የፈረሰኞቹ ገጽ - ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!



«ሀሹ ሎኦ የሳ» 
«ሀሹ ሎኦ ጋምአሳ»

የቅዱስ ጊዮርጊስ የልዕካን ቡድን አባላት 312 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ከዕለተ ሐሙስ አንስቶ ከንጉሥ ካዎ ጦና ሀገር ይገኛሉ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የስታዲየም ድምቀት የሚለውን ማዕረጋቸውን አንግበው፥ በቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካናማ ቀለማት ተውበው ወደ ወላይታ ሶዶ ጉዟቸውን ጀምረዋል።

ወላይታ ታሪካዊቷ ምድር ነው። ቀድሞ በታላቁ የዳሞት አስተዳደር በንጉስ ሞቶሎሚ ጊዜ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ ምስራቅ እና መካከለኛው የኢትዮጽያን ሰፊ ክፍል በሚሸፍነው አስተዳደር ወላይታ የግዛቱ አንድ አካል ነበረች፡፡ የዳሞት መንግስት በንጉሥ አምደ ጽዮን መሸነፍ እና መገበር በኋላ «ካዎ» በሚባሉ ነገስታቶች ነፃ ግዛታቸውን ማስተዳደር ጀመሩ።

በመካከለኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ወላይታዎች ለንጉሥ አምደ ጽዮን እና ንጉሥ ይስሀቅ ይገብሩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ሆኖም ከአህመድ ግራኝ ወረራ በኃላ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ መንግስት በመገንጠል ነፃና ሰፊ ግዛት አቋቋሙ። ይህም እስከ 19ኛው መቶ ክፈለ ዘመን የመጨረሻው የወላይታ ንጉስ ካዎ ጦና ድረስ የዘለቀ ሆነ።

ካዎ ጦና!

የመጨረሻው የወላይታ ንጉስ ናቸው። እጅግ ብልህ ጦረኛ እና አዋቂ ንጉሥ ነበሩ። ከንጉሥ ምንሊክ ጦር ጋር ለ6 ያህል ጊዜ ተዋግተው ገትረው ያቆሙ ናቸው። ንጉሥ ካኦ ጦና እስከ 1894 (እ.ኤ.አ) ድረስ በጀግንነት የተዋጉ እንዲሁም ንጉሥ ምኒሊክ በጀግንነታቸው የመሰከሩላቸው ንጉሥ ናቸው። እንዲሁም የኢትዮጵያውን ኩራት በሆነው የአድዋ ጦርነት ወቅት የወላይታን ህዝብ እየመሩ በአድዋው ጦርነት ለሀገራቸው ዋጋ የከፈሉ የነፃነት ባለውለታም ናቸው። ፈረሰኞቹ የሚገኙት ከእነዚህ የጦር ፈረሰኞች ሀገር ነው። እኛም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እየተጓዝን ያለነው ወደዚህ ታሪካዊ አገር ነው።

የኦሞቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ በባህላቸው የሚኮሩ ህዝቦች መገኛ፣ ሙዚቃቸው ብዙኃኑን የሚያወዛውዝ፣ በራቸውን ከፍተው ጋምሳ (በቂንጬ የተሰራ በቅቤ የታሸ ገንፎ) ጋብዘው ቦርዴ (ፐርሶ) አጠጥተው እንግዳ ወደሚቀበሉት ወላይታዎች ሀገር ሶዶ እየተጓዝን እንገኛለን።

ለጊዮርጊስ ሲሉት ውድና ብቸኛ ህይወቱን ለመክፈል የማያመነታው ቤተሰብ፣ ስራና የግል ህይወቱን ትቶ ክለቡን እየተከተለ በጉዞ ላይ ይገኛል። የሚደግፈው ክለብ ቢሸነፍ፣ አቻ ቢወጣም ሆነ ቢያሸንፍ የትም ላይርቅ ቃል ኪዳን የገባው ሰራዊት የቅዱስ ጊዮርጊስ አርማን ከፍ አድርጎ ሰቅሎ ጉዞውን ጀምሯል።

የደቡብን ለምለም መሬት ረግጠን፣ ውብ ተራራዎችን አቆራርጠን፣ ከወላይታዎች መንደር የመድረስ ተስፋን ሰንቀን በዝማሬዎቻችን ታጅበን በጉዞ ላይ ነን። በኦሞቲክ ቋንቋ «ሀሹ ሎኦ የሳ» (እንኳን ደህና መጣችሁ) ሲሉን መልሰን በቋንቋቸው «ሀሹ ሎኦ ጋምአሳ» (እንኳን ደህና ቆያችሁን) ለማለት መንገዳችንን ይዘናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13ተኛው ሳምንት የኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ መርኃ ግብር ዛሬ በ9 ሰዓት በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ከወላይታ ድቻ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።

Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ