የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ በነገው ዕለት በጎንደር አጼ ፋሲለ ደስ ስታዲየም በፋሲል ከነማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ይካሄዳል፡፡ ይህ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት እና ጨዋታ ምክንያት ሳይካሄድ የቆየው ጨዋታ በተስተካካይ መርኃ ግብር መሰረት ይካሄዳል፡፡ ይህ በፋሲል ከነማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የሚካሄደው ጨዋታ በዕለተ ረቡዕ በ9 ሰዓት ጅማሮውን ያደርጋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የ2009 ዓ.ም የእርስ በእርስ ግንኙነት!

በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት ህዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር። ይህ ጨዋታ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ4ኛ ሳምንት መርኃ ግብር ሆኖ የተከናወነ ሲሆን ጨዋታው የተካሄደው በጎንደር አጼ ፋሲለ ደስ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሠዓት ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ፋሲል ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የተጫወተው ከፈረሰኞቹ ጋር ነበር፡፡ ያማረ የእንግዳ አቀባበል እና ማራኪ የስታዲየም ድባብ በታየበት በዚህ ጨዋታ ባለ ሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-1 ማሸነፍ መቻላቸው ይታወሳል፡፡ ፈረሰኞቹ ሳላሃዲን ሰኢድ 12ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ፋሲል ከነማዎች አብዱራሕማን ሙባረክ በጨዋታ እና የጨዋታው መገባደጃ ላይ ኤዶም በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ጎሎች ፋሲል ከነማ አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2009 ዓ.ም የ2ኛ ዙር ጨዋታውን ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረገው እሁድ ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ የተካሄደው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲሆን በዚህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ሳይሸናነፉ 2–2 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ1ኛ ደቂቃ ላይ ራምኬል በቅጣት ምት ባስቆጠረው እንዲሁም 34ኛ ደቂቃ ላይ ብሩኖ ኮኔ ከያሲር ሙገርዋ የተቀበለውን ኳስ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹ ጨዋታውን 2–0 መምራት ችለው ነበር፡፡ ሆኖም ፋሲል ከነማዎች በጨዋታው 2ኛ አጋማሽ በ57ተኛው ዲቂቃ በጨዋታ እንዲሁም በ81ኛው ዲቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠሩት ጎል ጨዋታው 2–2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 9 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 4 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ የተቀረውን 5 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሟል፡፡ ፋሲል ከነማ 10 ጨዋታዎችን ማድረግ ሲችል 3 ጨዋታን በአሸናፊነት አጠናቆ 7 ጨዋታን በአቻ ውጤት ጨርሷል፡፡ በመሆኑም ይህ ጨዋታ በአመቱ ሽንፈትን ባላስተናገዱ ሁለት ክለቦች መካከል የሚካሄድ ነው። ፈረሰኞቹ 17 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ ፋሲል ከነማ 16 ነጥቦችን በመያዝ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን ጨዋታ የሚያከናውነው ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በመሆኑ አስቀድመን ፋሲል ከነማ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያስመዘገበውን ውጤት እንመልከት፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ፋሲል ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ያደረገው 3 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ብቻ ነው፡፡ ፋሲል ከነማ በሜዳው ማድረግ የነበረበት 4 ጨዋታዎችን ቢሆንም ከመቐለ ከነማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ አዲስ አበባ ላይ የተደረገ በመሆኑ በሜዳው ያደረጋቸው ጨዋታዎች ወደ 3 ያወርደዋል፡፡ ፋሲል ከነማዎች በደጋፊያቸው እና በሜዳቸው ማድረግ ከቻሉት 3 ጨዋታዎች መካከል በ1 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናቸው በ2 ጨዋታዎች አቻ ተለያተዋል፡፡ ይህ ክለብ በሜዳው ካከናወናቸው ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው ወላይታ ድቻን ብቻ ሲሆን ያሸነፈበት ውጤትም 1–0 ነው፡፡

ፋሲል ከነማዎች በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ካደረጉት ጨዋታዎች መካከል አቻ የተለያዩት ከወልዲያ እና ከሃዋሳ ከነማ ጋር ሲሆን ከወልዲያ 0—0 እንዲሁም ከሀዋሳ ከነማ 2—2 የአቻ ውጤቶቹ ናቸው፡፡ ፋሲል ከነማ በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 3 ጎል ሲያስቆጥር 2 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡

ፋሲል ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ 6 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 6 ጨዋታዎች መካከል በ2 ጨዋታዎች ድል ሲቀናቸው የተቀሩትን 4 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ ይህ ክለብ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ማሸነፍ የቻለው ወደ ጅማ እና አዲስ አበባ ተጉዞ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያን በተመሳሳይ 1—0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጪ በመጓዝ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ከወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲ፣ ደደቢት፣ አዳማ ከነማ እና ድሬዳዋ ከነማ ጋር ነው፡፡ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2—2፣ ከደደቢት 0—0፣ ከአዳማ ከነማ 0—0 እና ከድሬዳዋ ከነማ 1—1 ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁባቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ ፋሲል ከነማ በአጠቃላይ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 6 ጨዋታዎች ላይ 5 ጎሎችን ሲያስቆጥር 3 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎቹን አስተናግዷል፡፡ ፋሲል ከነማ በበኩሉ በ10 ጨዋታዎች 8 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካይ በጨዋታ 1.22 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ፋሲል ከነማ በጨዋታ በአማካይ 0.8 ጎል እያስቆጠሩ ለዚህ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ በአማካይ 0.22 ጎሎችን ሲያስተናግድ ፋሲል ከነማ በጨዋታ በአማካይ 0.5 ጎል አስተናግዷል፡፡

የፋሲል ከነማ የጨዋታ አቀራረብ!

ፋሲል ከነማ በያዝነው የውድድር ዓመት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የተጠቀመው 4-3-3 የጨዋታ ፎርሜሽንን ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ስብስብ በውስን ጨዋታዎች ላይ 4-2-3-1 የጨዋታ ዘይቤን ለመተግበር የተንቀሳቀሰ ቢሆንም ባለፉት የቅርብ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ምርጫውን 4-3-3 ላይ አድርጓል። ይህም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጎንደር አቅንቶ የሚገጥመው በተመሳሳይ 4-3-3 የጨዋታ አቀራረብ ላይ ያለውን ክለብ ይሆናል፡፡

ፋሲል ከነማ በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርኃ ግብር ከመቐለ ከነማ ጋር ጨዋታውን ሲያደርግ የተጨዋቾች አጠቃቀሙ ይህንን ይመስላል፡፡

ግብ ጠባቂ፡- ሚካኤል ሳማኬ
ተከላካዮች፡- ፍጹም ከበደ፣ ሰኢድ ሀሰን፣ ከድር ሐረዲን፣ አምሳሉ ጥላሁን
አማካዮች፡- ኤፍሬም አለሙ፣ ያሲር ሙገርዋ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ
አጥቂዎች፡- ራምኬል ሎክ፣ ፊሊፕ ዳውዝ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ

የአሰልጣኝ ምንተሰኖት ጌጡ ስብስብ ኳስን በመመስረት እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ የሚሞክር ቡድን ነው። በተለይም በሜዳቸው ሲጫወቱ በዚህ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ ላይ ያተኩራሉ። ፋሲል ከነማ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ጨዋታውን ሲያደርግ የጨዋታው ምት ፈጣን እና አጭር ቅብብልን መሰረት ያደርጋል። ፈጣን ሽግግሮችን ያደርጋል። ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር በአንፃራዊነት ፍጥነት ይታይበታል።

ከቅርብ ሳምንታት አንስቶ የፋሲል ከነማ የማጥቃት አጨዋወት መሰረቱን ያደረገው የአጥቂ አማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ ላይ ይመስላል። ከተከላካይ አማካዩ ያሲር ሙገርዋ የሚነሱት ኳሶች ዕቅድ ለዚህ ተጨዋች መድረስ ነው፡፡ ዳዊት እስጢፋኖስ በመስመሮች መካከል ሆኖ ኳሶችን ሲቀበል የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በግልፅ ይጀመራል። ይህ ተጨዋች ለፊት አጥቂዎች እና ለመስመር አጥቂዎች በመስመሮች መካከል የሚያደርሳቸው ኳሶች የፋሲል ከነማ ሁነኛ የግብ ዕድል የሚፈጠርባቸው መንገዶች ናቸው። በተለይም የመስመር አጥቂው ኤርሚያስ ኃይሉ ራሱን ለአግድሞች ሩጫ አዘጋጅቶ የሚጠብቅበት መንገድ ለፋሲል ከነማዎች የግብ ዕድል ለመፍጠር በተደጋጋሚ ረድቷቸዋል።

ፋሲል ከነማ አስቀድሞ ጎል ካስቆጠረ አጨዋወቱን ከ4-3-3 ወደ 4-2-3-1 ሲቀይሩ ይታያል። በዚህ ሂደት ተጨዋቾች ላይ የሚና ለውጦችን በማድረግ የጨዋታውን ዘይቤ ይቀይራሉ። በዚህ የሚና ለውጥ የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች የመስመር አማካይ ሲሆኑ ዳዊት እስጢፋኖስ ብቸኛ የአጥቂ አማካይ ይሆናል።

ፋሲል ከነማ ከማጥቃት ወደ መከላከል ሲሸጋገር መስመሮችን በመዝጋት የሚያምን ስብስብ ነው። የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች በቡድኑ የመከላከል ሂደት ላይ መስመሮችን በመዝጋት ሂደት ውስጥ በንቃት ይሳተፋሉ። የመስመር አጥቂዎቹ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሆነው ኳሶችን ከመጠበቅ ይልቅ በራሳቸው ሜዳ ክልል በመግባት እና ለመስመር ተከላካዮች አንፃራዊ ሽፋን በመስጠት ላይ ያተኩራሉ።

እነኚህ የመስመር አጥቂዎች በማጥቃት ሂደት ላይ አይነተኛ ሚና አላቸው። በተለይም ቡድኑ ከመከላካል ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር ከአጥቂ አማካዮች በመስመሮች መካከል ተደጋጋሚ ኳሶች ይደርሳቸዋል። በተለይም የአጥቂ አማካዩ የመጨረሻ ኳስ ለእነዚህ የመስመር አጥቂዎች ሲያደርስ በቀደሙት ጨዋታዎች ላይ ተመልክተናል።

በፈረሰኞቹ ቤት ያሉ ጉዳቶች!

ከዚህ በፊት በነበሩት ጨዋታዎች ላይ እንደነበረው ሁሉ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ አሜ መሃመድ፣ ታደለ መንገሻ እና አሉላ ግርማ የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም። የመስመር አጥቂው ጋዲሳ መብራቴ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ቢመለስም የዚህ ጨዋታ አካል ለመሆን የህክምና ባለሙያዎችን እና የአሰልጣኞችን ውሳኔ ይጠብቃል።

እናሸንፋለን፣በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!

Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ