ብሪያን ኡሙኒ ለጨዋታ ብቁ ባለመሆኑ ምክንያት በዚህ ወቅት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አይመለስም።
ለቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት አጥቂ እንዲሁም የመስመር አማካይ ሆኖ ተጫውቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው መልካም የሚባል እንቅስቃሴ አድርጓል። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ የሚባሉ ጎሎችን አስቆጥሯል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ለ2 አመታት የሚያቆይ ኮንትራት ፈርሞ በጉዳት ከሜዳ እስኪርቅ ድረስ በክለቡ ቆይታውን አድርጋል።
ብሪያን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለያየ ረጅም ጊዜያት ቢቆጠርም ባለፈው ሳምንት ብሪያንን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በድጋሚ የሚያገናኝ ዜና ተሰማ። ብሪያን ከጉዳቱ ማገገሙ ተጠቅሶ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመመለስ ጥያቄ እንዳቀረበ ተነገረ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥያቄውን ተቀብሎ ቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሙከራ እንደሚያደርግ ተገለፀ።
የፈረሰኞቹ ገጽ ምንጮች እንዳረጋገጡልን ከሆነ የብሪያን ኡሙኒ በያዝነው የውድድር ዘመን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመመለሱ ሂደት አልተሳካም። ይህም የሆነው ብሪያን ወደ ጠንካራ ልምምድ የሚሸጋገረው ከፊታችን ጥር ወር አንስቶ በመሆኑ ነው። በዚህ ወቅት የካፍ የተጨዋቾች ምዝገባ የሚጠናቀቅ በመሆኑ እንዲሁም ተጨዋቹን በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ መጠቀም ስለማይቻል የተጨዋቹ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመመለስ ዕድል ተጨናግፏል።
ብሪያን በዚህ ወቅት ቀላል ልምምዶችን በመስራት ላይ ይገኛል። ወደ ጨዋታ ለመመለስ እና የጨዋታ ብቁነትን ለማግኘት ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል ተጨዋቹ ለፈረሰኞቹ ገጽ ምንጮች ተናግሯል። ምን አልባት በመጪው የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያደርገው የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ሙከራ ለማድረግ እንደሚሞክር ብሪያን ኡሙኒ ለፈረሰኞቹ ገጽ ምንጮች ጨምሮ አሳውቋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ሰዓት ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚፈልጋቸው ተጨዋቾች ለጨዋታ ዝግጁ የሆኑ እንዲሁም በአህጉራዊ ውድድር ላይ በቋሚ 11 ውስጥ መሳተፍ የሚያስችል ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች ነው። ብሪያን ኡሙኒ ይህ እና ተያያዥ ጉዳዮች በዚህ ሰዓት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲመለስ ያላስቻለው ነጥብ ነው።
Comments
Post a Comment