የፈረሰኞቹ ገጽ - የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ አንስቶ በክልል እና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዚህ ሳምንት መርኃ ግብሩን የሚያከናውነው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲሆን ተጋጣሚው ጅማ አባ ጅፋር ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሐሙስ በ11 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል፡፡
የጅማ አባ ጅፋር ጉዞ ከከፍተኛ ሊግ እስከ ፕሪሚየር ሊግ!
ጅማ አባ ጅፋር በ2009
ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውስጥ ሲወዳደር የቆየ ክለብ ነው፡፡ በወቅቱ በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደር ጅማ ከተማ በሚል መጠሪያ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ካለፈው
ዓመት መገባደድ በኋላ የመጠሪያ ለውጥ በማድረግ ወደ ጅማ አባ ጅፋር መጠሪያቸውን ቀይረዋል፡፡ እጅግ አድካሚ በሆነው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ የምድቡ ቀዳሚ በመሆን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው ባሳለፍነው ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር፡፡ ይህ ቡድን የከፍተኛ ሊጉ አሸናፊ ለመሆን በድሬዳዋ ስታዲየም ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረገው ጨዋታ ድል ቀንቶት የከፍተኛ ሊጉ ሻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመጣ ክለብ ነው፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ የጅማ ከተማው ተጨዋች አቅሌስያስ ግርማ በ22ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ጅማ ከተማ የከፍተኛ ሊጉ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል፡፡
ጅማ አባ ጅፋር ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከመጣ ጀምሮ ቡድኑን ለማጠናከር ተንቀሳቅሷል፡፡ በቀዳሚነት ባሳለፍነው ዓመት ከጅማ አባ ቡና ጋር የነበሩት አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ ወደ ከፍተኛ
ሊግ የወረደ ክለባቸውን ለቀው ጅማ አባ ጅፋርን ይዘዋል፡፡ እኚህ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ ረጅም አመት ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ በቀዳሚነት ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀሉ አሰልጣኝ
ናቸው፡፡ ይህ ክለብ ከ10 በላይ አዲስ ተጨዋቾችን በማስፈረም እንዲሁም ወደ 8 የሚደርሱ ተጨዋቾቹን ውል በማደስ ቡድኑን እንደ አዲስ በማደራጀት ላይ የቆየ ክለብ ነው፡፡
ዳዊት አሰፋ፣ሄኖክ አዱኛ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ፣
ቢኒያም ሲራጅ፣ እንዳለ ደባልቄ፣ አሸናፊ ሽብሩ፣ ጌቱ ረፌራ፣ ሳምሶን ቆልቻ፣ ዮናስ ገረመው፣ ይሁን እንዳሻው፣ አሚኑ ነስሩ
እና የመሳሰሉት ተጨዋቾች በዚህ ዓመት ብቻ ክለቡን ከአገር ውስጥ ውድድር የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
ጅማ አባ ጅፋር በአገር ውስጥ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች ጎን ለጎን 3 የውጭ አገር ተጨዋቾችን አስፈርሟል፡፡ ጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ኦጄ፣ የማሊ ዜግነት ያለው ሲሶኮ አዳማ እና
ናይጄሪያዊው የፊት አጥቂ አኪኪ አፎላቢ በዚህ የውድድር ዓመት ከውጭ አገራት ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ሆኖም ግብ ጠባቂው ዳንኤል ኦጄ ወደ ሀገሩ አቅንቶ
ባለመመለሱ ምክንያት በዚህ ወቅት የጅማ አባ ጅፋርን የግብ ክልል እየጠበቀ የሚገኘው በያዝነው የውድድር ዓመት ከወልድያ
ያስፈረሙት ዳዊት አሰፋ ነው፡፡
የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?
ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 7 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 3 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ የተቀረውን 4 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሟል፡፡ ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ካደረጋቸው 9 ጨዋታዎች መካከል 4 ጨዋታን በአሸናፊነት፣ 2 ጨዋታን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በ3 ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ፈረሰኞቹ 13 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ጅማ አባ ጅፋር 14
ነጥቦችን በመያዝ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ጅማ አባ ጅፋር ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥመው ከሜዳው ውጪ
ተጉዞ በመሆኑ አስቀድመን የጅማ አባ ጅፋርን ከሜዳ ውጪ ያሉ ውጤቶችን እንመልከት፡፡
ጅማ አባ ጅፋር በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ 4 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 4 ጨዋታዎች ላይ 1ጨዋታን ማሸነፍ ሲችል፣ በ2 ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግዶ የተቀረውን 1 ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ማሸነፍ የቻለው አርባምንጭ ከነማን ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው በጅማ አባ ጅፋር 3-1 አሸናፊነት ነው፡፡ ይህ ክለብ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ሽንፈትን ያስተናገደው በመቐለ ከነማ እና በድሬዳዋ ከነማ ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት ነው፡፡
ጅማ አባ ጅፋር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የመጀመሪያ
የሆነውን የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ያደረገው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ሲሆን ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የጨዋታው
መገባደጃ ላይ የውጤት ሰሌዳው 0-0 መሆኑን አሳይቷል፡፡ ጅማ አባ ጅፋር በአጠቃላይ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ላይ 3 ጎሎችን ሲያስቆጥር 3 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ጅማ አባ ጅፋር በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው ያደረገው 5 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ነው፡፡ በደጋፊ እና በሜዳቸው ማድረግ ከቻሉት 5 ጨዋታዎች መካከል በ3 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናቸው፣ በ1 ጨዋታ አቻ ተለያተው በቀሪው 1 ጨዋታ
ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡ ይህ ክለብ በሜዳው ካከናወናቸው ጨዋታዎች ላይ ሃዋሳ ከነማን፣ ኢትዮጵያ
ቡናን እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ማሸነፍ ችሏል፡፡ በእነዚህ 3 ክለቦች ላይ በድምሩ 7 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ሀዋሳ
ከነማን እና ኢትዮጵያ ቡናን በተመሳሳይ 2-0 እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 3-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው እና
በደጋፊው ፊት የተሸነፈው በፋሲል ከነማ ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ነው፡፡ ይህ ቡድን በሜዳው
ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል በ1 ጨዋታ አቻ የተለያየ ቢሆን ጨዋታው የተካሄደው በአዳማ ስታዲየም እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ጅማ
አባ ጅፋር ሜዳው በመቀጣቱ ምክንያት ይህንን ጨዋታ በአዳማ ስታዲየም ለማድረግ ሲገደድ ጨዋታው የተካሄደው ከሲዳማ ቡና ጋር
ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ጅማ አባ ጅፋር በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 7 ጎል ሲያስቆጥር 1 ጎል ብቻ አስተናግዷል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው 7 ጨዋታዎች 8 ጎሎችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎቹን አስተናግዷል፡፡ ጅማ አባ ቡና በበኩሉ በ9 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ሲያስቆጥር 4 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካይ በጨዋታ 1.14 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ጅማ አባ ጅፋር በጨዋታ በአማካይ 1.11 ጎል እያስቆጠሩ ለዚህ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ በአማካይ 0.29 ጎሎችን ሲያስተናግድ ጅማ አባ ጅፋር በጨዋታ በአማካይ 0.44 ጎል አስተናግዷል፡፡
የጅማ አባ ጅፋር የጨዋታ አቀራረብ!
የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስብስብ የሊጉ ጅማሬ ላይ ደካማ መስሎ ቢታይም በቅርብ ሳምንታት ውስጥ አስፈላጊ
ውጤቶችን በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ያለፉት 3 ጨዋታዎች በተከታታይ አሸናፊ መሆኑ ነው፡፡ በአንጻሩ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት 3 ጨዋታዎች ውስጥ 1 ጨወታን በድል ሲወጣ 2 ጨዋታዎች ላይ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አብዛኛውን ጊዜ ቅዱስ
ጊዮርጊስን የሚፈትን ቡድን መስራት ይሳካለታል ብንል የተሳሳትን አይመስለንም፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው መከላከያን በያዘበት
ዓመታት ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን ለመሸነፍ ሲቸገር ተመልክተናል፡፡ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ
በይበልጥ ወደሚታወቅበት 4-4-2 የጨዋታ ፎርሜሽን ፊቱን አዙሯል፡፡ ይህም ስኬታማ ሲያደርገው ተመልክተናል፡፡
ጅማ አባ ጅፋር ባለፉት ጨዋታዎች ላይ 4-4-2
የጨዋታ ፎርሜሽንን ሲተገብር በአብዛኛው ጨዋታዎች ላይ የተጠቀማቸው ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ግብ ጠባቂ፡- ዳዊት አሰፋ
ተከላካዮች:- ሄኖክ አዱኛ፣ አዳማ ሲሶኮ፣ ቢንያም ሲራጅ፣ ኤልያስ አታሮ
አማካዮች፡- ሄኖክ ኢሳያስ፣ ይሁን እንዳሻው፣ አሚን ነስሩ፣ ዮናስ ገረመው
አጥቂዎች፡- ተመስገን ገብረኪዳን፣ ኦኪኪ አፎላቢ
ይህ ስብስብ ባሳለፍነው ሳምንት ወልዋሎ አዲግራት
ዩኒቨርሲቲን 3-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ 3 ቁልፍ ተጨዋቾችን በጉዳት ምክንያት አጥቷል፡፡ የመስመር አማካዩ ዮናስ ገረመው፣
የፊት አጥቂዎቹ አኪኪ አፎላቢ እና ተመስገን ገብረኪዳን ጅማ አባ ጅፋር ከወልዋሎ አዲግራት ጋር ባደረጉት ጨዋታ በጉዳት
ምክንያት ጨዋታውን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ በተለይም ሁለቱ የፊት አጥቂዎቹ ወደ ጨዋታ የማይመለሱ ከሆነ አሰልጣኝ ገብረመድህን
ኃይሌ የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጅማ አባ ጅፋር ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን
ነው፡፡ የመከላከል ዕቅዳቸው በመተባበር ላይ ተመሰረተ ነው፡፡ የቡድኑ 2 አጥቂዎች በመከላከል ላይ ያላቸው ተሳትፎ መልካም
የሚባል ነው፡፡ ተጋጣሚ ቡድን በሜዳው ኳስን እንዳያደራጅ እነኚህ 2 አጥቂዎች ተጨዋቾችን በመጫን ይሳተፋሉ፡፡ የመስመር
ተከላካዮቹ በማጥቃት ላይ የቡድኑን ባላንስ ጠብቀው ይሳተፋሉ፡፡ በተለይም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ በማጥቃት ላይ
ያለው ተሳትፎ ማራኪ ነው፡፡ ይህ ተጨዋች የተጋጣሚን ቡድን ተጨዋቾች በመቀነስ ለመስመር አማካዩ እና ለፊት አጥቂዎች
የሚያደርሳቸው ኳሶች ማራኪ ናቸው፡፡ ይህ የቀኝ መስመር ተከላካይ ከግራ መስመር ተከላካዩ በተለየ የሜዳውን መስመር ሸፍኖ
ይጫወታል፡፡
ጅማ አባ ጅፋር ኳስን ከግብ ጠባቂ አንስቶ በመመስረት
ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ የሚሞክር ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ ምርጫውን የሚያደርገው አጭር ኳስ ላይ ሲሆን ከመከላከል ወደ
ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር መልካም የሚባል ነው፡፡ በተለይም በተጋጣሚ ቡድን ጫና ሲፈጠርባቸው ሁለቱ አጥቂዎች ወደ ራሳቸው
የሜዳ ክልል መስመር ላይ ተጠግተው ራሳቸውን ለመልሶ ማጥቃት የሚያዘጋጁበት መንገድ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ ጅማ አባ ቡና
በያዝነው የውድድር ዓመት ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር ያስቆጠራቸው ጎሎች የእነዚህ የፊት አጥቂዎች ጥረት እና
ተጨዋቾቹ ከኳስ ውጪ ያላቸው እንቅስቃሴ ታክሎበት ነው፡፡
ይህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ ጨዋታ
በ4-4-2 የሚፈተንበት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት መከላከያ ይዞት የገባው 4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ
ነበር፡፡ በዚህኛውም ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር አስቀድሞ የሚጠቀመውን 4-4-2 የጨዋታ ዘይቤ ይዞ ከቀረበ ፈረሰኞች በ5 ቀናት
ውስጥ በተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ይፈተናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሳለፍነው ሳምንት በመከላከያ ላይ በመሃል ሜዳ የቁጥር ብልጫን
ወስዶ፣ ኳስን የመመስረት እና የተጋጣሚ የፍጹም ቅጣት ምት ድረስ የመንቀሳቀስ ፍቃድ የተሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጋጣሚን
የመከላከል ዕቅድ ማክሸፍ እና የግብ ዕድል የመፍጠር ድክመት ታይቶበታል፡፡
በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት የማይሰለፉ ተጨዋቾች!
ከጉዳት ጋር ተያይዞ አሜ መሃመድ፣ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ እና ታደለ መንገሻ ከጉዳታቸው ማገገም ባለመቻላቸው የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም፡፡ የፈረሰኞቹ የአጥቂ አማካይ አብዱልከሪም ኒኪማ
በገጠመው ከባድ የጉንፋን ህምም ምክንያት በትላንትናው ዕለት ልምምድ አልሰራም፡፡ እንዲሁም በዛሬው ዕለት በሚኖረው የመጨረሻ
ልምምድ ላይም የማይካፈል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ ተጨዋች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚያልፈው
ተጨዋች ይሆናል፡፡
እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!
Comments
Post a Comment