የቅድመ ጨዋታ ዳሠሳ፦ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ (ቅዳሜ) አንስቶ በክልል እና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን የ8ኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ አዲግራት ተጉዞ ለማከናወን የብድኑ የልዑካን ቡድን አባላት በትላንትናው ዕለት ወደ አዲግራት አቅንተዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ እሁድ በ9 ሰዓት በአዲግራት ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል፡፡
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጉዞ ከከፍተኛ ሊግ እስከ ፕሪሚየር ሊግ!
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውስጥ በሰሜን ዞን ምድብ ሲወዳደር የቆየ ክለብ ነው፡፡ እጅግ አድካሚ በሆነው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የዞኑ
ሻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው ባሳለፍነው ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር፡፡ ይህ
ቡድን የከፍተኛ ሊጉ አሸናፊ ለመሆን በድሬዳዋ ስታዲየም ከጅማ ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ድል ሳይቀናው ቀርቶ በአጠቃላይ በከፍተኛ
ሊጉ 2ኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በፍጻሜው ጨዋታ የጅማ ከነማው ተጨዋች አቅሌስያስ ግርማ በ22ኛ
ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ጅማ ከነማ የከፍተኛ ሊጉ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከመጣ ጀምሮ ቡድኑን ለማጠናከር ተንቀሳቅሷል፡፡ ይህ
ክለብ ከ10 በላይ አዲስ ተጨዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን እንደ አዲስ በመገንባት ላይ የቆየ ክለብ ነው፡፡ ሙሉዓለም ጥላሁን፣ ሮቤል
ግርማ፣ በረከት ተሰማ፣ ቢኒያም አየለ፣ እዩብ ወልደማርያም፣ ወግደረስ ታዬ፣ ብሩክ አየለ፣ እንየው ካሳሁን፣ ተስፋዬ ዲባባ፣ ዋለልኝ ገብሬ፣ ዘውዱ መስፍን እና የመሳሰሉት ተጨዋቾች በዚህ ዓመት ብቻ ክለቡን ከአገር
ውስጥ ውድድር የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአገር
ውስጥ ከሚጫወቱ ተጨዋቾች ጎን ለጎን 3 የውጭ አገር ተጨዋቾችን አስፈርሟል፡፡ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች የቡርኪናፋሶ ዜግነት
ያለው ፕሪንስ ሰቪርኒሆ፣ ጋናውያኑ ፍሬዲክ ቦአቴንግ እና አብዱልራህማን ፉሴይኒ በዚህ የውድድር ዓመት ከውጭ አገራት ወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲን የተቀላቀሉ
ተጨዋቾች ናቸው፡፡
የዘንድሮ የውድድር ዓመት ቁጥሮች ስለ ሁለቱ ቡድኖች ምን ያሳያሉ?
ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው የውድድር አመት 5 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 3 ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥቶ የተቀረውን 2 ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈጽሟል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች መካከል 2 ጨዋታን በአሸናፊነት፣ 4 ጨዋታን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በ1 ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ በዚህ ውጤት መሰረት ፈረሰኞቹ 11 ነጥብ በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲ 10 ነጥቦችን በመያዝ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው 4 ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል፡፡ በእነዚህ 4 ጨዋታዎች ላይ 1 ጨዋታን ማሸነፍ ሲችል፣ በ1 ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዶ የተቀሩትን 2 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ጨዋታውን አጠናቋል፡፡ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ማሸነፍ የቻለው ኢትዮጵያ ቡናን ብቻ ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው 1-0 በሆነ ውጤት ነው፡፡ በሜዳው ሽንፈትን ያስተናገደው በመከላከያ ሲሆን ጨዋታው የተጠናቀቀው 1-0 በሆነ ውጤት ነው፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሜዳው 2 ጨዋታዎችን አቻ ያጠናቀቀው ከፋሲል ከነማ እና ከሲዳማ ቡና ጋር ሲሆን ከሲዳማ ቡና 0-0 እንዲሁም ከፋሲል ከነማ ጋር
2-2 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ በሜዳው ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ላይ 3 ጎሎችን ሲያስቆጥር 3 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ የሆነው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የውድድር ዓመት ከሜዳው ውጪ ያደረገው 3 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ነው፡፡ ከሜዳቸው ውጪ ተጉዘው ማድረግ ከቻሉት 3 ጨዋታዎች መካከል በአንድ ጨዋታ ላይ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ በተቀሩት 2 ጨዋታዎች ላይ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግቡ ከሜዳቸው ውጪ ሽንፈትን አላስተናገዱም፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ድል ያደረገው በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲሆን ያሸነፈውም
ክለብ ኢትዮ አሌክትሪክ ነው፡፡ ጨዋታው የተጠናቀቀበት ውጤት 3-1 መሆኑም ይታወሳል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሜዳቸው ውጪ በአቻ ውጤት የተለያዩት ከመቐለ ከነማ እና ከአርባምንጭ ከነማ ጋር ሲሆን የአቻነት ውጤቱ የሚከተለው
ነው፡፡ ወደ መቐለ ስታዲየም ተጉዘው ከመቐለ ከነማ ጋር 0-0 እንዲሁም ወደ አርባምንጭ ተጉዘው
1-1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ 4 ጎሎችን አስቆጥሮ 2 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች 8 ጎሎችን ሲያስቆጥር 2 ጎሎቹን አስተናግዷል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዪኒቨርሲቲ በበኩሉ በ7 ጨዋታዎች 7 ጎሎችን ሲያስቆጥር 5 ጎሎችን አስተናግዷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካይ በጨዋታ 1.6 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በጨዋታ በአማካይ 1.00 ጎል እያስቆጠሩ ለዚህ ጨዋታ ደርሰዋል፡፡ በመከላከል ረገድ ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታ በአማካይ 0.4 ጎሎችን ሲያስተናግድ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በጨዋታ በአማካይ 0.71 ጎል አስተናግዷል፡፡
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የጨዋታ አቀራረብ!
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በያዝነው የውድድር አመት በተለይም በቅርብ ጨዋታዎች ላይ
የሚታወቁ 11 ተጨዋቾች ያሉት ክለብ ነው፡፡ ምን አልባት በሴካፋ ዋንጫ ምክንያት ወደ ኬኒያ ያቀናው ግብ ጠባቂው በረከት
አማረን በዘውዱ መስፍን ከመቀየር ውጪ ቡድኑ የሚታወቅበት የጨዋታ አቀራረብ ያለው ቡድን ነው፡፡ በአሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሄር
የሚመራው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቱ በሜዳው 4-3-3 እንዲሁም ከሜዳው ውጪ 4-4-1-1 የጨዋታ ዘይቤን የመተግበር ልምድ
አለው፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ
በሜዳው ሲጫወት በ4-3-3 የጨዋታ አቀራረብ የሚጠቀማቸው ተጨዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ግብ ጠባቂ፡- በረከት አማረ
ተከላካዮች፡- እንየው ካሳሁን፣ በረከት ተሰማ፣ ተስፋዬ ዲባባ፣ ሮቤል ግርማ
ተከላካዮች፡- እንየው ካሳሁን፣ በረከት ተሰማ፣ ተስፋዬ ዲባባ፣ ሮቤል ግርማ
አማካዮች፡- አፈወርቅ ኃይሉ፣ አሳሪ አልመሀዲ፣ ዋለልኝ ገብሬ
አጥቂዎች፡- ፕሪንስ ሰቨሪንሆ፣ ሙሉአለም ጥላሁን፣ ከድር ሳሊህ
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ ለማጥቃት ቅድሚያ
የሚሰጥ ክለብ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው 3ቱ የፊት አጥቂዎች ሰፊ ጊዜያትን የሚያሳልፉት በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ነው፡፡
እነዚህ 3 አጥቂዎች ኳስ በቡድናቸው ተጨዋቾች እግር ስር ሲሆን መገኛቸው የተጋጣሚ ፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን አቅራቢያ ነው፡፡ አሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሄር
በቀኝ እና በግራ መስመር አጥቂነት የሚጠቀሟቸው ሁለት ተጨዋቾች የቡድኑ የማጥቃት ኃይል ናቸው፡፡ በተለይም የቅዱስ ጊዮርጊስ
የቀድሞ ተጨዋች ፕሪንስ ሰቬርኒሆ ለወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሁነኛ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኝ ተጨዋች ነው፡፡ ይህ ቡድን
የግራ እግር ተጨዋቹን ፕሪንስ ሰቬርኒሆን በቀኝ መስመር አጥቂነት፣ የቀኝ እግር ተጨዋቹን ከድር ሳሊህን በግራ መስመር አጥቂነት
ይጠቀማል፡፡
ይህ
ቡድን ደረቅ እና
ሙሉ በሙሉ አፈርማውን የሆነውን
ሜዳ በሚገባ የለመዱ ተጨዋቾች ይዟል፡፡ ኳስን በመመስረት እና በፈጣን
ቅብብል በሜዳው 3/4ኛ ክፍል በፍጥነት ይደርሳሉ፡፡ የመስመር አጥቂዎቹ ሜዳውን
አጥበብበው ይጫወታሉ። በተለይም የመስመር አጥቂዎቹ ኳስን ወደ ተጋጣሚ ተከላካይ የሚገፉበት መንገድ እና በቀጥታ ወደ ግብ የሚሞክራቸው ኳሶች
ማራኪ ናቸው፡፡ እነኚህ የመስመር አጥቂዎች በተደጋጋሚ የሚገኙት
የፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ መሆኑን ተመልክተናል።
የወልዋሎ
አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የአጥቂ አማካዮች ከኳስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማራኪ ነው፡፡ ለቀላል ቅብብሎች ራሳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡ የመስመር
አጥቂዎቹ በመስመሮች መካከል ከአጥቂ አማካዮች ኳስ ለመቀበል ያላቸው ዝግጁነት በጣም አስደናቂ ነው። ይህ ክለብ የሚፈጥራቸው አብዛኞቹ የግብ ዕድሎች መነሻቸው ከአጥቂ አማካዮች በመስመሮች መካከል ለፊት አጥቂው እና ለመስመር አጥቂዎች በሚደርሱ ኳሶች ነው። በተለይም የአጥቂ
አማካዮቹ በተከላካዮች እና በግብ ጠባቂው መሃል ለመስመር አጥቂዎች የሚያሻግሯቸው ኳሶች ለወልዋሎ አዲግራት የግብ ሙከራ አይነተኛ
እገዛ አላቸው፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለመልሶ ማጥቃት የተጋለጠ
ቡድን መሆኑ በግልጽ ይታያል፡፡ በተለይም ተጋጣሚ ቡድን ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርገው ሽግግር ፈጣን እና ክፍተቶችን የሚመለከት
ከሆነ ባለሜዳው ቡድን ጫና ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህ ክለብ ጎል እስኪያስቆጥር ድረስ ባለው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመሃል ተከላካዮችን
ወደ መሃል ሜዳ አስጠግቶ የሚጫወተው ሲሆን ቡድኑ ለማጥቃት ሙሉ አቅሙን ሲጠቀም ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርገው ሽግግር ደካማ
ነው፡፡ በዚህም መነሻነት ጎሎች እንደተቆጠረበት ተመልክተናል፡፡
በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት የማይሰለፉ ተጨዋቾች!
ከጉዳት ጋር ተያይዞ ሳላሃዲን ሰኢድ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ ታደለ መንገሻ እና አሜ መሃመድ የዚህ ጨዋታ አካል አይሆኑም፡፡ በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ ለአለም ብርሃኑ ወደ ስፍራው
ያልተጓዘ ተጨዋች ነው፡፡ እንዲሁም በያዝነው የውድድር ዓመት ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ወደ ዋናው ቡድን ያደጉት ዮሃንስ ዘገየ፣ አቤል አንበሴ እና ሳሙኤል ተስፋዬ ወደ አዲግራት ያልተጓዙ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
እናሸንፋለን፣
በሳንጃው ሙሉ እምነት አለን!
Comments
Post a Comment