ዛሬ የጨዋታ ቀን ነው!



የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ያልረገጡት ክልል ውስን ነው፡፡ ያልሄዱበት የኢትዮጵያ መዳረሻዎች ጥቂት ናቸው፡፡ በሰሜን ቢባል በደቡብ፣ በምስራቅ ቢባል በምዕራብ ታላቁን ክለባቸው ተከትለው ተጉዘዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ አርማን ከፍ አድርገው በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ላይ አሷይተዋል፡፡ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየዘመሩ፣ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየወጉ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ውብ አርማዎችን ለብሰው ኢትዮጵያን ዞረዋል፡፡

አዲግራት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጉዞ ታሪክ ከአዲስ አበባ የራቀ ቦታ ላይ ያለች ከተማ ናት ብንል የተሳሳትን አይመስለንም፡፡ ይህች ምስረታዋን በ1811 ዓ.ም ያደረገችው ከተማ ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ልትደምቅ የተመረጠች ከተማ ሆናለች፡፡ የቦታ ርቀት፣ አየር ጸባይ ለውጥ፣ ነባራዊ ሁኔታ እና መሰል እንቅፋቶች ወደ ኋላ የማይመልሳቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ካለፉት ጥቂት ቀናት አንስቶ ወደ ስፍራው በማቅናት ላይ ይገኛሉ፡፡

አዲግራት ከለመደችው ቢጫ ቀለም በተለየ በዛሬው ዕለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀለማት በሆኑት ቢጫ፣ ቀይ እና ብርቱካንማ ቀለማት ትቀልማለች፡፡ በጥሩ ሰዓሊ እንደተሳለ ስዕል ደምቃ ትታያለች፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስን በሰፊ ርቀት የሚመራውን ክለብ ታስተናግዳለች፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲባል ስሙን ከሩቅ ሲሰሙ የነበሩት የከተማው ነዋሪዎች ክለባችንን እና ደጋፋዎቹን ይተዋወቃሉ፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ክልል ስታዲየም የሚያቀናው ለመርኃ ግብር ማሟያነት አይደለም፡፡ ለመርኃ ግብር ማሟያነት የሚጫወት ክለብ ቢሆን ኖሮ ደጋፊዎቹ 900 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ባልተጓዙ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የክልል ስታዲየም ፎቢያ የለበትም፡፡ ይህንን ጠንቅቀው የሚያውቁ ደጋፊዎቹ ክለባቸውን በፍጹም ብቻውን ለመተው አይሞክሩምና 900 ኪሎ ሜትሮችን አቋርተው አዲግራት ስታዲየም ላይ ይታደማሉ፡፡ ክለባቸውን በፍጹም ፍቅር በመነጨ ጥልቅ ስሜት ይደግፋሉ፡፡ 3 ነጥብ ይዘው ለመውጣት የሚጠበቅባቸውን አሻራ በጨዋታው ላይ ያሳርፋሉ፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታውን ዛሬ በ9 ሰዓት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ