የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአማካይ ተከላካይ ተጨዋች ናትናኤል ዘለቀ በህንድ አገር በሚገኘው በፎርቲስ የህክምና ማዕከል የተሳካ ቀዶ ጥገና አከናወነ፡፡


ናትናኤል ዘለቀ በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ውስጥ አልፎ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና ቡድን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በወጣትነት ዕድሜው በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የአሰልጣኝነት ጊዜ የተከላካይ አማካይ ሚና ሲሰጠው ለብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተስፈኛ ተጨዋች መሆኑን ካሳየበት ጊዜ አንስቶ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በቋሚነት በመሰለፍ ላይ ይገኛል፡፡



ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሳካቸው 14 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች መካከል በ4ቱ ዋንጫዎች ላይ አሻራውን አሳርፏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት አዲስ ታሪክ ሲሰራ በታሪክ ቀያሪው ቡድን ስብስብ ውስጥ ተካቶ አይነተኛ ሚናውን አበርክቷል፡፡


 

ናትናኤል ዘለቀ ካለፉት አመታት አንስቶ ተደጋጋሚ የትከሻ ጉዳቶች ሲያስተናግድ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከጉዳቱ በፍጥነት በማገገም ወደ ጨዋታ እየተመለሰ ክለቡን ሲያግዝ ተመልክተነዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አመራሮች ተጨዋቹ በተደጋጋሚ ከሚገጥመው የትከሻ ጉዳት በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝ በማሰብ ወደ ህንድ አቅንቶ የህክምና ክትትል እንዲያደርግ ዕድሎችን አመቻችተውለት ከ10 ቀናት በፊት ወደ ህንድ አቅንቷል፡፡ 

ናትናኤል በህንድ ሙምባይ በፎርቲስ የህክምና ማዕከል የህክምና ክትትሉን እንደጀመረ ሰምተናል፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ ናትናኤል የገጠመው የትከሻ ህመም ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልገው በማመን የቀዶ ጥገና ህክምና ባሳለፍነው ሳምንት አድርገውለታል፡፡



በህንድ ፎርቲስ ህክምና ማዕከል ያደረገው የቀዶ ጥገና ህክምና የተሳካ እንደነበር የህክምና ባለሙያዎቹ እንዳሳወቁት ናትናኤል ዘለቀ ለፈረሰኞቹ ገጽ ተናግሯል፡፡ ከቀዶ ጥገናው ህክምና ጎን ለጎን የፊዚዮቴራፒ ህክምና ክትትል እየተሰጠው ይገኛል። ይህ የፊዚዮቴራፒ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰም በኋላ የሚቀጥል ይሆናል። 



በዚህ ሰዓት በህንድ አገር በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኘው ናትናኤል የህክምና ክትትሉን አላጠናቀቀም፡፡ በመጪው ቅዳሜ ቀዶ ጥገና ካከናወኑለት የህክምና ባለሙያዎች ጋር ቀጣይ ቀጠሮ አለው፡፡ በቀጣይ ቀጠሮው ወደ ጨዋታ የሚመለሰው ከምን ያህል ጊዜ በኋላ እንደሆነ እንደሚታወቅ ነግሮናል። በመጪው ቅዳሜ ከሚኖረው የህክምና ክትትል በኋላ ወደ አዲስ አበባ የሚመለስበት ቀን የሚታወቅ መሆኑን ናትናኤል ዘለቀ ለፈረሰኞቹ ገጽ ጨምሮ ተናግሯል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ጅማ - ደማችን የፈሰሰባት፣ ድላችንን የተቀማንባት ከተማ!

በሚዲያ አጠቃቀም የኋልዮሽ ጉዞ ላይ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ!

በፖለቲካ የተዋጠው፣ የፖለቲከኞች እጅ የተጫነው እግርኳሳችን! - በፈረሰኞቹ ገጽ