የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፡- ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11 ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ አንስቶ በክልል እና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የዚህ ሳምንት መርኃ ግብሩን የሚያከናውነው በወልድያው ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ስታዲየም ሲሆን ተጋጣሚው ወልድያ ስፖርት ክለብ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልድያ ስፖርት ክለብ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ አርብ 9 ሰዓት ካሄዳል፡፡

ወልድያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳለፍነው ዓመት እርስ በእርስ ግንኙነት!

2009 . የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታቸውን ያደረጉት ረቡዕ ጥር 3 ቀን 2009 . ነበር። ይህ ጨዋታ ምሽት 11፡30 የተካሄደ ጨዋታ ሲሆን የዚህ ጨዋታ አሸናፊ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ በዚህ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ጎል ለማስቆጠር 75 ያህል ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደው ነበር፡፡ በጨዋታው 75ኛ ደቂቃ ላይ ሳላሃዲን ሰኢድ የፍጹም ቅጣት ምት መግቢያ ላይ ያገኘውን ኳስ ለአቡበከር ሳኒ ሰጥቶት አቡበከር ሳኒ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ መሬት ለመሬት ኳሱን አክርሮ በመምታት የጨዋታውን ብቸኛ ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ 2009 . 2 ዙር ጨዋታውን ከወልድያ ጋር ያደረገው ረቡዕ ሚያዚያ 18 ቀን 2009 . ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ የተካሄደው በወልድያ ስፖርት ክለብ በሼህ መሐመድ አል አሙዲ ስታዲየም ሲሆን የዚህ ጨዋታ ውጤት ለቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አስፈላጊ ውጤት ነበር፡፡ ለዚህም እጅግ በርካታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በ8 አውቶብሶች፣ በግል ትራንስፖርት እና በአየር ወደ ስፍራው በማቅናት ከክለባቸው ጎን መገኘታቸው ይታወሳል፡፡

በዚህኛውም ጨዋታ ልክ እንደ አንደኛ ዙር ጨዋታ ፈረሰኞቹ በጨዋታው ላይ ጎል ለማስቆጠር በርካታ ደቂቃዎችን መታገስ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ በጨዋታው 67ኛ ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳላሃዲን ሰኢድ የተቀበለውን ኳስ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት አስደናቂ ጎል አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡

የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 8 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 4 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ የተቀረውን 4 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሟል፡፡ ወልድያ ስፖርት ክለብ በተመሳሳይ 8 ጨዋታዎችን ማድረግ ሲችል 2 ጨዋታን በአሸናፊነት፣ 4 ጨዋታን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ 2 ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ፈረሰኞቹ 16 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 2 ደረጃ ላይ ሲገኙ ወልድያ 10 ነጥቦችን በመያዝ 11 ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን ይህንን ጨዋታ የሚያከናውነው ከሜዳው ውጪ ተጉዞ በመሆኑ አስቀድመን ወልድያ በሜዳው ያደረጋቸው ጨዋታዎችን ውጤት እንመልከት፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ወልድያ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው ያደረገው 3 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ነው፡፡ በደጋፊያቸው እና በሜዳቸው ማድረግ ከቻሉት 3 ጨዋታዎች መካከል 2 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀናቸው 1 ጨዋታ አቻ ተለያተዋል፡፡ ወልድያ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን ያላስተናገደ ክለብ ነው፡፡ እንዲሁም በሜዳው አንድም ጎል ያልተቆጠረበት ክለብ ነው፡፡ ይህ ክለብ በሜዳው ካከናወናቸው ጨዋታዎች ላይ አዳማ ከነማን እና አርባምንጭ ከነማን ማሸነፍ ችሏል፡፡ እነዚህን ሁለት ክለቦች በተመሳሳይ 2-0 በማሸነፍ በሁለቱ ክለቦች ላይ በድምሩ 4 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡

ይህ ቡድን በሜዳው ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል 1 ጨዋታ አቻ መለያየቱን ከላይ መጥቀሳችን ይታወቃል፡፡ በአቻ ውጤት ያጠናቀቁትን ጨዋታ ያደረጉት ከድሬዳዋ ጋር ሲሆን ይህ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ወልድያ  በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 4 ጎል ሲያስቆጥር ምንም ጎል ያላስተናገደ ክለብ ነው፡፡

ወልድያ በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ 5 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 5 ጨዋታዎች መካከል አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ሆኖም ከ5ቱ ጨዋታዎች መካከል በ2 ጨዋታዎች ላይ ሽንፈትን አስተናግዶ የተቀሩትን 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡ ወልድያ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ሽንፈትን ያስተናገደው በሀዋሳ ከነማ እና በኢትዮጵያ ቡና ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው በሃዋሳ ከነማ 4-1 እና በኢትዮጵያ ቡና 2-0 አሸናፊነት መሆኑ ይታወሳል፡፡

ወልድያ ከሜዳው ውጪ በመጓዝ አቻ ውጤት ያስመዘገበው ከፋሲል ከነማ፣ ከሲዳማ ቡና እና ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ነበር፡፡ ከፋሲል ከነማ 0-0፣ ከሲዳማ ቡና 1-1 እና ከወልዋሎ ኢግራት ዩኒቨርሲቱ 0-0 መለያየት ችሏል፡፡ ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ያተከናወነው ጨዋታ የተካሄደው በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሆነ ይታወሳል፡፡  ወልድያ በአጠቃላይ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ላይ 2 ጎሎችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው 8 ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎቹን አስተናግዷል፡፡ ወልድያ በበኩሉ 8 ጨዋታዎች 6 ጎሎችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካይ በጨዋታ 1.38 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ወልድያ በጨዋታ በአማካይ 0.75 ጎል እያስቆጠሩ ለዚህ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ በአማካይ 0.25 ጎሎችን ሲያስተናግድ ወልድያ በጨዋታ በአማካይ 0.88 ጎል አስተናግዷል፡፡

የወልድያ ስፖርት ክለብ የጨዋታ አቀራረብ!

ወልድያ በያዝነው የውድድር ዓመት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የሚጠቀመው 4-2-3-1 የጨዋታ ፎርሜሽንን ነው፡፡ ይህ ክለብ 2 የተከላካይ አማካይን አጣምሮ በመጫወት ላይ ምርጫውን አድርጓል፡፡ ወልድያ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን ሲያደርግ የተጨዋቾች አጠቃቀሙ ይህንን ይመስላል፡፡

ግብ ጠባቂ፡- ኤሚክሪል ቤሊንጌ

ተከላካዮች፡- ያሬድ ሀሰን፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ አዳሙ መሃመድ፣ ታደለ ምህረቴ

የተከላካይ አማካዮች፡- ዳንኤል ደምሴ፣ ሐብታሙ ሸዋለም

የመስመር አማካዮች እና አጥቂ አማካይ፡- ፍፁም ገብረማርያም፣ ምንያህል ተሾመ፣ ያሬድ ብርሀኑ

የፊት አጥቂ፡- ኤደም ኮድዞ

ወልድያ በዚህ ጨዋታ ላይ ከተጨዋቾች ጉዳት እና ቅያሪ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተጨዋቾችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጠቅሟል፡፡ የመስመር ተከላካዩን የተከላካይ አማካይ አድርጎ ጨዋታውን የጀመረው ወልድያ የመሃል ተከላካዩ አዳሙ መሃመድን ጉዳት ተከትሎ ተስፋዬ አለባቸውን የተከላካይ አማካይ አድርጎ በማስገባት ዳንኤል ደምሴን ወደተለመደው ቦታ ወስዷል፡፡ በቀደሙት ጨዋታዎች ላይ የፊት አጥቂ አድርጎ ሲጠቀምበት የነበረው አንዷለም ንጉሴን ወደ ተቀያሪ ወንበር በመውሰድ በዚህ ሰዓት ኤዶም ኮድዞን በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ በአጥቂ አማካይ ቦታ ላይ አስቀድሞ ሰለሞን ገብረመድህንን ሲጠቀም የቆየው ወልድያ በዚህ ሰዓት ምንያህል ተሾመን እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ምንያህል ተሾመ በቀደሙት ጨዋታዎች ላይ የቀኝ መስመር አማካይ ሆኖ ሲሰለፍ የቆየ ተጨዋች ነው፡፡

ወልድያ ከሚጠቀማቸው ተጨዋቾች አንጻር የሚጠቀመው የጨዋታ ዕቅድም ይለያያል፡፡ ለምሳሌ አንዱዓለም ንጉሴን በፊት አጥቂነት ሲጠቀም ቡድኑ ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ በተደጋጋሚ ኳሶችን ለማሻገር ይሞክራል፡፡ በተለይም ለአንዱዓለም ከመስመር የሚጣሉ ኳሶች ይበረክታሉ፡፡ አንዱዓለም ንጉሴ በፊት አጥቂነት በሚሰለፍበት ወቅት ከሚሻገሩ ኳሶች መነሻነት ሜዳውን አጥብበው ለሚጫወቱት የመስመር አማካዮች የሚያዘጋጀው ሁለተኛ ኳስ ለቡድኑ በተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፈጠር መንስኤዎች መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በአጥቂ አማካይ ቦታ ላይ ሰለሞን ገብረመድህንን ሲጠቀም ተጨዋቹ በጠባብ ቦታዎች ላይ ኳስን ከመቀበል እና ከመስጠት ጋር ካለው ክህሎት አንጻር ለአጥቂው እና ለመስመር አማካዮች በመስመሮች መካከል የማድረስ ብቃቱ መልካም የሚባል ነው፡፡

ወልድያ የሚጠቀማቸው የመስመር ተከላካዮች ከማጥቃት ይልቅ ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የሚሄዱት እጅግ በቀዘቀዘ ሩጫ ነው፡፡ወልድያ በግልጽ የሚታይ ደካማ ጎኑ ይህ የመስመር ተከላካዮች ቦታ ነው፡፡ እነኚህ የመስመር ተከላካይ ተጨዋቾች ኳስ የሚገፋባቸው ተጨዋች ሲገጥማቸው በቀላሉ ይታለፋሉ። በእነዚህ ቦታዎች ላይ በግልጽ ጥቃት ሲደርስባቸው ይታያል፡፡ በተለይም የቡድኑ የግራ መስመር ወልድያዎችን ለማጥቃት ሁነኛ መስመር ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የመስመር አማካይ ሆኖ የሚሰለፈው ፍጹም ገብረማርያም ሙሉ በሙሉ በማጥቃት ተግባር ላይ ሰለሚሳተፍ ይህ መስመር ክፍተት ይታይበታል፡፡

የወልድያ የመሃል ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ቢሌንጌ ለወልድያ የመከላከል ተግባር ተጠቃሽ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ እነኚህ የመሃል ተከላካዮች በአየር ላይ ኳስ የተሻለ የሚባል ጥንካሬ አላቸው፡፡ እንዲሁም የክለቡ ግብ ጠባቂ ኤሚክሪል ቤሊንጌ የአየር ላይ ኳስ አጠባበቁ መልካም የሚባል ነው። በተመለከትናቸው ጨዋታዎች ላይ ከመስመር የሚሻገሩ እንዲሁም ከቅርብ ርቀት ጭምር የሚሞከሩበት የአየር ላይ ኳሶች በአስገራሚ ብቃት ሲመልስ ተመልክተናል።  

ወልድያ በሜዳው የግራ መስመር ላይ የማጥቃት ፍላጎት ቢኖረውም ይህ በእንቅስቀሴ የታጀበ አይደለም። ከሜዳቸው ሲወጡ በቁጥር አንሰው መውጣታቸው ይህ የማጥቃት ፍላጎት የበለጠ እንዲጎለብት አያስችላቸውም፡፡ በቡድኑ የመስመር አማካይ ቦታ ላይ የሚገኘው ፍጹም ገ/ማርያም በሚገኝበት የግራ መስመር ላይ ቡድኑ አንጻራዊ ጥንካሬ አለው፡፡ አብዛኞቹ የግብ ዕድሎች እና ሙከራዎች መነሻቸው ከዚህ መስመር ላይ ነው፡፡ ሆኖም ከላይ በጠቀስናቸው ችግሮች ምክንያት አብዛኞቹ ኳሶችም ሲበላሹ እና የግብ ሙከራ ሲሆኑ አይታይም።

በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት የማይሰለፉ ተጨዋቾች!

ከጉዳት ጋር ተያይዞ ጋዲሳ መብራቴ፣ አሜ መሃመድ፣ አሉላ ግርማ፣ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ እና ታደለ መንገሻ ከጉዳታቸው ማገገም ባለመቻላቸው የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም፡፡

እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!

Comments

Popular posts from this blog

3 የምዕራብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾች በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በሙከራ ላይ ይገኛሉ፡፡