የፈረሰኞቹ ገጽ - ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!
ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትለን ረጅም ጉዞ ለማድረግ ስናስብ ከጉዞው በፊት ያሉት ቀናት ይረዝሙብናል፤ ለሊቱ አይነጋልንም። ከረጅሙ ቀን ከለሊቱ ንጋት በኋላ በደረስንበት ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምባሳደሮች ነንና ፍቅራችንን ልናሳይ ጉዟችንን እንጀምራለን። በውብ ዝማሬያችን የብዙዎችን ልብ ልንማርክ፣ በውብ ቀለማቶቻችን መዳረሻ ከተማዎችን ልናደምቅ ቤት ውስጥ የምንተወው የጊዮርጊስ መለያ አይኖረንም። በቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካንማ ማሊያችን አጊጠን፣ ስካርፓችንን በአንገታችን አስረን፣ መኪኖቻችንን በጊዮርጊስ አርማ አስውበን፣ ከቤተሰብም በላይ ያቀራረበንን ጊዮርጊስን ተከትለን እንነሳለን።
«ከሳንጃው ጋር አብረን ለመጓዝ፣ የትም ቢሆን የማይደክመን፣
እምነት አለን በክለባችን ማሸነፍ ነው ያስለመደን»
ብለን እየዘመርን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጀን ልንሆን ወደ ታሪካዊቷ ከተማ ጎንደር በመጓዝ ላይ እንገኛለን። ስለ ጎንደር ካነሳን አይቀር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጎንደርን ያዛመዳቸውን ዕንቁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰው እዚህ ላይ እናንሳው።
«የጎንደር
ልጅ ነው ያውም የቋራ፣
መንግስቱ ወርቁ ልበ ተራራ፡፡»
መንግስቱ ወርቁ ልበ ተራራ፡፡»
ይህን ብለን የዘመርንለት መንግስቱ ወርቁ ከጎንደር ተነስቶ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የነገሰ ጀግናችን ነው፡፡ የጋሽ መንግስቱ ወርቁ ውልደት ቋራ ዮፍታ ጊዮርጊስ በተባለ ቦታ በ1932 ዓ·ም ነው፡፡ አባቱ ፊታውራሪ ወርቁ ስንቄ፣ እናቱ ወይዘሮ እማዋይሽ አብተው ይባላሉ፡፡
ፊታውራሪ
መንግስቱ ወርቁ ከቋራ ተነስቶ፣ አዲስ አበባን ረግጦ፣ በመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት አቋርጦ ከ1951—1966 ዓ·ም ለቅዱስ ጊዮርጊስ 8 ቁጥር ማሊያን ለብሶ ተጫውቷል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ የማንንም ክለብ ማሊያ ያለበሰ ተጨዋች ነው። መንግስቱ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረው በ1951ዓ.ም በሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜ ነው፡፡ ለአስራ ሶስት ዓመታት ከ1951 እስከ 1963ዓ.ም ዘጠና ስምንት ጊዜ ለብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ 61 ጎሎችን ለብሔራዊ ቡድኑ በማግባት ባለታሪክ ነው፡፡
መንግስቱ
ወርቁ የተዋጣለት
ኳስ ተጫዋች ነበር። ኢትዮጵያ በታሪኳ ያያችው የተለየ ተጨዋች ነው በሚለው ብዙዎች ይስማሙበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስን አብዝቶ የሚወድ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን ያለ ስስት የሰጠ ቅዱስ ጊዮርጊሳዊ ነው። የሚወደውን ክለብ በተጨዋችነት አገልግሏል። ታላላቅ ክብሮችን እና ስኬቶችን በ8 ቁጥር ማሊያ ታጅቦ አሳካቷል። በምክትል አሰልጣኝነት ረድቷል። በዋና አሰልጣኝነት ክብሮችን ተጎናፅፏል። ለዚህ ዘመናት ለማይሽረው አገልግሎቱ ይለብሰው የነበረው 8 ቁጥር ማሊያ በክብር ተቀምጦለታል። ለመንግስቱ ክብር ሲባል በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ማንም እንዳይለብሰው ከፍ ተደርጎ ተሰቅሏል።
መንግስቱ
ወርቁ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ለንዋይ ፍቅር አይደለም። ስለተከፈለውም አይደለም። ሥራ ሆኖበትም አይደለም። በአንድ ወቅት ስለ ጊዮርጊስ ሲጠየቅ ይህንን መልሶ ነበር።
«ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስጫወት አንድም ቀን ደመወዝ ተከፍሎኝ አያውቅም፡፡ መጠየቅ ደግሞ ያስፈራል፡፡ በዚያ ላይ ክለቡ የገቢ ምንጭ የለውም፡፡ የሚያጫውትህ የሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ ከማሊያው ጋር ተዋህጄ ስለነበር ትቼ መሄድ አልፈለኩም። ደምተህና ተፈንክተህ ቡድኑን እዚህ ካደረስክ በኋላ እንዴት ጥለህ ትሄዳለህ?
ስለዚህ ጊዮርጊስ
አልከፈለኝም ብዩ አንድም ቀን ገንዘብ ጠይቄ ቀርቶ ሰንፌ አላውቅም፡፡»
«ለጨዋታ ቀን እንኳ ምሳ ካለን መልካም ከሌለን ደግሞ የምንበላው ተበድረን ነው፡፡ የዚህ ክለብ አነሳስ እኮ ይገርማል፤ ከምንም ነው የተነሳው፡፡ በሰዎቹ ጥንካሬና በቲፎዞ ብርታት እንጂ እዚህ ደረጃ የሚደርስ አልነበረም፡፡ ለምሳሌ እኔ ስገባ ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባ እንኳ ስንጫወት ከጨዋታው በኋላ ለአውቶብስ 10 ሳንቲም አይሰጠንም፡፡ ሁል ጊዜ የምመላለሰው በእግሬ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መኪና ሲኖር እግረ መንገዱን ወደዚያ የሚሄድ ካለ ሊፍት ይሰጠኛል፡፡»
«አንዳንዴ
እኛ ምሳችንን
ከቤት በልተን እንመጣለን፡፡ ከጨዋታ በኋላ ደግሞ የሚበላ የለም፡፡ እኔ ለምሳሌ እንደዚያ ተጫውቼ ደክሞኝ በእግሬ ጉለሌ ድረስ መጥቼ ትምህርት ቤት ውስጥ የእራት ሰዓት ካለፈ የጉለሌን ውሃ ጠጥቼ እተኛለሁ፡፡ ለጊዮርጊስ በመጫወቴ እና ባመጣነው ውጤት ስለምረካ ለምግብ አላስብም፡፡»
ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ በ9 ሰዓት በአጼ ፋሲለደስ ስታዲየም ከፋሲል ከነማ ጋር ያደርጋል።
Comments
Post a Comment