ማሊያዊው የፊት እና የመስመር አጥቂ አማራ ማሌ አዲሱ ፈረሰኛ ለመሆን ተቃርቧል።




በአሁኑ ሰዓት በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በሙከራ ላይ ከሚገኙት 3 ተጨዋቾች መካከል የማሊ ዜግነት ያለው አማራ ማሌ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞችን ማሳመን እንደቻለ የፈረሰኞቹ ገጽ ታማኝ የመረጃ ምንጮች አሳውቀውናል። ይህ የፊት  እና የመስመር አጥቂ ተጨዋች በልምምድ ሜዳ እያሳየ ካለው ብቃት መነሻነት የክለቡ አሰልጣኞች በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ ተጨዋቹ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይጠቅማል ብለው በማመናቸው በቀጣይ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ተጨዋች መጪውን አዲስ አመት በማስመልከት በቀጣይ ቀናት ወደ ማሊ የሚጓዝ ሲሆን አዲስ አመትን በአገሩ አሳልፎ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ኮንትራት ይፈራረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮቻችን ያደረሱን መረጃ ያሳያል፡፡ 



አማራ ማሌ በማሊ እግርኳስ ክለብ ታሪክ ታላላቅ ስም ባላቸው ክለቦች ውስጥ ያለፈ ተጨዋች ነው። በአሁኑ ወቅት በማሊ ታላቅ ክለብ የሆነው የስታድ ማሊ ክለብ ተጨዋች ሲሆን 1ሜትር 82 ሳንቲሜትር ይረዝማል። ይህ ተጨዋች በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ታህሳስ 5 ቀን 1982 እንደተወለደ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ተጨዋቹ 25 ዓመቱ ሲሆን በሁለቱም እግሮቹ ኳስ መጫወት የሚችል ተጨዋች ነው፡፡


2009-2012 የማሊ ክለብ ለሆነው ባማኮ፣ 2013-2015 ለጆሊባ እንዲሁም 2016 ወደ ጊኒ ተጉዞ ለሆሪያ ክለብ መጫወት ችሏል፡፡ ከሆሪያ ክለብ ጋር ከተለያየ አንስቶ ለስታድ ማሊ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህ ተጨዋች በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ 2 ጨዋታዎች ላይ፣ በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ 2 ጨዋታዎች ላይ፣ 20 አመት በታች የአለም ዋንጫ ላይ 2 ጨዋታዎች ላይ፣ በቻን የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ 1 ጨዋታዎች ላይ፣ በቻን የአፍሪካ ዋንጫ 3 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ተጨዋቹ 2016 የጊኒ ክለብ የሆነው ሆሪያ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የዛምቢያውን ዜስኮ ዩናይትድን ሲገጥም 65 ደቂቃዎችን ያህል ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡


አማራ ማሌ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተያያዘ ታሪክ ያለው ተጨዋች ነው፡፡ 2013 ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጆሊባን ሲገጥም ይህ ተጨዋች በወቅቱ የጆሊባ ተጨዋች ሆኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገጥሟል፡፡ በዚያ ጨዋታ ላይ 78 ደቂቃ ተቀይሮ ገብቶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቷል፡፡ በወቅቱ ይህ ጨዋታ በማሊ የተከናወነ ሲሆን ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡


አማራ ማሌ ከ3 ዓመታት በፊት የነበረውን የእግርኳስ እንቅስቃሴ ከታች ባለው ቪዲዮ ላይ ተካቷል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ