ከጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ የምንማራቸው 3 ነገሮች!


ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባ ጅፋርን 3-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ ይህ ጨዋታ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዥ በተከታታይ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክለቦች ያደረጉት ጨዋታ እንደመሆኑ ጨዋታው ትኩረት አግኝቶ ነበር፡፡ በዚህ ጨዋታ ፈረሰኞቹ 3 የቆሙ ኳሶች በተነሱ ኳሶች ታግዘው ጅማ አባ ጅፋርን 3-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የፈረሰኞቹ ገጽ ከዚህ ጨዋታ ተነስተን በዚህ ጨዋታ የምንማራቸው ነገሮችን ለማንሳት ወደድን፡፡

1.ኮሪደሮችን በመጠቀም የግብ ዕድል የሚፈጥርን ክለብ በኮሪደር ማጥቃት ሁነኛ ምላሽ ነው፡፡

ጅማ አባ ጅፋር ኳስን ከግብ ጠባቂ በመመስረት ለመጫወት የሚሞክር ስብስብ ነው፡፡ ይህ ከግብ ጠባቂ የተመሰረተ ኳስ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲደርስ የሚጠቀሙት የጨዋታ ዕቅድ ኳሶችን ወደ ማስመር ማውጣት ነው፡፡ የጅማ አባ ጅፋር ጥንካሬ ምንጭ ኮሪደሮችን መጠቀም ነው፡፡ ለዚህም የቡድኑ ፉልባኮች ሁነኛ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ጅማ አባ ጅፋር የግብ ዕድልን እንደሚፈጥር ይታወቃል፡፡

ትላንት በነበረው ጨዋታ ላይ ይህን ኮሪደር የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ተቆጣጥረውታል፡፡ በግራ መስመር አበባው ቡጣቆ እና አቡበከር ሳኒን፣ በቀኝ መስመር አብዱልከሪም መሃመድ እና በሃይሉ አሰፋን የተጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን የጅማ አባ ጅፋርን የጨዋታ ዕቅድ ቀድሞ እንደተረዳ በግልጽ ይታወቅ ነበር፡፡ ለዚህም መፍትሄ አድርገው የተጠቀሙት የመስመር አጥቂዎች እና የመስመር ተከላካዮች በጥልቀት ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል በመስግባት ይህንን የሜዳ ክልል በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው፡፡

ፈረሰኞቹ ይህንን የጨዋታ ዕቅድ በሚተገብሩበት ወቅት የጅማ አባ ጅፋር የመስመር ተከላካዮች እና የመስመር አማካዮች ቦታቸውን ለመሸፈን በራሳቸው የሜዳ ክልል እንዲቆዩ ተገደዋል፡፡ በተለይም የጅማ አባ ጅፋር የመስመር ተከላካዮች ከሜዳቸው እንዳይወጡ በፈረሰኞቹ የመስመር አጥቂዎች ጫና ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ የጨዋታ እቅድ በሚገባ አላንቀሳቅስ ያላቸው የጅማ አባ ጅፋር የመስመር ተከላካዮች ወደ ጉልበት አጨዋወት እና ብስጭት ሲገቡም መመልከታችን ይታወሳል፡፡

የጅማ አባ ጅፋር የመስመር አማካዮች ኳሶችን ይዘው ወደ ፊት ለመሄድ በሚሞክሩበት አጋጣሚ እገዛ ስለማይደረግላቸው በቀላሉ ኳሶቻቸው በፈረሰኞቹ እንዲነጠቁ ሲገደዱ ተመልክተናል፡፡ ይህም በመስመሮች ላይ ጥገኛ የነበረውን ክለብ በመስመር ማጥቃት እና በመስመር ላይ ብልጫን መውሰድ የተጋጣሚ ቡድንን የማጥቃት ዕቅድ ማበላሸት እንደሚቻል ከጅማ አባ ቡና ጨዋታ የምንማረው አንደኛው ነገር ነው፡፡

2. በጨዋታ ጅማሬ ላይ ጎል ማስቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊስን የቤት ስራ በብዙ እጥፍ ይቀንሳል፡፡

ባሳለፍነው የአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በግልጽ ያየናቸው እውነታዎች አሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ፣ ኤሌክትሪክን፣ አርባምንጭ ከነማን እና ጅማ አባ ጅፋርን ሲያሸንፍ ሶስቱም ክለቦች ላይ በተመሳሳይ ሶስት ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ማሸነፍ በቻላቸው ጨዋታዎች ላይ በርካታ ጎሎችን መስቆጠሩ በግልጽ የሚነግረን እውነታ አለ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚዎች ጎል ካልተቆጠረባቸው በስተቀር ከኳስ ጀርባ በመከማቸት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን እግር በእግር በመከተል ኳሶችን ማጨናገፍ የተጋጣሚ ቡድኖች የጨዋታ ዕቅድ ነው፡፡ ይህ የጨዋታ ዕቅድ በአብዛኛው የሚያገለግለው ለመጀመሪያ የጨዋታ ክፍል ጊዜ ሲሆን በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከዚህ ጎን ለጎን የሚጨመሩ ሌሎች ዕቅዶችም አሉ፡፡ ሰዓት ማባከን እንዲሁም ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ በማቆራረጥ የጨዋታውን ቀጣይነት ማቆራረጥ የተጋጣሚ ቡድኖች የጨዋታ ዕቅድ መሆኑን ተመልክተናል፡፡

ለዚህም መፍትሄ የሚሆነውን ወሳኝ ነጥብ በትላንትናው ዕለት ተመልክተናል፡፡ በጨዋታው 3 ደቂቃ ላይ የተቆጠረችው ጎል የቅዱስ ጊዮርጊስ የቤት ስራ ያቀለለች እንዲሁም የጨዋታውን መንፈስ ወደ እግር ኳስ ፉክክርነት የለወጠች ጎል ነበረች፡፡ ከዚህች ጎል በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች በሜዳው ላይ ማድረግ የፈለጉትን እንቅስቃሴ ከጫና ተላቀው ለማከናወን ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ በጨዋታ እንቅስቃሴ የግብ ዕድልን የመፍጠር ድክመቶች በጨዋታው ላይ ቢታይም ፈረሰኞቹ በጨዋታው ላይ የሚፈልጉትን አድርገው ለወውጣት ሞክረዋል፡፡

በያዝነው የውድድር ዓመት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከናወኑ ጨዋታዎች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ጎል ካስቆጠረ በኋላ እምብዛም ሲቸገር አላየንም፡፡ ይልቁን ከአንደኛው ጎል መቆጠር በኋላ ተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠርና ጎሎችን ማስቆጠር እየታዩ ያሉ እውነታዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚ ቡድኖች ላይ አስቀድሞ ጎል ለማስቆጠር መሞከር እና ለዚህም የሚረዳውን የጨዋታ ዕቅድ መተግበር ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ከጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ የምንማረው 2ኛው ነገር ነው፡፡


3. የአጥቂ አማካዮችን ክፍተት በመስመር አጥቂዎች እና በመስመር ተከላካዮች መሸፈን በዚህ ሰዓት ሁነኛ አማራጭችን ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጥቂ አማካይ ላይ የሚጠቀማቸው አማራጮች እየሳሱ መጥተዋል፡፡ በተለይም በትላንትናው ጨዋታ አብዱልከሪም ኒኪማ፣ አሉላ ግርማ እንዲሁም በቀደሙት ጨዋታዎች ላይ የታደለ መንገሻ መጎዳትን ተንተርሶ በዚህ ቦታ ላይ ቅያሪ ተጨዋችን ለመያዝ እንኳ አልተቻለም ነበር፡፡ ከዚህ ውጪም በዚህ ቦታ ላይ የሚሰለፉ ተጨዋቾች የሚና አተገባበር እና ከጨዋታው የሚጠበቅባቸውን ተግባራት መፈጸም መጓደል ጋር ተያይዞ ቡድኑ ሲቸገር ተመልክተናል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በትላንትናው ዕለት ከቀደሙት ጨዋታዎች በተለየ መስመሮችን በመጠቀም ላይ የተለየ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይህንን በቁጥር 1 ላይ ካነሳነው የጨዋታ እቅድ ጋር ማያያዙ እንዳለ ሆኖ በዚህኛው ጨዋታ ላይ ያሳየን አንድ እውነታ ግን አለ፡፡ የቡድኑ የአጥቂ አማካዮች ኳሶችን በተደጋጋሚ ወደ መስመር ያወጡ ነበር፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች እና የመስመር አጥቂዎች ኮሪደሩን በቅንጅት የሚጠቀሙበት መንገድ ካለፉት ጨዋታዎች አንጻር ይህኛው የሚበረታታ ነው፡፡

በትላንትናው ጨዋታ ላይ የመስመር ተከላካዮች እና የመስመር አጥቂዎች በአንድ ሁለት ቅብብል 5 ጊዜያት በላይ የጅማ አባ ጅፋር የመጨረሻ የመስመር ተከላካዮችን ቀንሰው ኳሶችን ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ይዘው መግባት ችለዋል፡፡ ምንም እንኳ ኳሶቹ በተገቢው መንገድ መድረስ ባይችሉም ይህ የጨዋታ እንቅስቃሴ የግብ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ግብ ለማስቆጠር የቀረበ የጨዋታ እንቅስቃሴ እንደሆነ መመልከት ችለናል፡፡

በተደጋጋሚ ወደ መስመር የሚወጡ ኳሶች በአንጻራዊ የአጥቂ አማካዮችን ከጫና ሲያላቅ ተመልክተናል፡፡ በተለይም የመስመር ተከላካዮች አሊያም የመስመር አጥቂዎች ሜዳውን አስፍተው ለመጫወት በሚሞክሩበት ሰዓት አንደኛው ተጨዋች በአግድሞሽ ሩጫ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ሲገባ የመስመር አማካዮች ከጫና ይላቀቁ ነበር፡፡ ይህም በፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን አቅራቢያ ፈረሰኞቹ በቁጥር በዝተው ኳሶችን እንዲቀባበሉ ያስቻላቸው አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህ የመስመር ተከላካዮችን እና የመስመር አጥቂዎችን በጥልቀት የማጥቃት ክልል ውስጥ በማስገባት እንዲሁም መስመሮችን የጨዋታ ዕቅድ በማድረግ የመስመር አማካዮችን ክፍተት መሸፈን እና የግብ ዕድሎችን መፍጠር ያለውን ፋይዳ ከጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ የምንማረው 3 ነገር ነው፡፡


Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ