የቅዱስ ጊዮርጊስ የሴቶች ቡድን 2ኛ ተከታታይ ሽንፈትን አስተናግደዋል።
ከ17 ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ
መልስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን ወደ ጨዋታ ተመልሰዋል፡፡ የ ዛሬ በ9 ሰዓት በተካሄደው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 3ኛ ሳምንት ጨዋታ በሀዋሳ ከነማ 3—2 በሆነ ውጤት ሽንፈትን አስተናገደዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን 10ኛ ደቂቃ ላይ ቤተልሄም ሰማን ባስቆጠረችው ጎል መሪ መሆን ቢችሉም፣ ሀዋሳ ከነማ በ14ኛ እና በ42ኛ ደቂቃ ላይ ባስቆጠሩት ጎል ታግዘው የመጀመሪያው አጋማሽ በሃዋሳ ከነማ 2—1 መሪነት ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ በ46ኛ ደቂቃ ላይ ቤተልሄም ሰማን ለራሷም ሆነ ለክለቧ 2ኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲቀጥል አስችላ ነበር። ሆኖም በ90ኛ ደቂቃ የሃዋሳ ከነማዋ የመስመር ተጨዋች 2 የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾችን በአስገራሚ ፍጥነት በማለፍ ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻገረችውን ኳስ ሀዋሳዎች ወደ ጎልነት ቀይረው ሃዋሳ ከነማዎች ጨዋታውን 3–2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን በ2010 ዓ·ም የሴቶች የአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር 3 ጨዋታ አድርገዋል። ካለፉት 3 ጨዋታዎች ውስጥ በ2 ጨዋታዎች ሽንፈትን ሲያስተናግዱ በአንድ ጨዋታ ድል አድርገዋል። ሴት ፈረሰኞቻችን ሽንፈትን ያስተናገዱት በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በሀዋሳ ከነማ ሲሆን ማሸነፍ የቻሉት ጌድኦ ዲላን ነው። ባለፉት ጨዋታዎች ላይ 5 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 5 ጎሎችን አስተናግደዋል። በዚህም በጨዋታ በአማካይ 1·67 ጎል ሲያስቆጥሩ፣ 1.67 ጎሎችን አስተናግደዋል።
ማራኪ የእግርኳስ ፍሰትን እየተገበ የሚገኘው የአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ስብስብ የእግርኳስ ቤተሰቡን የሚያስደስት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ሴት ፈረሰኞቻችን በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታጀበ፣ በርካታ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ። ሆኖም የተገኙ የጎል ዕድሎችን ወደ ጎልነት በመቀየር ረገድ ድክመት ይታይባቸዋል። ይህንን ክፍተታቸውን ማረም ከቻሉ በቀጣይ ብርቱ ተፎካካሪ ለመሆን የሚያስችል ብቃት እንዳላቸው እየተመለከትን እንገኛለን።
Comments
Post a Comment