስ ጊዮርጊስ - ንብረቴ ነው
ቅዱስ ጊዮርጊስ - እሱን ካጣሁ
ቅዱስ ጊዮርጊስ - መሞቴ ነው
ቅዱስ ጊዮርጊስ - አትንኩብኝ ሳንጅዬን ህይወቴ ነው፡፡»
ይህ ዝማሬ ከጥላፎቅ ካታንጋ ሲደርስ፣ ከዳፍ ትራክ ተነስቶ ከማን አንሼ ሲመለስ ካምቦሎጆ ይንቀጠቀጣል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰራዊት ህብረ ዜማ አካባቢውን ወደ ጣፋጭ አየር ይቀይረዋል፡፡ ምሽቱ በደስታ ይደምቃል፡፡ በስታዲየም ዙሪያ የሚያልፉ ሁሉ ቆም ብለው ያደምጣሉ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ልባቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ፍቅር የቀለጠ አዛውንቶች ዐይን በእንባ ይሞላል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በደስታ የምንዋኝበት የፍቅር ወንዛችን፣ በአንድነት ያቆራኘን ቤተሰባችን ፣ የልጅነት ቅኝታችን፣ የወጣትነት መአዛችን፣ የእርጅና ጊዜ ትዝታችን ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርኃ ግብር ዛሬ በ11 ሰዓት ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ