የፈረሰኞቹ ገጽ - የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ (ቅዳሜ) አንስቶ
በአዲስ አበባ እና በክልል ስታዲየሞች ይካሄዳሉ፡፡ ፈረሰኞቹ የዚህ ሳምንት መርኃ ግብራቸውን ለማድረግ ወደ ወላይታ ሶዶ በትላንትናው ዕለት አቅንተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን ጨዋታ ቅዳሜ በ9 ሰዓት ከወላይታ ድቻ ጋር ያደርጋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ የ2009 ዓ.ም የእርስ በእርስ ግንኙነት!
በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት ቅዳሜ ታህሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር። ይህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ7ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ሆኖ የተከናወነ ሲሆን ጨዋታው የተካሄደው በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ በ9 ሰዓት ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ የውጤት ማጣት ገጥሞት ያካሄደው ጨዋታ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ3 ተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት ያጡት ፈረሰኞቹ በጫና ውስጥ ሆነው ያካሄዱት ጨዋታ የታሰበውን ያህል ከባድ አልነበረም፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ከዚህ ጨዋታ ፍጻሜ በኋላ ለጋዜጠኞች ሲናገሩም የተናገሩት ይህንን ነበር፡፡ በጨዋታው ፈረሰኞቹ አቡበከር ሳኒ እና አዳነ ግርማ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ታግዘው 2-0 ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2009 ዓ.ም የ2ኛ ዙር ጨዋታውን ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረገው ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ የተካሄደው በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ሲሆን በዚህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች
ሳይሸናነፉ 1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በዚህ
ጨዋታ ፈረሰኞቹ ተዳክመው የታዩበት ጨዋታ ነበር፡፡ ይህ ነው የሚባል የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ የቆዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዳነ
ግርማ በ42ኛ ደቂቃ ላይ በተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ በግብ ጠባቂው አናት ላይ በማሳለፍ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ
ነበር፡፡
ሆኖም ከእረፍት በኋላ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ወላይታ
ድቻዎች በ49ኛ ደቂቃ ላይ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርረው በመምታት ያስቆጠሩት ጎል አቻ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ ጎል
በኋላም ወላይታ ድቻዎች ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ በዚህም ይህ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት
ተጠናቋል፡፡
የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?
ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 10 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 5 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ የተቀረውን 5 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሟል፡፡ ወላይታ ድቻ 12 ጨዋታዎችን ማድረግ ሲችል 3 ጨዋታን በአሸናፊነት አጠናቆ 4 ጨዋታን በአቻ ውጤት ጨርሷል፡፡ እንዲሁም 5 ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን
አስተናግዷል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ፈረሰኞቹ 20 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ወላይታ ድቻ 13 ነጥቦችን በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስን ይህንን ጨዋታ የሚያከናውነው ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በመሆኑ አስቀድመን ወላይታ ድቻ በሜዳው ያደረጋቸው ጨዋታዎችን ውጤት እንመልከት፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ወላይታ ድቻ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ያደረገው 5 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ነው፡፡ ወላይታ ድቻዎች በደጋፊያቸው እና በሜዳቸው ማድረግ ከቻሉት 5 ጨዋታዎች መካከል በ2 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናቸው በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተው በ2 ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡ ይህ ክለብ በሜዳው ካከናወናቸው ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻላቸው ክለቦች ኢትዮ ኤሌክትሪክን እና አርባምንጭ ከነማን እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ወላይታ
ድቻ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 እንዲሁም አርባምንጭ ከነማን 1-0 በማሸነፍ ከተደጋጋሚ ውጤት ማጣት ማገገሙን እያሳየ የሚገኝ
ስብስብ ነው፡፡
በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ካደረጉት ጨዋታዎች መካከል
አቻ የተለያዩት ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ሲሆን ውጤቱም 1-1 መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህ ቡድን በደጋፊው እና በሜዳው ታግዞ
በሚያደርገው ጨዋታ በ2 ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን ማስተናገዱን ጠቅሰናል፡፡ አዳማ ከነማ እና መቐለ ከነማ ወላይታ ድቻን በሜዳው
ያሸነፉት ክለቦች ናቸው፡፡ አዳማ ከነማ 2-1 እንዲሁም መቐለ ከነማ 1-0 ወላይታ ድቻን ከሜዳው 3 ነጥብ የቀሙት ክለቦች
ናቸው፡፡ ወላይታ ድቻ በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 5 ጎል ሲያስቆጥር 4 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡
ወላይታ ድቻ በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ 7 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 7 ጨዋታዎች መካከል በ1 ጨዋታ ድል ሲቀናቸው በ3 ጨዋታዎች ላይ የአቻ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ የተቀሩትን 3 ጨዋታዎች በሽንፈት ፈጽመዋል፡፡ ይህ ክለብ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ
ማሸነፍ የቻለው መከላከያን ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው 1-0 በሆነ ውጤት ነው፡፡
ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ በመጓዝ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ከደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ነው፡፡ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 1-1፣ ከደደቢት 0-0፣ እና ከኢትዮጵያ ቡና 1-1 ጨዋታቸውን በአቻ
ውጤት ያጠናቀቁባቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ ወላይታ ድቻ በአጠቃላይ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 7 ጨዋታዎች ላይ 4 ጎሎችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡
የወላይታ ድቻ የጨዋታ አቀራረብ!
ወላይታ ድቻ የሊጉ ጅማሮ ላይ ከገጠመው የውጤት ቀውስ ለመውጣት በቅርቡ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገ ክለብ ነው፡፡ ይህ
ክለብ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እያለ በ3-5-2 እና በ3-4-3 የጨዋታ ዘይቤ ሲቀርብ እንደነበር ይጣወሳል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ
ተፈሩ የተከላካይ መስመሩን በ3 ተከላካይ ገንብተው ለረጅም የሊግ ጨዋታዎች ላይ ተጠቅመዋል፡፡ ወላይታ ድቻ የአሰልጣኝ ለውጥ
አድርጎ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰኃን ከሾመ በኋላ 4 ተከላካዮችን ሲጠቀም ተመልክተናል፡፡ በዚህም 4-5-1 እና 4-1-4-1 የጨዋታ
ዘይቤን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡
የወላይታ ድቻ የኳስ ምስረታው መልክ መያዝ የሚጀመረው
ከተከላካይ አማካዩ ኃይማኖት ወርቁ ነው፡፡ ይህ ተጨዋች የቡድኑን ባላንስ የሚጠብቅ እና የቡድኑን ኳስ ምስረታ የሚቆጣጠር
ተጨዋች ነው፡፡ ኃይማኖት ወርቁ በአጭር ኳስ ቅብብል ላይ ጥሩ የሚባል ተጨዋች ነው፡፡ እንዲሁም በረጅም የሚያሻግራቸው ኳሶችም
ለመስመር አማካዮች እና አፊት አጥቂው ጥሩ የሚባሉ መሆናቸው በግልጽ ይታያል፡፡
ወላይታ ድቻ ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲሸጋገር የቡድኑ
የመከላካል ዕቅድ የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾችን እግር በእግር በመከተል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የቡድኑ ተጨዋቾች ተመድቦ
የተሰጣቸው ተጨዋች ያለ ይመስል በፍጥነት ተጨዋቾችን እግር በእግር በመከተል እና የመጫወቻ ክፍተት በማሳጣት ላይ ትኩረታቸውን
ያደርጋሉ፡፡ በተለይም ከቡድኑ ፍጹም ቅጣት ምት እስከ ግማሽ ሜዳ ድረስ የሚኖሯቸው 5 ተጨዋቾች የተጋጣሚ ቡድንን ተጨዋቾች
ለመከታተል የሜዳው ጥበት ጥበት ያግዛቸዋል፡፡ ወላይታ ድቻ የትኩረት ማነስ እና ተደጋጋሚ
ስህተትን የሚሰሩ ተከላካዮች እንዳሉት የቅርብ ሳምንታት ጨዋታዎች ያሳያሉ፡፡
ወላይታ ሶዶ ስታዲየም እንደ አብዛኞቹ የክልል
ስታዲየሞች ኳስን መስርቶ ለመጫወት አስቸጋሪ ከሆኑ ሜዳዎች ውስጥ ይገኝበታል፡፡ በዚህም ባለፉት አመታት ፈረሰኞቹ እጅጉን
ሲቸገሩ አይተናል፡፡ ባለሜዳዎቹ እንደ ልባቸው ኳሶችን ሲያንሸራሽሩበት የሚታየው ሜዳ ለእንግዳ ቡድኖች እጅጉን አስቸጋሪ ነው፡፡
በተለይም ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል አቅራቢያ አንስቶ ያለው ወጣ ገባ ሜዳ ለእንግዳ ቡድኖች እጅጉን አስቸጋሪ ነው፡፡ የባለሜዳው
ቡድን ተጨዋቾች ይህ ሜዳ ለግብ ጠባቂ ያለውን አስቸጋሪነት በመረዳት ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ መሬት ለመሬት አክርረው
ኳሶችን በመምታት በወጣ ገባው ሜዳ ታግዘው ግቦችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደርጋሉ፡፡
የወላይታ ድቻው የፊት አጥቂ ጃኮ አረፋት የክለቡ
የግብ ዕድል ፈጠራ እና ግብ አስቆጣሪ ተጨዋች ነው፡፡ ይህ ተጨዋች ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ ቡድን
ተካላካዮች አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይም ወላይታ ድቻዎች መስመሮችን በመጠቀም ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ የሚያሻግሯቸው ኳሶችን
ለመጠቀም ይህ ተጨዋች እጅጉን ይጥራል፡፡ የወላይታ ድቻዎች የማጥቃት ዕቅድ ትኩረቱን የሚያደርገው በዚህ ተጨዋች ላይ ነው፡፡
በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት የማይሰለፉ ተጨዋቾች!
ከጉዳት ጋር ተያይዞ አዳነ ግርማ፣ አሉላ ግርማ፣ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ አቤል አንበሴ እና ታደለ መንገሻ ከጉዳታቸው ሙሉ በሙሉ ማገገም ባለመቻላቸው የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም፡፡ ያለፉትን ቀናት በህመም ምክንያት ከፈረሰኞቹ ጋር ልምምድ ያልሰራው ምንተስኖት አዳነ ቡድኑ
በቦታው ላይ ተጨዋቾች የሌሉት እንደመሆኑ መጠን በጨዋታው ላይ የመሰለፍ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!
Comments
Post a Comment