ባለፉት 5 ጨዋታዎች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ይጎድለዋል?
7 ሳምንታትን ባሳለፈው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ቅዱስ
ጊዮርጊስ 5 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ውስጥ 3 ጨዋታዎችን በድል ሲወጣ 2 ጨዋታዎችን በአቻ
ውጤት አጠናቋል፡፡ በዚህም ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥቦች ውስጥ 11 ነጥቦችን በማሳካት በፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የፈረሰኞቹ ገጽ ያለፉትን 5 ጨዋታዎች ተንተርሶ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደካማ ጎን ምን ላይ ነው የሚለውን ከመፍትሄ ኃሳቦች ጋር አያይዞ
ለማዳሰስ ይሞክራል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ዓመታት ሲተገብረው ከነበረው የእግርኳስ ፍልስፍና
አንጻር የአሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ቡድን ሽግግር ላይ እንዳለ በግልጽ ያስታውቃል፡፡ በተለይም በቋሚነት እየተጠቀመባቸው ካሉት ተጨዋቾች መካከል 5 ተጨዋቾች ያህል ለክለቡ እንግዳ ናቸው፡፡
አብዱልከሪም መሃመድ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ ኢብራሒም ፎፋና፣ ጋዲሳ መብራቴ እና አሜ መሃመድ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ የመሰለፍ
ዕድል ያገኙ አዲስ ፈራሚ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ክለቡን በያዝነው የውድድር ዓመት የተቀላቀሉ እንደመሆናቸው እንዲሁም
አዲሱ አሰልጣኝ እየተገበሩት ያሉት የጨዋታ ዘይቤ ለነባር ተጨዋቾች ለማስረጽና እንዲሁም ነባር እና አዲስ ተጨዋቾችን ለማቀናጀት
ጊዜ እንደማስፈለጉ ያህል ክፍተቶች የሚጠበቁ ናቸው፡፡ አሰልጣኞች ቡድናቸውን ከልምምድ ሜዳ ባልተናነሰ ሁኔታ እየገነቡ የሚሄዱት
በጨዋታዎች ላይ ነው፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ የተጨዋቾችንም ሆነ የሚና ለውጦች እያደረጉ፣ የተጨዋቾችን ክፍተት እና ጎዶሎ ጎን እያረሙ
እና ወደሚፈልጉት የጨዋታ ዘይቤ ለመምጣት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ የፈረሰኞቹ ገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእንዲህ አይነት የሽግግር ጊዜ ላይ
እንደሚገኝ ያምናል፡፡
በሽግግር ላይ እንዲሁም በቡድን እና በጨዋታ ዘይቤ ትግበራ ላይ የሚገኘው
ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበትን ክፍተት ብናነሳ ግን መልካም ነው ብለን እናምንለን፡፡ በመሆኑም ባለፉት 5 ጨዋታዎች ላይ የታዩ ጉድለቶችን
እያነሳን እንዲሁም መታረም ያለባቸው ከፍተቶች እየጠቆምን ምልከታዎችን እናስፍር፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት 5 ጨዋታዎች ላይ 4-3-3 የጨዋታ ታክቲክ
አቀራረብን ተግብሯል፡፡ ምን አልባት ከ4-3-3 የተለየ የቸዋታ ዘይቤ የተገበረው በይርጋለም ስታዲየም በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ
ክፍለ ጊዜ ላይ ነው፡፡ ይህም ወደ 4-2-3-1 የተደረገ ሽግግር ሲሆን ከዚህ ጨዋታ ውጪ ያሉ ጨዋታዎች በጠቅላላው በ4-3-3 የቸዋታ
አቀራረብ ላይ የተመሰረቱ ነበሩ፡፡
አብዛኛው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንደሚያውቁት የቅዱስ ጊዮርጊስ
አይነተኛ ችግር ያለው ኳሶች ከግብ ጠባቂ ተነስተው በተከላካይ አማካዮች ተሻግረው የተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲደርሱ ነው፡፡ ቡድኑ ኳሶችን
ሲመሰርት እና ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ሲደርስ ብዙም ጫና ውስጥ አይወድቅም፡፡ ሆኖም የተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲደርስ ኳሶችን የማንሸራሸር እና
በተጋጣሚ ቡድን አማካዮች እና ተከላካዮች መሃል የሚደረገው ቅብብል ይደበዝዛል፡፡ የኳስ ቅብብሎቹ በተደጋጋሚ ይቋረጣሉ፡፡ የግብ
ዕድል ለመፍጠር እንኳ አቅም ያነሳቸው ቅብብሎሽ ይበረክታሉ፡፡ ለመሆኑ የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
1.የአጥቂ አማካዮች ሚና!
የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች የቡድኑን የጨዋታ ሂደት ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ
የመጀመሪያ ዕቅዳቸው ኳሶች ከግብ ጠባቂ ተነስተው በተዋረድ እና በቀላል ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ሜዳ እንዲደርስ የማድረግ መንገድ በተጨዋቾች
ላይ ማስረጽ ነው፡፡ በዚህ ላይ ጊዜ ወስደው ሰርተዋል ማለት እንችላለን፡፡ የፈረሰኞቹ ገጽ በተከታተላቸው ልምምዶች ላይ አሰልጣኞቹ
ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ የቆዩት ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር ላይ ኳሶች ከራሳቸው ሜዳ በሚነሱበት ሂደት ላይ
ነው፡፡ ይህም ግብ ጠባቂ፣ የመስመር እና የመሃል ተከላካይ እንዲሁም የተከላካይ አማካይ በዚህ ሽግግር ወቅት የሚኖራቸው የቦታ አያያዝ
እና የጨዋታ ተግባራትን የተመለከተ ተደጋጋሚ ስልጠና በአሰልጣኞቹ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ስልጠና ረጅም ጊዜያትን የፈጀው በተከላካይ
ክፍል ተጨዋቾች ላይ ነው፡፡ እነዚህ ተጨዋች በቀላል የኳስ ቅብብል እና ከተጋጣሚ የፊት መስመር ተጨዋቾች ጫና ተላቀው ኳሶችን ወደ
ተጋጣሚ ሜዳ የሚያሸጋግሩበት ስልጠና ረጅሙን ጊዜ ወስዷል፡፡ ይህም ተከላካዮች በሜዳቸው ስህተትን እንዳይሰሩ እና በቀላሉ የተጋጣሚ
ፊት መስመር ተጨዋቾችን ቀንሰው እንዲሸጋገሩ ለማስቻል የተሰጠ ስልጠና ነው፡፡
በፈረሰኞቹ ገጽ እምነት የተከላካይ ክፍል ተጨዋቾች የተሰጣቸውን ያህል
ስልጠና የቡድኑ ከወደብ በላይ ያሉ ተጨዋቾች አግኝተዋል ብለን አናምንም፡፡ ይህም ቡድኑ ከሜዳው ተነስቶ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ክፍል
ሲገባ ያለው ክፍተቶች ያሳያሉ፡፡ በተለይም ይህ ክፍተት በአጥቂ አማካይ በሚሰለፉ ተጨዋቾች ላይ ጎልቶ ይታያል፡፡ ምን አልባት አሰልጣኞቹ
ይህንን ክፍተት በጨዋታዎች ላይ ለማረም እና ተግባራዊ ስልጠናውን በጨዋታ ላይ አስታከው ለመስራት አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም
በጨዋታ ላይ በዚህ ስፍራ ላይ የሚታይ ክፍተት ይታያል፡፡
በ4-3-3 የጨዋታ ዘይቤ የቡድኑ የአጥቂ አማካይ ላይ የሚሰለፉ ተጨዋቾች
የቡድኑ ሁነኛ የማጥቃት ኃይል ናቸው፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ቡድኑ ለሚያደርገው የተሳኩ ቅብብሎች እና የግብ ዕድል ፈጠራ ላይ አሻራቸው
የጎላ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አመታት ይቸገርበት የነበረው ቦታ ይህ ቦታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በዚህ ቦታ ላይ ዘንድሮም
እየተጠቀማቸው የሚገኙት ተጨዋቾች ከዚህ በፊት በዚህ ቦታ ላይ እየተሰለፉ የሚገኙ ተጨዋቾች ሲሆኑ አአሁን ላይ እየታየ ያለውም ክፍተት
ከዚህ በፊት ከምናወራቸው ክፍተቶች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
በያዝነው ውድድር ዓመት 2 የአጥቂ አማካይን እየተጠቀመ የሚገኘው ቅዱስ
ጊዮርጊስ በዚህ ቦታ ላይ የተለያዩ ተጨዋቾችን ተጠቅሟል፡፡ አብዱልከሪም ኒኪማ፣ ምንተስኖት አዳነ፣ አሉላ ግርማ፣ አዳነ ግርማ እና
ጋዲሳ መብራቴ በዚህ ቦታ ላይ የመሰለፍ ዕድል ያገኙ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ በአንድ ጨዋታ ላይ ብቻ በዚህ ቦታ ላይ ከታየው ጋዲሳ መብራቴ
ውጪ የተቀሩት ተጨዋቾች በአጥቂ አማካይ ቦታ ላይ በተደጋጋሚ የመሰለፍ ዕድልን አግኝተዋል፡፡
ይህ የአጥቂ አማካይ ሚና የሚፈልገው አንድ ዲስፕሊን አለ፡፡ ይኸውም
በትክክለኛ ጊዜ ላይ ትክክለኛ ቦታ ላይ መገኘትን ይፈልጋል፡፡ የአጥቂ አማካይ ሚናን የተሰጣቸው ተጨዋች በተጋጣሚ ቡድን የተከላካይ
እና የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች መካከል መገኘት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡ የአጥቂ አማካይ ተጨዋቾች ሁነኛ ቦታው ይህ ቦታ ነው፡፡
በዚህ ቦታ ላይ ራሳቸውን በመስመሮች መካከል ኳሶች እንዲደርሳቸው ምቹ አድርገው መገኘት ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ኳሶች ተመስርተው
ከተከላካይ ወደ ተከላካይ አማካይ ሲሸጋገሩ ራሳቸውን በተጋጣሚ ቡድን የአማካይ ስፍራ ተጨዋቾች እና የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾች መሃል
ላይ በሚገኝ ቦታ ላይ አመቻችተው በመገኘት ኳሶችን መቀበል ይገባቸዋል፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነት ቅብብሎች በአብዛኛው እንቅስቃሴ
ላይ መመልከት አልቻልንም፡፡ -
በተጋጣሚ ቡድን የተከላካይ እና የአማካይ ስፍራ ላይ የሚገኙ የአጥቂ
አማካዮች ፊታቸውን 45 ዲግሪ ወደ ተከላካዮች አዙረው ኳስ መቀበል ከቻሉ በቀጥታ የሚያገኙት የተጋጣሚ ቡድንን ተከላካይ ነው፡፡
ይህም ኳሶች ከግብ ጠባቂ አንስቶ ተመስርተው እና ሂደታቸውን ጠብቀው ሲመጡ እንዳይቆራረጡ የአጥቂ አማካዮች ሁነኛ ቦታ ላይ መገኘታቸው
የግድ ይላል፡፡ ይህም ኳስች እንዳይቆራረጡ ከማድረግ ጎን ለጎን በተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሁነኛ መፍትሄ ይሆናል፡፡
የአጥቂ አማካዮች መገኘት ያለባቸው ቦታ በጣም ጫና ያለበት ቦታ እንደሆነ
ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ቦታው በሁለት የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች መሃል የሚገኝ እንደመሆኑ ኳስ በተቀበሉበት ፍጥነት በተጋጣሚ ቡድን
ተጨዋቾች ጫና ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ በተጨማሪም ቦታው ከሌሎች ቦታዎች በተለየ በርከት ያሉ ተጨዋቾች የሚሰባሰቡበት ቦታ እንደመሆኑ
ኳሶችን በተደጋጋሚ መነጠቆች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በዚህም ተጨዋቾች በዚህ ቦታ ላይ ተገኝቶ ኳሶችን መቀበል ስጋት ውስጥ ሊጥላቸው
እንደሚችል ይገመታል፡፡ ሆኖም በዚህ ቦታ ላይ የሚሰለፉ ተጨዋቾችን የማዘጋጀት እና ያለውን ነባራዊ እውነታ ማስረዳት ከአሰልጣኞች
ይጠበቃል፡፡ ይህንን ልንል የተገደድነንበት እውነታ አለ፡፡
በዚህ ቦታ ላይ የመሰለፍ ዕድል የገጠማቸው ፈረሰኞች በተደጋጋሚ ቦታቸውን
በመልቀቅ ወደ ኋላ ተስበው ይጫወታሉ፡፡ ራሳቸውን የአጥቂ አማካይ መገኘት ካለበት ቦታ በማውጣት በፍጥነት ለተከላካይ አማካዮ ቀርበው
ኳሾችን ይቀበላሉ፡፡ በውስን ጨዋታዎች ላይ የአጥቂ አማካዮች የተከላካይ አማካዮን ሚና ወስደው ሲተገብሩም በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡
ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ሲሆን በተጨማሪም የቡድኑ የጨዋታ ዕቅድ የሚያበላሽ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የአጥቂ አማካዮች ወደዚህ
አይነት ተግባር የሚሸጋገሩት በቦታቸው ላይ ያለውን ጫና በመስጋት እንዲሁም ከጫናዎች ወጥተው የተረጋጋ የኳስ ቅብብል ለማድረግ የሚሻል
ነጻ ቦታን በመፈለግ መሆኑ እሙን ነው፡፡
2. የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀርፋፋ ቅብብል እና ሽግግር!
ባለፉት አመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚለይባቸው ጥንካሬዎች አንዱ ከመከላከል
ወደ ማጥቃት የሚያደርገው ፈጣን ሽግግር ይገኝበታል፡፡ በዚህ ፈጣን ሽግግር በመታገዝ ፈረሰኞቹ በርካታ ጎሎችን ማስቆጠራቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ጥንካሬ ባሳለፍነው ዓመት በግልጽ የሚታይ እውነታ ነበር፡፡ ሆኖም በያዝነው የውድድር ዓመት ላይ ባየናቸው ውስን ጨዋታዎች ላይ
ይህ ጥንካሬን በሜዳ ላይ እየተመለክትን አይደለም፡፡ ፈረሰኞቹ የሚያደርጓቸው ቅብብሎች እና ሽግግሮች በፍጥነት ያልታጀቡ እንዲሁም
የተጋጣሚ ቡድን ራሱን የሚያደራጅበት ጊዜን የሚሰጥ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ባልተለመደ ሁኔታ ቀርፋፋ እግር ኳስን እየተገበረ ይገኛል፡፡
ኳሶች ከግብ ጠባቂው ተነስተው ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመድረስ የሚደረጉ ቅብብሎሽ በጣም ቀስ ባሉ ቅብብሎች የታጀቡ ናቸው፡፡
ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ክፍል ከደረሰም ይህ ቀርፋፋ ቅብብል አይለቀውም፡፡ ይህም ተጋጣሚ ቡድን ስህተትን ቢሰራ እንኳ ስህተቱን የሚያርምበት
ጊዜ ይሰጣል፡፡ በመሃል ሜዳ ተጨዋቾችን በማካመቻት ለታወቀው የሊግ ውድድር ቀርፋፋ እግርኳስን መጫወት ለተጋጣሚ ቡድን ተጨማሪ ዕድልን
መስጠት ነው ብለን እናምናለን፡፡ በመሆኑም ኳሶን በመመስረት እና ኳሶችን በማደራጀት ወደ ማጥቃት ወረዳ ለመግባት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች
በፈጣን ቅብብል እና ሽግግር ሊታገዙ ይገባል፡፡
3. በተጋጣሚ ቡደን ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የጨዋታ ዕቅድ!
ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዝነው ውድድር ዓመት የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረገው
ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኢትዮ. ኤሌክትሪክ 1 ነጥብ ፍለጋን ወደ ሜዳ ስላለገባ
እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመፈተን ስለሞከረ ነው፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመሳሳይ 4-3-3 የጨዋታ ዘይቤን
ለመተግበር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከወገብ በላይ ያለው የኤሌክትሪክ ተሰላፊዎች ለማጥቃት ያላቸው ተነሳሽነት ማራኪ ነበር፡፡ ይህም ለቅዱስ
ጊዮርጊስ የተመቸ ነበር፡፡
መቐለ ከነማ እና አርባምንጭ ከነማ(በመጀመሪያው አጋማሽ) ሙሉ በሙሉ
ለመከላካል ቅድሚያ የሰጡ ቡድኖች ነበሩ፡፡ እነዚህ ቡድኖች ከኳስ ጀርባ የሚሆኑ 10 ተጨዋቾችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ይህም ለቅዱስ
ጊዮርጊስ እጅግ ፈታኝ ሆኖበት ታይቷል፡፡ ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች እግር ስር ስትሆን የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋችን እግር በእግር
እየተከተሉ የመጫን አጨዋወት ላይ ፈረሰኞቹ ጫና ውስጥ ሲገቡ ተመልክተናል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በቅርብ ለመረዳት ለሞከረ ከቅዱስ
ጊዮርጊስ ጋር የሚጫወቱ በርካታ ቡድኖች እንዲህ አይነት አጨዋወትን ይዘው እንደሚመጡ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች
ተጋጣሚ ቡድኖች ለሚያደርጉት ይህን መሰል አጨዋወት መፍትሄ ይዘው ሊቀርቡ ይገባል፡፡ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ
የተንቀሳቀሰው በተጋጣሚ ቡድን ፈቃደኝነት አሊያም በጨዋታ ላይ በሚፈጠሩ ሁነኛ አጋጣሚዎች አንድ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ነው፡፡ እንዲህ
አይነት አጋጣሚዎች ካልተከሰቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ዕድል የመፍጠርም ሆነ ተጋጣሚ ቡድንን የመጫን ሂደት ላይ ደካማ ሲሆን ታዝበናል፡፡
እንደ አስፈላጊነቱ ኳስን ለረጅም ሰዓታት ይዞ የተጋጣሚ ቡድንን ማስከፈት ካልተቻለ ለተጋጣሚ ቡድን ኳሱን ሰጥቶ ተጋጣሚ ቡድን ከሜዳው
እንዲወጣ ማስገደድም ተግባራዊ ቢደረግ አይከፋም ብለን እናምናለን፡፡ ይህም በፈጣን ሽግግር የግብ ዕድል ለመፍጠር ይረዳል፡፡
4. የመስመር አጥቂዎችን አጠቃቀም!
ባለፉት ጨዋታዎች ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች የመስመር አጥቂዎችን
የሚጠቀሙበት ሁኔታ ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ተመልከተናል፡፡ የግራ እግር ተጨዋቹ ጋዲሳ መብራቴ በግራ፣ የቀኝ እግር ተጨዋቾቹ
ኢብራሒም ፎፋና፣ አቡበከር ሳኒ እና በሃይሉ አሰፋ በቀኝ መሰመር አጥቂነት ሲሰለፉ አይተናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ጋዲሳ መብራቴ ተጠባባቂ
ወንበር ላይ በተቀመጠበት ጊዜ የቀኝ እግር ተጨዋቾች በግራ መስመር ላይ ሲሰለፉ ታይቷል፡፡
የግራ እና የቀኝ መስመር አጥቂዎች (በሚጫወቱበት የግራ እና የቀኝ
መስመር ላይ ሲሰለፉ) የሚጠበቁ ኹነቶች አሉ፡፡ ኳሱን ከመስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ለፊት አጥቂው ማሻገር፣ የተጋጣሚ ቡድን የመስመር
ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ሳጥን ውስጥ ኳሱን ይዞ መግባት፣ ለአግድሞሽ ሩጫ ለሚዘጋጁ የአጥቂ አማካዮች በመስመሮች መካከል ኳሶችን
ማድረስ እና ከመስመር ተከላካዮች ጋር የተጋጣሚን ቡድን የመስመር ተከላካዮች ጋር የመቀነስ ሂደት ከእነዚህ የመስመር አጥቂዎች ይጠበቃል፡፡
እዚህ ላይ የተለየ ነጥብ እናንሳ፡፡ ጋዲሳ መብራቴ በሃዋሳ ከነማ እያለ
የሚሰለፈው በቀኝ መስመር አጥቂነት ነበር፡፡ በውስን ጨዋታዎች ላይ በገራ መስመር አጥቂነት ተሰልፎ ያነው ቢሆንም ጥሩ ለመንቀሳቀስ
ግን በቀኝ መስመር መሰለፍ ምቾት እንደሚሰጠው ታዝበናል፡፡ ኢብራሒም ፎፋና በኢትዮ ኤሌክትሪክ በመስመር አጥቂነት ሲሰለፍ የሚሰጠው
ሚና የግራ መስመር አጥቂነት ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ተጨዋቾች ጥሩ ፍጥነት ያላቸው እና ተጨዋቾችን መቀነስ የሚችሉ ናቸው፡፡
የግራ እግር ተጨዋችን በቀብ የቀኝ እግር ተጨዋችን በግራ መስመር ስናሰልፍ
የሚገኙ ጥቅሞች ይኖራሉ፡፡ በተይም ተጨዋቾቹ ኳስን ወደ ተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች በድፍረት የሚገፉ ከሆነ ምርጫቸውን የሚያደርጉት
ሜዳውን እያጠበቡና ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን እየገፉ መግፋትን ይመርጣሉ፡፡ ይህም የተጋጣሚ ቡድን የተከላካይ ክፍል እንዳይረጋጋ
ከማስቻል በላይ ስህተቶችን እንዲሰራ ያስገድዳሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የቡድኑ የአጥቂ አማካዮች እና የፊት አጥቂዎች በቂ ክፍተት
እና በመስመሮች መካከል ኳሶችን የመቀበል ዕድል ይመቻችላቸዋል፡፡
በመሆኑም የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች ቡድኑ ከሚተገብረው ኳስን ተቆጣጥሮ
የመጫወት ፍልስፍና ጎን ለጎን የመስመር አጥቂዎችን ቀያይሮ የመጠቀምን ጥቅምና ጉት በልምምድ ሜዳ ቢሞክሩት እና ተገቢ ሆኖ ከተገኘ
ወደ ተግባር ቢለወጥ መልካም ነው፡፡
Comments
Post a Comment